ʿታዳጊʾ ክልሎች ፡  ከፖለቲካዊ ጭቆና ወደ ኢኮኖሚያዊ  መገለል?

(በዑስማን ሰይድ) – የኢህአዴግ  መስራች የሆኑት አራቱ ብሔራዊ ድርጅቶች ከሚመሯቸው ትግራይ ፤ አማራ ፤ ኦሮሚያ እና ደቡብ ክልሎች ውጭ የሚገኙት የኢትዮጵያ ሶማሌ፤ የአፋር ፤ የሐረሪ ፤ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና የጋምቤላ ክልሎች የኢህአዴግ አጋር ፓርቲዎች በመባል የሚታወቁት የፖለቲካ ድርጅቶች የሚመሯቸው ናቸው፡፡ ስለዚህ በአጋሮች የሚመሩት የሚለውን አባባል እየተጠቀምን እንግለፃቸው፡፡

እነዚህን በኢህአዴግ አጋሮች የሚመሩ ክልሎች በተመለከተ ከዚህ ቀደም ʿጥልቅ ተሃድሶ ለኢንዶውመንትʾ  በሚል መጠነኛ አስተያየት በዚህ ገፅ አስፍሬ  ነበር፡፡  ዛሬ ደግሞ በአጠቃላይ የሩብ ክፍለ ዘመን የኢህአዴግ አመራር በእነዚህ ክልሎች እና በኢህአዴግ የሚመሩት ክልሎች መካከል በአሳሳቢ ደረጃ ሊታይ የሚገባው የኢኮኖሚ ልማት ልዩነት ስለመኖሩ እና ይህም በአጋሮቹ  ክልሎች ላይ በኢኮኖሚ መገለል ሊገለጥ የሚችል ኋላ መቅረት እያጋጠማቸው ስለመሆኑ የግል ምልከታየን ላካፍላችሁ፡፡

የዛሬው አገራዊ ፌደራላዊ አደረጃጀት ከመዋቀሩ አስቀድሞ በነበረው ሁኔታ ዛሬ በአጋር ፓርቲዎች የሚመሩት አካባቢዎች ነዋሪዎች በዋናነት በማንነት ጭቆና ውስጥ የነበሩ ናቸው፡፡ ለነገሩ በአገር ደረጃ የማንነት ማጎልበት ንፍገት የነበረባት አገር ነበረችና ሰሜነኛው የማንነት መገለጫ አገራዊ መገለጫ ሆኖ ዜጎች የራሳቸውን ጉዳይ በራሳቸው ሳይሆን በገዢዎቻቸው የሚወሰንላቸው ነበሩ፡፡ በአገሪቱ ፖለቲካዊ ጉዳች ላይ የመሳተፍ እና እኩል የመሰለፍ መብት ያልነበረበት የመገለል ዘመን ነበር፡፡ እናም ሰፊ ፖለቲካዊ ጭቆና እና ፖለቲካዊ መገለል የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ብሔር ብሔረሰቦች መለያ ሆኖ በኢትዮጵያዊነት ተስፋ እንዲቆርጡ ያደረገ ዘመን ነበር፡፡

ከኢህአዴግ ወደስልጣን መምጣት ጋር በተያያዘ ከተከሰቱ አወንታዊም አሉታዊም ጉዳዮች መካከል ደግሞ ይህ ፖለቲካዊ ጭቆና  እና መገለል በህዝቦች  ማንነት ላይ የሚያስከትለው ጭቆና እንዲቀር ማድረጉ ትልቁ አወንታዊ ድል ነው፡፡ ህዝቦች በአካባቢያቸው ጉዳይ ባለቤት ሆነው ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ ይገኛሉ፡፡ ይህ ራስን በራስ የማስተዳደር ፖለቲካዊ ሁኔታ ግን በራሱ ፍቱን የኋላቀርነት መድሃኒት አልሆነም፡፡ በአዲስ የተደራጁት ክልሎች በሚሰበስቧት እጅግ አነስተኛ የግብር ገንዘብ እና የፌደራል መንግስት የድጎማ በጀት የክልላቸውን ሁኔታ የመለወጥ ኃላፊነት ቢወስዱም ዛሬም ከ25 ዓመት በኋላ ኋላቀር እና ድጋፍ የሚሹ ከሚለው መጠሪያ ሊላቀቁ አልቻሉም ብቻ ሳይሆን ለወሬ የሚበቃ መሻሻል ያልታየባቸው ናቸው፡፡ ለዚህ በርካታ ምክንያቶች ሊነሱ ይችላሉ፡፡

በአንድ በኩል ዛሬ ክልላዊ መንግስት ሆነው በተዋቀሩት የአጋር ክልሎች የትምህርት እድል ያልነበረበት ፤ እጅግ አነስተኛ የከተማ መስፋፋት፤ ተበታትኖ የሚኖር የህዝብ አሰፋፈር፤ የፀጥታ ሁኔታ እና ተያያዥ ምክንያቶች ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ ከዚህም በላይ ዛሬ ራስህን በራስህ አስተዳድር ሲባሉ ህዝብንም ሆነ በጀትን የማስተዳደር ልምድና ባህል የሌላቸው መሆኑ በ25 ዓመታትም ትርጉም ያለው ለውጥ ለማምጣት አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል፡፡ እነዚህን መሰል ሁኔታዎች ታሳቢ በማድረግ ይመስላል በአገሪቱ ህገመንግስት አንቀፅ 89 በኢኮኖሚ ነክ ዓላማዎቹ በእድገት ወደኋላ ለቀሩ ክልሎች ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባ በሚከተለው መንገድ አስቀምጦታል፡፡

የኢፌድሪ  ህገ መንግስት  አንቀፅ 89 ንዑስ አንቀፅ 4 – }  በእድገት ወደ ኋላ የቀሩ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ህዝቦች   መንግስት ልዩ ድጋፍ ያደርጋል ~

ሆኖም በህገ መንግስት ደረጃ እንዲህ የሰፈረውን የፌደራል መንግስት ኃላፊነት በመተግበር ረገድ  ብዙም የተሰራበት ሁኔታ እንደሌለ ክልሎቹ በኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ዘርፎች ያላቸው ፈቀቅ ያላለ ገፅታ ያሳያል፡፡  ህገመንግስታዊ ግዴታውን ለመወጣት በሚል የፌደራል ልዩ ድጋፍ ቦርድ ቢቋቋምም በዋናነት በአቅም ግንባታ ስራ ላይ የታጠረ የሚመስል ተሳትፎ የሚያደርግ በመሆኑ የክልሎቹን ሁኔታ ከአገራዊ እድገት ተመጣጣኝነት አኳያ የሚገመግም የማስፈፀም ድጋፍ አድርጓል ለማለት አያስደፍርም፡፡ ያ ቢሆን ኖሮ ዛሬ በታዳጊ አገር ፍፁም ኋላ የቀሩ ክልሎች ባልኖሩ ነበር፡፡ የማስፈፀምአቅም ግንባታው ውጤታማ ቢሆን ኖሮ በአጋር ክልሎችና በኢህአዴግ ክልሎች መካከል ያን ያህል ልዩነት ባልታየ ነበር፡፡

ክልሎቹ ከሩብ ክፍለዘመን በጀታቸው ውስጥ ለካፒታል በጀት ይዘውት የነበረው በጀት ምን ያህል ነው፤ በዚህስ ምን ሰሩበት? የሚለው ጥያቄ ሲነሳ አጥጋቢ መልስ የሚገኝበት አይደለም፡፡  የየክልሎቹ አመራሮች ላለባቸው የበጀት አስተዳደር  ክህሎት  ማነስ ታሪካዊ እና ነባራዊ ሁኔታዎች በምክንያትነት ሊጠቀሱ ቢችሉም በአገር ደረጃ ተመጣጣኝ  እድገት  አለመኖር  ነገ  የሚያመጣውን  ችግር  ታሳቢ ያደረገ እውነተኛ ድጋፍና ክትትል ማድረግ በተገባ ነበር፡፡ በተለይ በኢህአዴግ ከሚመሩት ክልሎች ጋር ሲነፃፀሩ ክልሎቹ በአሳዛኝ ደረጃ ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡  ይህ ነው የክልሎቹ  ነገር  ከፖለቲካዊ ጭቆና ወደ ኢኮኖሚያዊ መገለል ስለማምራቱ እንድንጠይቅ የሚያደርገን፡፡

አገራዊ  የኢኮኖሚ ተዋንያን  በክልሎች

በኢትዮጵያ ሁኔታ በዋናነት  የሚጠቀሱ  የኢኮኖሚ ተዋንያን አሉ፡፡ የመንግስት የልማት ድርጅቶች፤ የአገር ውስጥ እና የውጭ የግል ባለሃብቱ እና የኢንዶውመንት ድርጅቶች ሶስቱ ዋነኛ የኢኮኖሚያዊ ልማት ቀጥተኛ ተሳታፊዎች ናቸው፡፡ የፌደራልም ሆነ የክልል መንግስታት ደግሞ በሚይዙት የካፒታል በጀት አማካኝነት መሰረታዊ የመሰረተ ልማት ግንባታን በማከናወን እና የህጋዊ አስተዳደር ስራን በመወጣት የሚጠቀስ ሁሉንም ተዋንያን የሚመራ የጋራ ጥላቸው ነው፡፡  

መሰረተ ልማትን  በፍትሃዊነት የማዳረስ ኃላፊነት ያለበት መንግስትም ቢሆን የአካባቢን የኢኮኖሚ አቅም፤ የህዝብ ብዛትና አሰፋፈር ፤ ወዘተ….መለኪያዎች በመጠቀም እንደሚሰራ ይገልፃል፡፡ በዚህ ረገድ በክልሎች መካከል ምን ያህል ፍትሃዊነት አለ የሚለው ራሱን የቻለ ጥናትና ዝርዝር ምልከታ የሚፈልግ መሆኑ እንዳለ ሆኖ በኢህአዴግ ክልሎች መካከል እንኳ ልዩነቶች መኖራቸው ግልፅ ነው፡፡ የአማራ ክልል ህዝቦችን እንኳ እርስ በርስ (ለምሳሌ፡ ሰሜን ሸዋ እና ጎጃም፤ ሰሜን ሸዋ እና ጎንደር ) ማገናኘት ያልቻለው የመንገድ ልማት ግልፅ ማሳያ ነው፡፡  ሃያ አምስት አመት ሙሉ ምክንያት በሚደረደርላቸው የአጋር ክልሎችማ ይህን መሰሉ የመሰረተ ልማት ፍትሃዊ ስርጭት በእጅጉ አነስተኛ ነው፡፡ ዛሬም ድረስ በአንድና ሁለት አቋራጭ የአስፋልት መንገዶች ብቻ ያሉ ክልሎች ናቸው፡፡

የነዋሪዎች አሰፋፈር ለመሰረተ ልማት ተደራሽነት ያለው ተፅዕኖ እየታወቀ እንኳ በመንደር  አሰባስቦ መሰረተ ልማትን እና ማህበራዊ አገልግሎትን የማዳረስ አስፈላጊነት ከሃያ ዓመት በኋላ በዕትእ1 የታሰበ ነው፡፡ ምናልባት ከዕትእ1 ቀደም ብሎ በነበሩ ዓመታት (ለነገሩ ዛሬም ድረስ) በነዚህ አካባቢዎች ለምን የመሰረተ ልማት ተደራሽነት የለም? ቢባል የህዝቡ አሰፋፈር  በችግርነት መነሳቱ  አይቀርም ነበር፡፡ በጥቅሉ ሲታይ በመሰረተ ልማት ተደራሽነት ረገድ ሲታይ በብዛትም ሆነ በጥራት በኢህአዴግ እና በአጋር ክልሎች መካከል ሰፊ ልዩነቶች አሉ፡፡

በአገሪቱ ከሚጠቀሱ የኢኮኖሚ ተዋንያን መካከል የሆኑት የመንግስት የልማት ድርጅቶች ተሳትፎም ቢሆን በብዛት በኢህአዴግ ክልሎች የሚገኙ ናቸው፡፡ የትኞቹ ኮርፖሬሽኖች በየትኛው ክልል ምንእየሰሩ ነው የሚለውን መፈተሸ ይቻላል፡፡ ቀላል የማይባሉ የአገሪቱ ተቋማት እና ስራዎች ታሳቢ አድርገው የሚሰሩት እንደ አገር ነው ቢባል እንኳ በአጋር ክልሎች ያላቸው ተሳትፎ አነስተኛ ነው፡፡ ዛሬ በአገሪቱ በብዛት የሚገነቡት 13 የኢንደስትሪ ፓርኮች እና 17 የተቀናጀ የአግሮ-ኢንደስትሪ ፓርኮች ልማት ፕሮግራሞች ስርጭት ማሳያ ነው፡፡ የትኛውም ዓይነት ምክንያት ቢደረደር የሚታየው ግን እነዚህ የአጋር ክልሎች ንቁ የኢኮኖሚ መዳረሻ አለመሆናቸው ነው፡፡ ምናልባት የተሸከሟቸውን ስደተኞች ታሳቢ በማድረግ በጋምቤላ እና ኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች  የስራ እድል ፈጣሪ የተባሉ የኢንደስትሪ ዞኖች ለመገንባት ታስቦ እንደሁም ገና የምናየው ነው፡፡

በነገራችን ላይ በቤኒሻንጉል እየተገነባ ከሚገኘው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ምን እየተጠቀመ ነው? ወደፊትስ በምን መልኩ ተጠቃሚ ሊሆን ይችላል? የሚለውን ማጤን ተገቢ ነው፡፡ እርግጥ ነው ግድቡን ተከትሎ ብዙ ሰው ክልሉን መጎብኘት ጀምሯልና ለአሶሳ መነቃቃት ያግዛል፡፡ ሆኖም ክልሉ አሁን ባለበት ደረጃ ከሚመነጨው 6400 ሜዋ ኃይል 50 ሜጋ ዋት እንኳ ለመጠቀም የሚያስችል ሁኔታ እንደሌለ መረዳት ይቻላል፡፡ ለየትኛው ክልላዊ ከተሜነት እና ለየትኛው ኢንዱስትሪ? በግድቡ ግንባታ ሂደት እንኳ የስራ ባህላቸው አነስተኛ ነው በሚል እዚህ ግባ የማይባል የአካባቢ ተወላጅ ተሳታፊ ነው፡፡ የቁጥቋጦ ምንጠራ እንኳ ከሚወጣበት ከፍተኛ ገንዘብ አኳያ የአካባቢ ወጣት ከማደራጀት ይልቅ ጡረታ ለተሸኙ ወታደሮች መሰጠቱ በአትራፊ አትራፊ በቂ ጥቅም እንዳያገኙ አድርጓል የሚል ትዝብት ያላቸው አሉ፡፡ እናም የአካባቢው ወጣቶች ትልቁ ተስፋ ወደፊት በሚፈጠር ሐይቅ በአሳ ማስገር ተሰማርቶ መኖር መሆኑን ያነሳሉ፡፡ በአፋር የተሰራው ተንዳሆ ስኳር ልማት በስንት ምዝበራ እንዳለፈ እና ዛሬም ድረስ የሚያነክስ ፕሮጀክት እንደሆነ አገር የሚያውቀው ነው፡፡

የግል ባለሀብትን በተመለከተ የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ ኢንቨስተሮች ከአራቱ በኢህአዴግ ከሚመሩ ክልሎችና የፌደራል ከተሞች ከሆኑት አዲስአበባ እና ድሬዳዋ  ውጭ በታዳጊዎቹ ለወሬ የሚበቃ አይደለም፡፡ በትንሹም ቢሆን ከኢትዮጵያ ሶማሌ በስተቀር ሀረሪም፤ ቤኒሻንጉልም፤ ጋምቤላም፤ አፋርም ከማኑፋክቸሪንግ ልማት ተጣልተው አንዳንዶቹ  ደርግ ጥሏቸው እንደሄደ ናቸው፡፡ በዚህ ዘርፍ የነዚህን ክልሎች ሁኔታ ከአራቱ ኢህአዴግ መራሽ ክልሎች ጋር ማነፃፀር የቱን ያህል የኢኮኖሚ መገለል እንዳለ ማሳያ ነው፡፡ ከ25 ዓመት በኋላ አንድም ፋብሪካ የሌላቸው ክልሎች ይዞ ኢንደስትሪ የሚመራው አገር ማሰብ ቢቻልም እንኳ ማዕድን እና እርሻን የመሳሰሉ ማካካሻ ኢኮኖሚያዊ አቅሞች ወደጥቅም እንዲለወጡ አለማድረግ ለነዚህ ክልሎች የኢኮኖሚ መገለል ማሳያ ነው፡፡

ብዙሃኑ የአጋር ክልሎች ለእርሻ ልማት የተመቹ ቢሆኑም የአካባቢ አልሚዎች ሳይሆን ከውጭና ከሌሎች ክልሎች በመጡ  አልሚዎች መጠቀሚያ መሆናቸው እየተተቸ ይገኛል፡፡ የተረፈው ነገር ʿቢለሙ እንኳን ኢትዮጵያን አፍሪካን ይመግባሉʾ  የሚባል ንግግር ነው፡፡ ደርግ የአቦቦ እርሻ ልማትን፤  የአልዌሮ ግድብን፤ የጎዴ መስኖ ግድብን፤ የላይኛው እና ታችኛው አዋሽ እርሻ ልማቶች ላይ የሰራውን የሚስተካከል ልማት እንኳ   በሃያ አምስት አመት መፍጠር አልተቻለም፡፡

እንኳንስ ሌሎች የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ራሱ ተወላጁ እንኳ ለስራ አይመርጣትም የሚል  ትችት በሚቀርብባት ትግራይ የውጭ ኢንቨስተር ሄዶ ማልማት ሲጀምር በነዚህ አጋር ክልሎች ያውም ድንቅ የተፈጥሮ ፀጋን ተሸክመው ባሉበት እየለሙ አለመሆናቸው የኢኮኖሚ መገለል ማረጋገጫ ነው፡፡

በፌደራል መንግስትም ሆነ ዛሬ ዛሬ የግል መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሳይቀሩ አንድ አገራዊ ስራ ሲታሰብ አራቱን የኢህአዴግ ክልሎች እንጂ ሌሎቹን ታሳቢ የሚያደርግ አይደለም፡፡ ሃዋሳ፤ መቀሌ፤ አዳማ፤ ባህርዳር ተብሎ እንጂ ጂግጅጋ፤ አሶሳ፤ ጋምቤላ፤ ሰመራ  ተብሎ የሚጀምር አገራዊ ጉዳይ የለም፡፡ ምክንያቱም ተፈርጀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ከተማ በምትባለው አዲስአበባ ከሐረሪዎች በስተቀር በአዲስአባባ አሉ የሚባሉ የአፋር ወይም የኢትዮጵያ ሶማሌ ባለሃብቶች የትኞቹ ናቸው፡፡ የጋማቤላ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ህዝቦች ያፈሯቸው አዲስአበባ ውስጥ ያሉ ንብረቶች ምን ምን ናቸው? በኮንስትራክሽን፤ አስመጪና ላኪ ትሬዲንግ፤ በሆቴል እና ቱሪዝም የሚታወቁ የአጋር ክልል ባለሃብቶች እነማን ናቸው፡፡ ሃብት አዲስአበባ ከሌለ ሃብት አይደለም ማለት አይደለም፡፡ አሶሳም ሆነ ጋምቤላ እና ሌሎችም ዘንድ ቢኬድ ያንን ማየት አለመቻሉ አሳሳቢ ስለመሰለኝ ነው፡፡በጠቅላላው የግሉ ዘርፍ ኢንቨስትመንት በነዚህ የአጋር ፓርቲ ክልሎች ሲታይ ፍፁም አሳዛኝ ነው፡፡

የኢንዶውመንት ልማትን በተመለከተ ከዚህ ቀደም በዚሁ ገፅ የገለፅኩት ስለሆነ እሱን ማየት የሚሰጠው ስዕል ይኖራል፡፡ በክልሎች መካከል ተመጣጣኝ እድገት እንዲኖር የሚሰሩ ገዢ ግንባር እና አጋር ፓርቲዎች  የማመጣጠኛ መንገዶችን ሲያስቡ የሚያለያዩ ጉዳዮችን መመልከት ይገባቸዋል፡፡ በአራቱ ኢህአዴግ በሚያስተዳድራቸው ክልሎች ያሉ ብዙዎቹ ኢንዶውመንቶች አመታዊ ትርፍ ከአንዳንዶቹ የአጋር ፓርቲ ክልሎች የካፒታል በጀት የሚስተካከል ነው፡፡  እንደ ሱር ያሉ የኢንዶውመንት ድርጅቶች የፕሮጀክት በጀት ከነዚሁ አንዳንድ ክልሎች በጀት የተሻለም ነው፡፡ የኢንዶውመንት ልማት የልዩነት ምንጭ አይደለም ማለት በየክልሉ የሚካሔድ ኢንቨስትመንት የልዩነት ምንጭ አይደለም እንደማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ስህተት ነው፡፡ ከኢንቨስትመንት ውጭ የልዩነት ምንጭ ምን ሊሆን ይችላል፡፡ ዛሬ በኪራይ ሰብሳቢነት ተለውሶ እያለ ምክንያት በመደርደር ኋላ ቀርነትን ቅቡል ለማድረግ የሚመኘው የአንዳንድ የአጋር ክልልአመራር፤ ነገ እኛ ለምን ኋላ ቀረን ሌሎች ክልሎች እንዴት ከእኛ ተሻሉ  የሚል ጠያቂ ትውልድ የመጣለት እነሱ ኢንዶውመንት ስላላቸው ነው እኛ ያን የምናደርግበት አቅም አልነበረንም የሚል መልስ መስጠቱ አይቀርም፡፡ ዛሬ ላሉት ችግሮች ያለፉት ስርዓቶች ምክንያት መሆናቸው ተገቢ ትችት እንደሆነው ለነገው ኋላቀርነት ኢህአዴግ ተጠያቂ መደረጉ አይቀርም፡፡

ኢህአዴግ በበኩሉ በአስተዳደራዊ መመሪያ መድብሉ ስለ አጋር ድርጅቶች ባስቀመጠው መመሪያ ላይ እንዳስቀመጠው  }ለሰላም፣ ለልማትና ለዴሞክራሲ በሚደረገው እንቅስቃሴ ከኢህአዴግ ጋር ተባብሮ ለመስራት ዝግጁ የሆነ፤ በአካባቢው ምልአተ ህዝቡን በማንቀሳቀስ ከድህነትና ኋላቀርነት ለመላቀቅ በሚደረገው ትግል የመሪነት ሚና የሚጫወት፤ ጥገኛ አስተሳሰብና ድርጊቶችን በመታገልና ውስጠ ድርጅት አሰራሩን ዴሞክራሲያዊ በማድረግ በኩል ጥረት በማድረግ ላይ የሚገኝ፤ ለአብዮታዊ ዴሞክራሲ በጎ አመለካከት ያለው መሆን~  እስከቻለ ማንኛውም ብሔራዊ ድርጅት ከኢህአዴግ ጋር በአጋርነት መስራት ይችላል ይላል፡፡ ከዚህም በላይ }ኢህአዴግ ከአጋር ድርጅቶች ጋር የጋራ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ ይሰራል፤ የጋራ አመራር ይሰጣል፤ አስፈላጊ የሆኑ የመደጋገፍ ተግባራትን ያከናውናል፡፡~ ይላል፤ }ከአጋር ድርጅቶች ጋር የሚኖረው ግንኙነት ዝርዝር አፈፃፀም ምክርቤቱ በሚያወጣው መመሪያ~  እንደሚወሰን በመግለፅ፡፡

ሆኖም ከላይ  የቀረበው ዓይነት የኢኮኖሚ ልዩነት በሚታይበት ሁኔታ ኢህአዴግም፡ አጋሮቼ ካላቸው ፓርቲዎች  ʿበአካባቢው ምልአተ ህዝቡን በማንቀሳቀስ ከድህነትና ኋላቀርነት ለመላቀቅ በሚደረገው ትግል የመሪነት ሚና የሚጫወትʾ  አጋር ፓርቲ ሲጠፋ ምን እርምጃ ወሰደ የሚለው ቁልፍ ጥያቄ ነው፡፡ }ኢህአዴግ ከአጋር ድርጅቶች ጋር የጋራ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ ይሰራል፤ የጋራ አመራር ይሰጣል፤ አስፈላጊ የሆኑ የመደጋገፍ ተግባራትን ያከናውናል፡፡~  በሚልበት  እና  ክልሎቹ በዚህ ደረጃ የሚገለፅ ልዩነት በሚያሳዩበት  ሁኔታ የሰጠው የጋራ አመራር ምንድን ነው? እነዚህ ን የመሳሰሉ ጉዳዮችስ ለመደጋገፍ የማይመጥኑ ናቸው?

እናም እንደ አገር በክልሎች መካከል ፍትሓዊ እና ተመጣጣኝ እድገት እንዲመጣ ሲታሰብ፤ በህዝቦች እኩል ተጠቃሚነት የሚገነባ አንድ የጋራ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ስለመገንባት ሲታሰብ አንዱን ፊት ሌላውን ኋላ የሚያደርጉ ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎዎችን በማስተካከል ነው፡፡ ሙሉ ለሙሉ በሁሉም ዜጎች እና በሁሉም ክልሎች መካከል እኩል ኢኮኖሚያዊ አቅም እና ተጠቃሚነት ይኑር ማለት አይቻልም፡፡ ለማድርግ ቢታሰብም የማይቻል ነው፡፡ ሆኖም በሆነ መመሪያ እና ደንብ ሳይሆን በህገመንግስት ደረጃ የተቀመጠውን ለታዳጊ ክልሎች ድጋፍ የማድረግ ግዴታ ከልብ መስራት ያስፈልጋል፡፡ የድጋፉ ዓይነትና ስፋት በምን ደረጃ ሊሰራ እንደሚገባ ማስቀመጥ ያስፈልጋል፡፡ በፓርቲ ደረጃ በአጋርነት ለመስራት ሲወሰን እንዲሰሩ የተፈለጉት አጀንዳዎች የክልሎቹን እኩል ተጠቃሚነትና እድገት የሚያጎለብቱ ምክረ ሃሳቦች የሚስተናገዱበት እንዲሆን ከሁሉም የፓርቲ እና የመንግስት አመራሮች ብዙ ርቀት መጓዝን ይጠይቃል፡፡

2 Comments
 1. yohannes says

  ብአዴን ኣብ ልዕሊ ህወሓት ጎል ምእታው ቀፂልዎ ኣሎ!!
  ***************-******************************
  እዚ ፀወታ ኣብ እስታድዮም 4 ኪሎ እዩ ተካይዱ!!
  ብኣዴን፡ ህወሓት ትመርሖ ትግራይ ብፀቢብነት ንሓምዮ ኢና፡፡
  ህወሓት፡ ኣረ ፀቢብነት ዝባሃል የብልናን፡፡
  ብኣዴን፡ ኣይ ብስሩ ውን ናይ ምግንፃል ስዉር ዕላማ ኣለኩም:: ክሳብ ትለምዑ ኢኩም ትፅበዩ ዘለኩም፡፡
  ህወሓት፡ ዋይ! ታይ ወሪዱኩም? ንሕና ብኢትዮጵያ ኢና ንኣምን፡፡
  ብአዴን፡ እስኪ ብኢትዮጵያውነት ጥራሕ ትኣምኑ እንተኮይንኩም፡ ናይ ምግንፃል ዕላማ እንተድኣ ዘይብልኩም፡ ትግራይ ካተን 105 ግድባት ነፃ ትኩን? እስኪ? እተን ፕሮጀክታት እስኪ ቀስ ኣብሉወን፡፡
  ህወሓት፡ ዋይይ! እሺ፡ ንሕና ህዝቢ ትግራይ ምስ ካልኦት ህዝብታት ማዕረ ኢና ንሪኦ፡፡ ጥራሕ ኢ/ያ ትልማዕ ያው እዩ፡፡
  .
  ዓመሚቅ ተሃድሶ ኣኬባ ድማ መፀ፡
  ብኣዴን፡ ህወሓት ኣፋ እያ እንበር ፀቢብነት ኣለዋ ሕጂ ውን፡
  ህወሓት፡ ንሕና ናይ ምግንፃል ዕላማ የብልናን፡ ኢ/ያ እያ ዓለምና፡ እኮ ኢልና፡፡
  ብአዴን፡ መውፅኢ ኢኩም ትፈጥሩ ዘለኩም፡ እስኪ እቲ ባቡር መስመር ናብ መተማ ሱዳን ይዛወር ድኣ?
  ህወሓት፡ ዋይ! እሺ፡ ንሕና ኢትዮጵያ ለሚዓ ምርኣይ እዩ፡፡

 2. maru says

  ካቻምና አቶ ሐይለማርያም ደሳለኝ “የትግራይ ሕዝብ ትርፍ መስዋዕት ይከፍላል እንጂ ትርፍ ጥቅም አይፈልግም” አሉ፤
  የትግራይ ሕዝብ ሌላው ሕዝብ እንደሚያደርገው “ይህ ጎደለን፣ ይህ ይሰራልን” ብሎ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ እንዳያነሳ አፉን ለመዝጋት ወይም “ሼም ማስያዣ” መሆኑ ነው፤ በነገራችን ላይ ከዚያ አንድ ዐመት ቀደም ብለውም “100 % የትግራይ ገበሬ ሞዴል ሆኗል” ብለው ነበር፡፡

  ቀጥለው “ለሸዐብያ የትግራይ ሚሊሻ ይበቃዋልና No Peace No War የኢህአዴግ ፖሊሲ ይቀጥላል” አሉ-ከወራት በፊት- የትግራይ ገበሬ እርሻውን ትቶ፣ እራሱን መቀመቅ እየከተተ፣ እየተራበና እየተጠማ ሸዐብያን እየጠበቀ ሊኖር ማለታቸው ነው- ሊያውም ያለ ምንም ደሞዝ፤ ያለ ምንም ካሳ፡፡ እንዴት ነው ነገሩ?

  አሁን ደግሞ መጀመርያ ላይ ሑመራ ድረስ እንዲዘልቅ ተደርጎ ታቅዶ፤ ኃላ ላይ ሽረ ላይ እንዲያበቃ የተወሰነበት የወልዲያ- መቐለ- ሽረ-ሑመራ የባቡር መስመር ሕዝባችን መስመሩ በቀደመው እቅዱ መሰረት ወደ ሑመራ እንዲዘልቅ እየጠየቀ ባለበት ሰዐት አቶ ሐይለማርያም “የለም፤ እንደውም የመስመሩ መጨረሻ መቐለ ላይ እንዲሆን (ከመቐለ እንዲጎመድ) ወስነናል፤ ምክንያቱም ከመቐለ ወዲያ የባቡር መስመር መገንባት ውድ ነው፤ አዋጭ አይደለም” አሉ፡፡

  ነገሩ ማለቅያ ያለውም አይመስል፤

  የትግራይ ኣባቶች እንዲህ ዐይነቱን ብልጣብልጥነት ላይ ሲተርቱ “ዓሻ መሲልካ ድራሮም ወድአሎም” ይላሉ፤
  “ሞኝ መስለህ እራታቸውን ጨርስባቸው” እንደማለት ነው፤ “ቆዳው ሞኝ” ከሚለው የአማርኛ አባባል ጋርም በተወሰነ ደረጃ ይቀራረባል፡፡

  በዚህ የአቶ ሀይለማርያም አካሔድ ያልበገነ ትግራይ ወጣት የለም፡፡ ዳሩ ግን “ቀድሞ ነበር እንጂ አልሞ መደቆስ፤ አሁን አይደለም ድስት ጥዶ ማልቀስ” ነው- ህ.ወ.ሐ.ት/ኢህአዴግ በትግራይ ሕዝብ ላይ እንዲህ እንዲፈነጭ የፈቀደለትስ ማን ሆነና- የወጣቱ ዝምታ አይደለምን?

  አሁን የአቶ ሀይለማርያምና የህ.ወ.ሐ.ት አካሄድ ግልፅ ነው፤ የትግራይን ሕዝብ እንደ ቂል ቆጥሮ “ጀግኖች ናችሁ፤ ስርዐቱ የናንተ ነው፤ ብዙ መስዋእት መክፈል እንጂ እንዲህና እንዲያ ይሰራልኝ ማለት የናንተ አይደለም፤ ጀግኖች ድንበር ጠባቂዎች ናችሁና ሸዐብያን ብቻችሁ ጠብቁት” ወ.ዘ.ተ እያሉ ለ’ማጃጃል’ መሞከር፤ ከዚያም ህ.ወ.ሓ.ትን ከተጠያቂነት ተከላክሎ የትግራይን ሕዝብ ከጎን መውጋት፤ ከሰላምም ከልማትም ከሁሉም እንዳይሆን በሁሉም ረገድ መበደል…..
  እንዴት ያለ ነገር ነው?

Leave A Reply

Your email address will not be published.