ሀርቨስት ማይኒንግ ለተባለ የኢትዮ ካናዳ ኩባንያ የወርቅና የብር ማዕድን ማምረት ፈቃድ ተሰጠ

(ኤፍ.ቢ.ሲ)- የማዕድን፣ ነዳጅና ተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር ሀርቨስት ማይኒንግ ለተባለ የኢትዮ ካናዳ ኩባንያ የከፍተኛ ደረጃ የወርቅና የብር ማዕድን ማምረት ፈቃድ ሰጠ።

የማዕድን፣ ነዳጅና ተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስትር አቶ ሞቱማ መቃሳ እና የኩባንያው ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ውብሸት ካሳዬ የወርቅና የብር ማዕድን ማምረት ፈቃድ ስምምነቱን በዛሬው እለት ተፈራርመዋል።

ስምምነቱ ለ6 ዓመታት የሚቆይ ሲሆን፥ ወደፊት በኩባንያው ጥያቄ መሰረት መሠረት በእያንዳንዱ የፈቃድ ዕድሳት ጊዜ ከ10 ዓመታት ላልበለጠ ጊዜ ሊታደስ እንደሚችል ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

በስምምነቱ መሰረትም ኩባንያው በትግራይ ክልል ምዕራብ ትግራይ ዞን፣ ሽሬ እንደስላሴ ላዕላይ አዲያቦ ወረዳ ልዩ ስሙ ጥራቅምቲ በ2 ነጥብ 7682 ካሬ ኪሎ ሜትር ቦታ ላይ ማዕድን ማምረት ስራውን የሚያከናውን ይሆናል።

ኩባንያው የማዕድን ማምረት ስራውን ከ65 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር በላይ ወጪ የሚያከናውን ሲሆን፥ ወደ ሥራ ሲገባ ለ120 ኢትዮጵያዊያን የሥራ ዕድል ይፈጥራል ተብሏል።

በሚቀጥሉት 4 ዓመታትም 2 ሺህ 80 ኪሎ ግራም ወርቅ እና 8 ሺህ 968 ኪሎ ግራም ብር ያመርታል ተብሎ ይጠበቃል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.