ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዝብ ጥንካሬ መሠረቱ የሆነው አንድነቱ ይቅደም

(ጌታቸው ዶአ) – የአንድነት ፅንሰ-ሃሳብ በብሔር፣ በቋንቋ ወይም በባህል ተመሳሳይነት ላይ የተመሰረተ አይደለም። ከዚያ ይልቅ፣ ፖለቲካዊ አንድነት በሰብዓዊነት እሳቤ ላይ የተመሰረተ ነው። እንደ ሰብዓዊ ፍጡር ሁሉም ሰው እኩል መብትና ነፃነት አለው። በመሆኑም፣ ለእኔ የሚገባኝ መብትና ነፃነት ለሁሉም ሰው ይገባል በሚል እሳቤ ላይ የተመሰረተ ነው። በዚህ መሰረት፣ “አንድነት” ሲባል ሁላችንም እኩል መብት፣ ነፃነትና ተጠቃሚነት ያስፈልጋል ማለት ነው። በአጠቃላይ በአንድነት እና በእኩልነት መርህ ላይ የተመሰረተ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ የብዙሃን መብትና ነፃነት የተከበረበት ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመዘርጋት ያስችላል።

የኢትዮጵያ ህዝብ በአንድነቱና በጥንካሬው በዓለም ማህበረሰብ ዘንድ የሚታወቅ ኩሩና ጀግና ህዝብ ነው፡፡ ይህ ህዝብ ዓለም የሚያውቀውን የጥንካሬ ምንጭ ማለትም አንድነቱንና አብሮነቱን ከመቼውም ጊዜ በላይ አጥብቆና አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ ምክንያቱም ከማንም ሌላ አካል በላይ የአንድነቱንና የጥንካሬውን ምስጢር በተግባር የሚያውቀው ይኸው የተከበረው ህዝብ ነውና፡፡ በደስታም ሆነ በሃዘኑ እርስ በርሱ የሚካፈልና የሚረዳዳ አስደናቂ ህዝብ ነው፡፡ ያለው ለሌለው አካፍሎና ቆርሶ የሚሰጥና አብሮ የሚበላ ቸር ህዝብ ነው፡፡ የሐይማኖት ልዩነትን ድምቀቱ አድርጎ የሚያምን አንዱ የሌላውን መብት አክብሮ ለዘመናት የኖረና ለወደፊትም እንደዚሁ የሚኖር የመቻቻልና የአብሮነት ተምሳሌት ህዝብ ነው፡፡

የትኛውም ሀይማኖት ከሌላው ሀይማኖት አይበልጥም፤ አያንስም ማንኛውም ዜጋ ያመነበትን ሀይማኖት ያለማንም ተፅእኖና ጫና የመቀበልና የመከተል ህገ-መንግስታዊ መብት አለው፡፡

ኢትዮጵያ ሀገራችን ከተሰጣት ፀጋዎች መካከል አንዱና ዋነኛው የብሔርና የቋንቋ ብዝኃነት ሲሆን፣ እነዚህም ብሔሮች ምንም ብዙ ቢሆኑም የጥንካሬ ምንጭነታቸው የሚገለፀው በአንድነት ሲቆሙና መኖር ሲችሉ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ብዙ ልምድና ተሞክሮ ያለው የኢትዮጵያ ህዝብ እንደዛሬው ሁሉ ነገም ቢሆን በተለመደው ሁኔታ አንድነቱን አስጠብቆ ይቀጥላል፡፡ አንድ ሰው ብዙ የአካል ክፍሎች ቢኖሩትም ሙሉ ሰው የሚሆነው እነዚህ የአካል ክፍሎች በአንድ ላይ ሲደመሩ ነው፤ ጤናማ ሆኖ መተንፈስና መቆም የሚችለውም ሁሉም የአካል ክፍሎች ጤናማ ሲሆኑ ብቻ ነው፡፡ ከእነዚህ የአካል ክፍሎች አንዱን ቢያጣ እንኳ አካል ጉዳተኛ ስለሚሆን እንደፈለገ ተንቀሳቅሶ መስራትና ከአደጋ ማምለጥ እንደማይችል ሁሉ ሁሉም ብሔሮችና ብሔረሰቦች አንድ ላይ ካልሆኑ በስተቀር የትኛውንም ተልእኮ ለመወጣት አቅሙም ሆነ ብርታቱ ሊኖራቸው አይችልም፡፡ ለማንኛውም የውጭ ጠላት በቀላሉ ተጋልጠው ለጠላት እጅ እንደሚሰጡ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ከመንጋው የተለየ ምን እንደሚያጋጥመው መገመት ብቻ በቂ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ምርጫ ምን ጊዜም በእኩልነት ላይ የተመሰረተ አንድነት ነው፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ሁሉንም ብርቅዬ ብሔሮች ብሔረሰቦችን ዝቅ ሲልም ዜጎችን አባት ለልጅ የሚያስፈልገውንና የሚጎዳውን ነገር አውቆ እንደሚያደርገው ሁሉ ማገልገል ያስፈልጋል፡፡ አንዳንዴ ልጆች የሚያስፈልጋቸውን ነገሮች አባት ከተዘናጋ አባትን መጠየቅ ሊኖር ይችላል፡፡ ለዚህ ጥያቄ አባት ደግሞ ተገቢውን ምላሽ እንደሚሰጥ ይታመናል፡፡ ምላሽ ሲሰጥም አባት ለልጆቹ አድልዎ የለሌበትና ፍትሐዊ የሆነ ምላሽ እንደሚሰጥ ከመልካም አባት የሚጠበቅ ነው፡፡ ምክንያቱም ሁሉም የእሱ ልጆች ናቸውና፡፡ አባት ለልጆቹ አድሎአዊ የሆነ አገልግሎት የሚሰጥ ከሆነ ለጎረቤት፣ ለአካባቢ ብሎም በአገር ደረጃም ቢሆን ለዜጎች ፍትሐዊነትንና ሰብአዊነትን በሚጠይቁ ጉዳዮች ላይ ይህ አባት ማዳላቱ አይቀርም ማለት ነው፡፡ ስለዚህ መንግስትም እንደጥሩ አባት ለሁሉም የኢትዮጵያ ዜጎች (ብሔሮች) ከአድልዎ የፀዳና በእኩልነት ላይ የተመሠረተ አገልግሎት መስጠት ይኖርበታል፡፡ ምክንያቱም መንግስት ለሁሉም ዜጋ እንደ አባት ስለሚታይ ከተሳትፎ ጀምሮ እስከ ተጠቃሚነት ድረስ የሚታዩ ጉድለቶችን አርሞ ማስተካከል አለበት፡፡ አባት ልጆቹን በእኩልነት ካላገለገለ በልጆችና በአባት መካከል ፍቅርና አንድነት እየራቀ ልዩነት እየሰፋ እንደሚሄድ መገመት አይከብድም፡፡ ልዩነቶች ሲሰፉ አንድነት በዛው ልክ እየራቀ ሂዶ ሂዶ መጨረሻ ላይ ጥንካሬ በድክመት እየተተካ መከፋፈልና አቅም ማጣት መበታተን ይመጣል፡፡ ቤተሰብ ለአገር መሠረት እንደመሆኑ መጠን ከቤተሰብ ጀምሮ በአንድነትና በእኩልነት የሚያምን ዜጋ ለመፍጠር አባት ትልቅ ኃላፊነት አለበት፡፡ ይህንን ለማድረግ የቤቱ መሪ ወይም ዋና አስተዳዳሪ የሆነው አባት ሆደ ሰፊና በሳል ሆኖ ቤቱን ለማቃናትና ለመምራት የአንበሳውን ድርሻ መወጣት መቻል እንዳለበት ምንም ጥርጥር የለውም፡፡

ከፍ ሲል ቤተሰብን እንደምሳሌ አንስተን እንዳየነው ሁሉ አገርን አንድ በማድረግ ጥንካሬን ለማምጣት መሪዎች የሚጫወቱት ሚና ወሳኝ ነው፡፡ አመራር ማለት በሰራተኞች ወይም ዜጎች መካከል የጋራ የሆነ እምነት እንዲዳብርና ራዕይን እውን ለማድረግ የሚያስችል የመምራት ችሎታ ነው፡፡ አመራር ማለት በሌሎች ላይ ተጽዕኖ የማሳደር ችሎታ ነው፡፡ አመራር ግለሰብ በህዝቦች ላይ ተጽዕኖ በማሳደር እንዲከተሉት የማድረግ ሂደት እንደሆነ በተለይም የጋራ ዓላማን ለማሳካት ተምሳሌት ሆኖ ሰዎችን ወይም ቡድኖችን የመምራት ሃላፊነት ነው፡፡ መሪ ትኩረቱ በሰው አስተሳሰብ ላይ አዎንታዊ ተጽዕኖ የሚያሳድር፣ ተከታዮችን የሚያፈራ፤ ራዕይ ያለው፤ ከተለመደው አሰራር ውጪ በአዲስ መንገድ የሚጓዝ፤ ችግር ከመከሰቱ በፊት መውጫ መንገዱን የሚያዘጋጅና የማሳመን ችሎታ ያለው ነው፡፡ ስለዚህ አሁን በአገራችን የተፈጠረውን የመልካም አስተዳደር ችግር በመፍታት የህዝቡን አንድነት ከማረጋገጥ አኳያም የመሪዎች ሚና ተኪ የለውም፡፡ በየትኛውም የአገሪቱ ጫፍ ወይም ክፍል የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት በየደረጃው ካለው መሪ ውጭ ሌላ የሚጠበቅ አካል ሊኖር አይችልም፤ አይጠበቅምም፡፡

በዘመድ አዝማድ፣ በሀይማኖት ተከታይነት፣ በአንድ ቋንቋ ተናጋሪነት፣ በመንደርተኝነት……. ወዘተ የሚፈጸሙ አድሎአዊ ተግባራት ካልተወገዱ በስተቀር አንድነት ይመጣል ብሎ መጠበቅ ከየዋህነትም በላይ ሞኝነት ይሆናል፡፡ በሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ከወጣቶች ሥራ አጥነት ችግሮች ጋር ተዳምሮ ትልቁና ዋነኛው የመልካም አስተዳደር ችግር ይኸ ይመስለኛል፡፡ ይህ ደግሞ መወገድ ያለበት እኩይ ተግባርና ነቀርሳ ነው፡፡ የእህል እንጂ የሰው ዘር አይመረጥም፡፡ ያው የሁሉም ኢትዮጵያዊ የዘር ምንጭ አንድ መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡ እኛን የፈጠረን አላዳላም፤አያዳላም፣እኛ ግን እናዳላለን፡፡ ለምን?? የፈጠረን ቢያዳላ ኖሮ አለቅን ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ ፈጣሪ ፀሐይንና ጨረቃን ሳያደላ ለዓለም ሁሉ እኩል ያፈራርቃቸዋል፡፡ የምንተነፍሰውን አየር እንኳ ቢያዳላን ኖሮ አንኖርም፤አለቅን ማለት ነው አይደል? የሰው ልጅ ግን አድሎአዊ የሆነ ነገር የተማረው ከማን ይሆን?? መልካምነት ከሌለ መልካም አስተዳደር ከየትም ሊመጣ አይችልም፡፡ መልካምነት የሚመጣው ለእኔ የምፈልገውን ለሌላው በማድረግና በማካፈል ነው፤ በእኔ ላይ እንዲሆን የማልፈልገውን በሌላው ላይ አለማድረግ፣ አለመፈጸም፡፡ እያንዳንዱ መሪና ዜጋ መልካም ሆኖ መልካም ሥራ ከሰራ ክፉውን ነገርና ተግባር ፈልጎ ማግኘት በጣም ይከብዳል፡፡

መከፋፈልን የኢትዮጵያ ህዝብ አይፈልግም፡፡ ምክንያቱም ከመከፋፈል የሚገኝ ጥቅም ስለማይኖር፣ አንድነቱን አጠናክሮ ለማስቀጠል ትልቅ እምነት ያለው የአንድነት ተምሳሌት ህዝብ ነው፡፡ አንድነት ኃይል እንደሆነ ህዝቡ በተግባር ያውቃል፡፡ ይህንን በሳል ህዝብ የሚመራው አመራር ከህዝቡ በብዙ ርቀት ቀድሞ ወደፊት መጓዝ ይጠበቅበታል፡፡ ህዝቡ አመራሩን ከቀደመው መምራት በጣም ሊከብድ ይችላል፡፡ አመራር ከአመራር የሚጠበቀውን ሚና በአግባቡ ካልተወጣ አሉ የሚባሉ ችግሮችን ለመፍታት በጣም አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ፈጣሪውን የሚፈራና ለመሪው የሚታዘዝ ድንቅና በሳል ህዝብ በመሆኑ አሁን የተፈጠሩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችንም እንዲፈቱለት በተገቢውና በሰለጠነ መንገድ እየጠየቀ ይገኛል፡፡ ችግሮችንም ጊዜ ሳይሰጠው አንድ በአንድ መፍታት ለአገሪቱ መፃኢ እድልም የሚኖረው ትርጉም ቀላል አይደለም፡፡ እንደ ጥሩ ዳኛ የበሰለ ህዝብን መምራት በራሱ መታደል ነው፡፡ ይህንን እድል መጠቀም ደግሞ ብልህነት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ በጥሩም ይሁን በመጥፎ ጊዜ ከመሪው ጎን በመሆን ችግሮችን በመፍታትም ሆነ ደስታውን በመጋራት የሚታወቅ ህዝብ ነው፡፡ አሁን መፍትሔው ህዝቡ ዘንድ በመውረድ ምን ላድረግልህ? ምን ያስፈልግሃል? በማለት በቅርበት ማነጋገር፣ አዲስና ተግባራዊ የሚሆን ተስፋ መስጠት ያስፈልጋል፡፡

የአፍሪካ ህዝቦች መሰብሰቢያ መዲና የሆነችው ኢትዮጵያ እንዴት ልጆቿን አቅፋ መኖር ያቅታታል? አባቶቻችን የውጭ ወራሪን አሽቀንጥረው የጣሉትና ያሸነፉት እርስ በርስ በመከፋፈል ሳይሆን አንድ በመሆንና የተባበረ ክንድ በማንሳት ብቻ ነው፡፡ ያውም ምንም ዘመናዊ መሣሪያና ቴክኖሎጂ በለሌበት በጦርና በጋሻ የጠላት ወራሪ ኃይል የመከተ ጀግና ህዝብ ነው፡፡ ችግሮችም ካሉ በሰለጠነ መንገድ ፍርጥርጥ አድርጎ ተነጋግሮ መፍታት ይቻላል፤ የማይፈታ ነገር የለም፤ አይኖርምም፡፡ በአመፅና በሁከት ክቡር የሆነው የሰው ህይወት በፍፁም መጥፋት የለበትም፤ ያንተ፣ያንቺና የእኛ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ናቸውኮ!! ሀብትና ንብረትም ቢሆን የኛው ስለሆነ ባለው ላይ መጨመር እንጂ አጥፍተን ከዜሮ መጀመር የለብንም፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ የሚጠቅመውንና የማይጠቅመውን ለይቶ የሚያውቅ እውነተኛ ዳኛ ስለሆነ የየትኛውንም የውስጥም ሆነ የውጭ ኃይል አፍራሽ ቅስቀሳ አይሰማም፤ አይቀበልም፡፡ ስለዚህ እነዚህ አንድነታችንን ለማናጋት ህዝባችንን ከሚያስተምሩበትና ከሚቀሰቅሱበት ተልእኮ ቢቆጠቡ፣ ወጣቶቻችንም ሳያውቁት በዚህ ድርጊት እንዳይገቡ ሁሉም ወላጆች ቤተሰባዊ ምክራቸውን እንዲለግሱና እንዲመልሷቸው ወንድማዊ መልእክቴን በትህትና አስተላልፋለሁ፡፡ ምክንያቱም ከብጥብጥ የሚገኝ ጉዳትና ሞት እንጂ ሌላ ጥቅም የለውምና፡፡ የኢትዮጵያ ጠላቶች ግን መከፋፈሉንና መበታተኑን በጣም ይፈልጉታል፤ ለዚህ ደግሞ አስተዋፅኦም እያደረጉ ነው፡፡ እኛም ከእኛ አልፈን እንደ አህጉር የአፍሪካ ወንድሞቻችንም ጭምር አንድነት ለማረጋገጥ ቆርጠን ተነስተናል!! እናንተስ?

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.