መልካም አስተዳደር ፡ ከቢሮክራሲያዊ ሙስና አንፃር

በአንሙት አብርሃም (ani_abrish@yahoo.com)

በቅድመ ተሃድሶም ሆነ ድህረ ተሃድሶ የኢህአዴግ ትግል ውስጥ በየመድረኩ እና በየጉባኤው ቢታኘክም ፤ ከመሰረታዊ የአገሪቱ ችግሮች ዋነኛው መሆኑ ቢሰበክ ቢወገዝም፤ እንደ ልማቱ ሁሉ “በናዳ ስር ሩጫ” ተመስሎ ከህልውና ጋር ተያይዞ ቢመከርበትም፤ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ላይ አወንታዊ አመለካከቱ የተገነባ የህዝብ አገልጋይ መፍጠር አስቸጋሪ ሆኗል፡፡ ህዝብ ያማርራል፤ መንግስትም የችግሩን መኖር ይቀበላል፤ መፍትሔ ግን የለም፡፡ መፍትሔ ሲባልም በየደረጃው ያለ አመራርን ማንሳት ፡ መጣል ነው፡፡ እርምጃው የማስታገሻ ፤ የአንድ ሰሞን ጉድ ነው፡ ያበቃል፡፡ የችግሮቹ መገለጫ እንጂ የችግሮቹ ስርና ምንጭ ሲወሳ አይታይም፡፡

በመልካም አስተዳደር ችግሮች ዙሪያ ከሚሰጡት ጉልህ ፍረጃዎች ውስጥ የችግሩ ምንጭ ፖለቲካዊ ነው ቢሮክራሲያዊ የሚለው ላይ ያልተተነተነ አስተያየት ይሰነዘራል፡፡ የቢሮክራሲ ስርዓቱን ፀባይ እና አቅጣጫ የሚወስነው ፖለቲካዊ ፖሊሲው ይሁን እንጂ ትክክለኛ የፖሊሲ አቅጣጫ፡ በልኩ የተሰራ፤ ጥራት ባለው የቢሮክራሲ መዋቅር እና ግልፅነት ካልተፈፀመ ከንቱ ነው፡፡

በመሆኑም ትክክለኛ ፖለቲካዊ ፖሊሲ ትክክለኛ የቢሮክራሲ አሰራርን የግድ ይላል፡፡ የተሳሳተ ፖለቲካዊ አካሄድም ፡ በራሱ ልክ የሆነ ቢሮክራሲ ላይ ሊቆም አይችልም፡፡ አብሮ መስተካከል፡ አብሮ መበላሸት ነው፡፡ የአስተዳደር በደል የፖለቲካ ነው የቢሮክራሲ አሰራር የሚለውን ሙግት እንተወውና፡ የቢሮክራሲዊ ሙስና ምንጭ የሆኑት ቢሮክራሲያዊ ችግሮች ለአስተዳደር በደል የሚኖራቸውን ትርጉም እንመልከት፡፡ ቢሮክራሲያዊ ሙስና በቀዳሚነት ኪራይ ሰብሳቢነት በመሆኑ የመልካም አስተዳደር ጉዳይ ህገ ወጥ ኪራይ ፈላጊነትን እና ተሳክቶላቸው የሚሰበስቡትን የመታገል ጉዳይ ነው፡፡

በርካታ ምሁራን የቢሮክራሲዊ ሙስና ምንጭ በማለት የተለያዩ ጉዳዮችን ያነሳሉ፡፡ ከነዚህም መካከል፡-

  1. አቅመ ቢስ ሰራተኞች
  2. የዜጎች ልል ብሔራዊ ስሜት [soft state]
  3. ጎደሎ ባህል
  4. ልጓም አልባ (ደካማ) ህጎች
  5. ስር የሰደደ ድህነት

እነዚህ ችግሮች በአንድ ቢሮክራሲያዊ መዋቅር ውስጥ ዋነኛ የሙስና ምንጭ ይሁኑ እንጂ መገለጫዎቻቸው ግን ብዙ ናቸው፡፡ በሙስና የተበከለ ቢሮክራሲያዊ አገልግሎት ደግሞ የአስተዳደር በደል ማዕድ ነው፡፡ በዝርዝር እንመልከታቸው፡፡

  1. አቅመ ቢስ ሰራተኞች

በቢሮክራሲያዊ መዋቅር ውስጥ ሰራተኞች የሚቀጠሩበት ሂደት አቅምን መሰረት ያደረገ [meritocratic recruitment] ወይንም በጥቅማጥቅም፤ዘመድ አዝማድ እና የተሳሳተ ፖለቲካዊ ፍላጎት [patronage recruitment] የሚፈፀም ይሆናል፡፡ በጥቅም መረብ የሚፈፀመው ቅጥር ለቢሮክራሲው ጥራት መጓደል ዋነኛ ምክንያት ስለሚሆን የሙስና ምንጭ ነው፡፡ በአመራርም ሆነ በተራ ፈፃሚ ሰራተኞች መካከል በጥቅም እና በብቃት የተቀላቀለ የቅጥር ሂደት ሲኖርም [patronage and meritocratic recruitment] ተቋሙ የጎበዝ እና ደካሞች መድረክ ስለሚሆን የመስራት አቅሙና ፍላጎት ባላቸው እና በሌላቸው መካከል ግልፅና ስውር ትግል ይኖራል፡፡ ደካማው ኃይል በሚኖረው የአቃጣሪነት ሚና አሸናፊ የሆነ እንደሁ ጠንካሮችን ተስፋ የሚያስቆርጥ ተቋማዊ አሰራር ይሰፍናል፡፡ (ሁለቱ የሰራተኞች ቅጥር አፈፃፀም መንገዶች በቢሮክራሲ መዋቅር ውስጥ ያላቸው ተፅእኖ ራሱን ችሎ በስፋት ሊታይ የሚችል ነውና ወደፊት ለብቻው ሊታይ ይችላል፡፡)

አገር አቀፍ የልማት እቅዶች በስኬት እንዲፈፀሙ ከፍተኛ የመፈፀም እና የማስፈፀም አቅም ያላቸው ሰራተኞች እና የስራ ኃላፊዎች መኖር የግድ ነው፡፡ የመንግስት አገልግሎት ‘ደንበኛ’ ለሆነው የግሉ ዘርፍ ንቁ ተሳትፎም ፍላጎቶቹን ታሳቢ ያደረገ ቀልጣፋና ተራማጅ ቢሮክራሲያዊ አገልግሎት ይፈልጋል፡፡ ለነዚህ ደግሞ ተቋማዊ አገልግሎቱን የሚመጥን (በትምህርት ዝግጅት፤ ክህሎትና ልምድ፤….) ሙያተኞች ሊኖሩ የግድ ነው፡፡ በዚህ በኩል አቅመ ቢስ ሰራተኞች ከተቀጠሩ ግን ተቋማዊ አገልግሎቱን መስጠት አለመቻል እና ተገልጋይን መበደል ብቻ ሳይሆን የጥፋት ኃይል በመሆን በሙስና ይዘፈቃል፡፡

መስራት አይችልምና በተቀጠረበት መስሪያ ቤት፡ ‘ጉዳይ ገዳይ’ ተብሎ፡ የውስጥ ደላላነት ሚና ይይዛል፡፡ እሱ የመፈፀም አቅም የለውምና ቢሮክራሲያዊ አገልግሎትን ለማሻሻል የሚቀረፅ ይሁን የሚወርድ አሰራርን ሁሉ ይቃወማል፤ ይጠላል፡፡ በባህሪው ለውጥ ጠል ነው፡፡ ማወቅ ይጠላል፡፡ ውጤታማ የአገልግሎት ማሻሻያ ፡አንድም የእሱን አለመቻል ስለሚያጋልጥ ሁለትም የጥቅም መስመሩን ስለሚያጋልጥ ለማደናቀፍ የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም፡፡

በዚያ መስሪያ ቤት የመኖሩ ምክንያት አቅም እና መጣኝነት ሳይሆን ልዩ የግንኙነት መረብ በመሆኑ የጥቅም ተጋሪ እና አጋሪ ነው፡፡ የሚመጣ ለውጥ፡ ቢቻል እንዳይመጣ ከመጣም የእሱን ድርሻ እና ቦታ እንዳይነካ ለማመቻቸት ይተጋል፡፡ በስራ ሁኔታ ውስጥ የሚያገኙት ደንበኞች እና ባልደረቦች ሁሉ አለመቻሉን ሊገልጡበት ይችላሉና መስራትን ሳይሆን የሰራ መምሰልን ይካንበታል፡፡

የስራ ግምገማ ሲባል በስራዎች አፈፃፀም ላይ ሳይሆን ከተቋሙ ስራ ውጭ ባሉ ግላዊ ባህርያት እና ሰው ላይ ብቻ የሚደረግ ግምገማ እንዲሆን ያደራጃል፡፡ እጅ እጅ የሚል፡ የስራ ሽታ የሌለው ፤መስፈርት የሌለው አማራሪ ግምገማ ይሆናል፡፡ ባልተቆጠረ ስራ እና ውጤት፡ በሚፈፀም ግለሰባዊ ወቀጣ፡ ‘ግምገማ አለ’ በተባለ ቁጥር፡ ሰራተኛው ይጠላዋል፡፡ ስራ ስለማይገመገም የሰራ ሳይሆን የሰራ የመሰለ እና ያወራ የሚመሰገንበት መድረክ ይሆናል፡፡ የሚሰራን ቅስም ይሰብራል፡፡ መስክ እንኳን ተልኬ ግምገማን ባመለጥኩት ይላል፡፡

እናም ቀና የስራ መንፈስ ይጠፋል፤ አገልግሎት የለም፡፡ ከደንበኞች በላይ በሚሰራበት ተቋም ላይ ያማርራል፡፡ ደካማ ሰራተኛ እና አመራር መጥፎ ምሳሌ ነው፡፡ ሙስና ይፈፅማል፡፡ አለመቻል እና አለማገልገል ደግሞ የአስተዳደር በደል ነው፡፡

       1.1 የቢሮክራሲዊ መዋቅር ጉድለቶች

ቢሮክራሲ በአንድ ተቋም ውስጥ ያሉ የስራ ኣይነቶችና ሂደቶች አፈፃፀም፤ የስራ ኃላፊነት ዓይነትና አደረጃጀት፤ የኃላፊነት ክፍፍል እና ግንኙነቶችን የሚገልፅ የህጋዊ መመሪዎች አስተዳደራዊ አደረጃጀት ነው፡፡1 የተቆጠረ ስራ፤ ለእያንዳንዷ ስራ አስፈላጊ እና የሚመጥን የሰው ኃይል የሚፈለግበት አደረጃጀት ነው፡፡ ስራቸውን ቆጥረው መረዳት የማይችሉ ተቋማት ለቢሮክራሲዊ ጥራት መጓደል ምንጭ ናቸው፡፡

ለየትኛው ስራ ምን ዓይነት ሰው የቱ ጋር እንደሚያስቀምጡም አይረዱም፡፡ አሰራር ስለሆነ ብቻ ራዕይ፤ ተልዕኮ፤ እሴቶች ወዘተ ይደረድራሉ ፡፡ ለአመራሩ እና ሰራተኛው ባዳ ናቸው፡፡ የየትኞቹ የስራ ክፍሎች ምን ዓይነት ስራ ከራዕይ እና ተልዕኮ ጋር እንደሚሄድ ብዥታ አለ፡፡ በራዕይ እና ተልዕኮ መካከል ያለው የአፈፃፀም የጊዜ ልዩነት እንኳ ግልፅ አይደለም፡፡ ለዚያ ነው በአንዳንድ ተቋማት ለረጅም አመታት ተለጥፈው የተቀመጡ ራዕይ እና ተልዕኮዎች የሚታዩት፡፡ ራዕይ እና ተልዕኮ አብረው ያረጃሉ፡፡ የተጠናቀቀው እና የሚቀረው አይታወቅም፡፡

ለዚያ ነው በየመስሪያ ቤቱ ትርፍ ሰው እና ሰው ያጣ የስራ ዘርፍ በብዛት የሚታየው፡፡ ለዚያ ነው የቅጥር ደብዳቤን እንጂ የስራ ድርሻ [Job Discription] ለሰራተኞች የሚሠጡ መስሪያ ቤቶች የማይታዩት፡፡ ምክንያቱም የስራ ድርሻ ከታወቀ፡ ለዚያ ስራ የሚያስፈልግ አቅም ይጠየቃል፤ የተሰራው እና ያልተሰራው ይታወቃል፡፡ የስራ ድርሻ ከታወቀ በተሰጡት የስራ ድርሻዎች እና ኃላፊነቶች ያስመዘገበውን ውጤት እንጂ በአሰልቺ ሁኔታ ግላዊ ሁኔታውን መገምገም ግድ አይሆንም፡፡

እናም ወዴት እንደሚሄዱ ማወቅ የአንድ ተቋም ህልውና መሰረት ነው፡፡ ከራዕይ፤ ተልዕኮ፤ እሴቶች ወዘተ በተጨማሪ እያንዳንዱ የስራ ክፍል እና ሰራተኛ ለእነዚህ ግቦች መሳካት የሚኖረውን አስተዋፅኦ የሚያሳይ የስራ ዝርዝር ማስቀመጥ ቁልፍ ጉዳይ ነው፡፡ ያኔ ለእያንዳንዱ ስራ ምን ዓይነት ብቃት እንቅጠርለት ብሎ መስፈርት ማስቀመጥ ይቻላል፡፡ ፖለቲካዊ ሹመትንም ከተቋማዊ ፍላጎቱ እና የሚሾመው ሰው አቅም አንፃር ማየት ይቻላል፡፡ የፖለቲከኞች እና የቢሮክራሲው ግንኙነት በርካታ ዓለማቀፍ ሙግት ያለበት ቢሆንም ከኢትዮጵያ አንፃር መቃኘት ተገቢ ነው፡፡

ስራን እና ደንበኛን ማወቅ የህዝብ አገልግሎት መጀመሪያ ‘ ሀ ሁ..’ ነው፡፡ እነዚያን ስራዎች እንዴት ግልፅ፤ ቀላል እና ቀልጣፋ እናድርጋቸው ብሎ ለደንበኛ እርካታ ዘዴ ማበጀት እና ሁሌም ለማሻሻል መስራት ቁልፍ ጉዳይ ነው፡፡

ጥራት የሌለው ቢሮክራሲ፡ ጥራት ያለው የህዝብ አገልግሎት ሊሰጥ አይችልም፡፡ መደከም ያለበትም እንዴት የቢሮክራሲ ጥራት እንፍጠር የሚለው ላይ ነው፡፡ ቢሮክራሲውን ከጥገኛ ሲቪል ሰርቫንት አፅድቶ በተራማጅ አቅም የማደራጀት ነው፡፡ ያኔ ጥገኛ ደንበኛንም መለየት ይቻላል፡፡ ውስጥን አበላሽቶ ውጭው ላይ መረባረብ ከጥገናዊ ለውጥ አያመልጥም፡፡ ዞሮ ዞሮ ከውጫዊ ባህር ውስጥ ጥገኛ ስለማይጠፋ መፍትሔው የውስጥ አቅምን ማደራጀት ነው፡፡

ትክክለኛውን ሰው ትክክለኛ ቦታ ማስቀመጥ አንደኛው ቁልፍ የቢሮክራሲ ጥራት ማዕከል ነው፡፡ አንድ የስራ ክፍል/ቦታ/ ምን ዓይነት የትምህርት ዝግጁነት ይፈልጋል የሚለው ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ የትኞቹ መስሪያቤቶች ውስጥ ፡ የትኛው የኃላፊነት ደረጃ በፖለቲካ ሹመኞች ይመራ የሚለውም ቁልፍ መልስ ይፈልጋል፡፡ በማያውቀው ዘርፍ የፖለቲካ ሹመኛ በመሆኑ ብቻ ሲቀመጥ፤ ይቅርና የአሰራር ማሻሻያ ማምጣት ከሰራተኛ ጋር ተቀራርቦ መነጋገር እና መስራት ፈተና ይሆንበታል፡፡ የዘርፉን ሙያዊ ጉዳይ አያውቀውምና በሰራተኞቹ ዘንድ የሚሰጠው አመራር አያምርለትም፡፡ የድርጅት አባልነት ሽፋን ይሆናል፡፡ አባል ያልሆኑ ጠንካራ ሰራተኞችን ያሳቅቃል፡፡

በኢትዮጵያ በሚታየው የመልካም አስተዳደር ችግር ውስጥ የአገሪቱ ቢሮክራሲዊ መዋቅር ግልፅነት ያለው፤ በእያንዳንዱ ተቋም የሰራተኛ እና አመራር ሁለንተናዊ አቅምን በትክክለኛ ቦታ ማስቀመጥ፤ ትርጉም ያለው የአቅም ግንባታ እና ማሻሻያ ማከናወን ከሰራተኞች አቅም አንፃር የሚነሳን የአስተዳደር በደል ለመቀነስ ጠቃሚ ነው፡፡

2. የዜጎች ደካማ ብሔራዊ ስሜት [soft state]

ሌላው የቢሮክራሲያዊ ብሎም ፖለቲካዊ ሙስና ምንጭ በመሆን የአስተዳደር በደል ምክንያት የሚሆነው የዜጎች ብሔራዊ ስሜት ደካማ(ልል) መሆን ነው፡፡ ደካማ የአገር ፍቅር በመሪዎች እና ዜጎች ዘንድ መኖር ህዝብን የማገልገል ተነሳሽነትን እና ቁርጠኝነትን የሚያሳጣ ነው፡፡ ህዝብን የማገልገል ፍላጎት በዋናነት ከህዝብ እና ከአገር ፍቅር የሚመነጭ በመሆኑ ይህ አገራዊ ስሜት ሲነጥፍ ቢሮክራሲው ከፍ ሲልም ፖለቲካው በሙስና ይተበተባል፡፡ አገራዊ ቁጭት እና የህዝብ ተቆርቋሪነት በሌሉበት ህዝባዊ አገልግሎት በገንዘብ የሚገዛ እና የሚሸጥ ሸቀጥ ይሆናል፡፡

ብሔራዊ ስሜት በነጠፈባቸው አገራትም የህዝብ አገልግሎት ዘርፍ ፡ የመንግስት ሰራተኞች (ፐብሊክ ሰርቫንትስ/ሲቪል ሰርቫንትስ) ማበልፀጊያ ዘርፍ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ለህዝብ እና ለአገር ፍቅር ሲባል እንኳንስ ነፃ አገልግሎት ለመስጠት ደመወዝ ተቆርጦለትም ህዝብን የማገልገል ፍላጎት ይጠፋል፡፡

በአገራችን አንድ የታሪክ ምዕራፍ በነበረ የፖለቲካ ትግል ሂደት ውስጥ ደመወዝ ይቅርና የማይተካትን ነፍሱን ለህዝባዊ ዓላማ እና የአገር ፍቅር አሳልፎ የሰጠ ትውልድ ታይቷል፡፡ አገርና ህዝብ ከምንም ነገር በላይ ነበር፡፡ ዛሬ ጭንቅ የሆነው በሚሰጠው ቢሮክራሲያዊ ካሳ አገሩንና ህዝቡን ማገልገል ያለመፈለግ ነው፡፡ ስስ ብሔራዊ ስሜት እየወረረን ነው፡፡ ማስመሰል እና ተቃርኖ የሚበዛበት የአገር ፍቅር እናሳያለን፡፡

ወትሮ በአንድ ነፍጠኛ ገዢ መደብ ምክንያት ተፈጠረ የምንለው ኢ-ፍትሐዊነትና አስተዳደራዊ በደል በራሳችንና የአካባቢያችን ተወላጅ አስተዳዳሪዎች ይፈፀማል፡፡ ያለፈውን እየኮነነ ራሱ በዚያው ፀረ-ህዝብ ተግባር ተሰማርቷል፡፡ እቆረቆርለታለሁ የሚለውን ህዝብ የውጭ ጥቃት ሲሆን እንጂ የውስጥ ጥቃት ሆኖ በራሱ ወገን ሲፈፀም ዝም ይላል፤ አሊያም በበደል ይሳተፋል፡፡ ተቃርኖው እና ማስመሰሉ ልክ የለውም፡፡ ግልብ የአገርና ህዝብ ፍቅር ነው፡፡

‘ስደት እድል ሆነ’ እንዳለው ገጣሚ ሞገስ ሐብቱ (ኮ/ል) ኢትዮጵያዊ ስሜቱን የተነጠቀው ከተሜ ብዙ ነው፡፡ በት/ቤቶች ብሔራዊ መዝሙርን መዘመር ሃፍረት ሆኖ የተከፈተው ቴፕ እስኪጨርስ ችኮላው የጉድ ነው፡፡ ያው የውጭ ቋንቋ ት/ቤት እንጂ የሀገር ውስጥ ቋንቋ ት/ቤት መክፈትም ነውር ስለተደረገ እንጂ አዋጭ ስላልሆነ አይደለም፡፡

የልጅ ‘ተዓምራዊ እውቀትም’ የውጭ ቋንቋ መናገር መቻል ነው፡፡ የአገርን አለማወቅ አያስቆጭም፡፡ የሃብት ምንጭ የሆናቸውን አገር ፤ አምኖ የከፈላቸውን ስርዓት ስለማያምኑት በአንድ ወይም በሌላ መንገድ ገንዘብ በማሸሽ (መግባት ያለበት እንዳይገባም በማድረግ) በውጭ አገር ያከማቻል፡፡ በዚህ ረገድ የአሁኑን ትውልድ ተዓምር ፈጣሪነት አንስተው ካለፈው ስለመሻሉ ከሚሞግቱት ጋር አልስማማም፡፡ እኔ ከሞትኩ…. አይነት ራስ ወዳድነት ያነገሰ ትውልድ ውስጡ ባንዳ ነው፡፡

ደካማ ወይንም እየሟሟ በሚሄድ የህዝብ እና የአገር ፍቅር ስሜት ውስጥ ከመንግስት ተቋማት አገልግሎት የማግኘት ጉዳይ ከአገር እና ከህዝብ ጥቅም የሚነሳ ሳይሆን ከአገልጋዩ ሰራተኛ እና ከተገልጋዩ የጋራ ጥቅም የሚመነጭ ፍላጎት ነው፡፡ እናም የአገልግሎት መገናኛ ገመዱ ሙስና ይሆናል፡፡ የግል ጥቅም እንጂ የተገልጋይ ስቃይ (ውጣ ውረድ) አይታየውም፡፡ ተቋማዊ ኪሳራ አያሳስበውም፤ ህዝቡ ጉዳዩ አይደለም፤ የአገር ጉዳትም አይሰማውም፤ ብቻ እሱ ይጥገብ፡፡ ይህ ኣይነቱ አስተሳሰብ የኢንቨስትመንት ሉኣላዊነት በቅኝ ገዢዎች ቁጥጥር ስር ሆኖ ሃብት በጥቂት ባዕዳን በተያዘባቸው አገራት በሰፊው የሚስተዋል ነው፡፡ የቅንጦት ሕይዎት የእነሱ አይደለምና ከገዢዎች እና ነጭ ባለሃብቶች የሚተርፍ ፍርፋሪ የሚያገኝ በመሆኑ ለአገሬው ሰው፡ የአገር እና ህዝብ ፍቅር ምኑም አይደል፡፡ የማን አገር ነውና ይጨነቅበት፡፡

ስስ ብሔራዊ(አገራዊ) ስሜት በነገሰበት ህዝብ እና መንግስት ቢሮክራሲያዊ ሙስና ልቅ ይሁን እንጂ በሌላም መንገድ ብሔራዊ ጥቅምን አሳልፎ የመስጠት አደጋ ይፈጠራል፡፡ ለምሳሌ በበርካታ አገራት እንደሚታየው ከግል ጥቅም በሚመነጭ ፍላጎት ዜጎችን የሚፈጁ የሽብር ተግባራት በሽራፊ ሳንቲም በተገዙ ዜጎች ይፈፀማል፡፡ ማባበያ የሚከፍሉ የውጭ ኩባንያዎች የአገሪቱን ጥቅም የሚያሳጣ መድሎ ይፈፀምላቸው ዘንድ በጉምቱ ባለስልጣናት ትዕዛዝ ይተላለፋል፡፡ ግዢ ቅጡን ያጣል፡፡ የህዝብ እና የአገር ጥቅም ለጥቂት ግለሰቦች ጥቅም ሲባል ለውጭ ኩባንያ ይሰጣል፡፡

ብሔራዊ ስሜቱ የነጠፈ ኃይል የፖለቲካ ስልጣን ሲይዝም (ቢሮክራሲያዊ ቁጥጥር ሲኖረው) በአንድ በኩል የፖለቲካ ኃይሉ አባላት ከሀገር ሃብት ለግል ጥቅም ሲመዘብሩ በሌላ በኩል ከፖለቲካ ቡድኑ ውጭ የሆነ ኃይል ይሄንን ጥቅማቸውን የሚያስከብር ቢሮክራሲያዊ ሙስናን እንዲፈፅም የሚያስገድዱ ህጎችን ያወጣል፡፡ ከዚህ አኳያ በደቡብ አፍሪካ ለረጅም አመታት ተግባራዊ የተደረጉ ህጎች አናሳ ነጮች ከሰፊው ጥቁር ህዝብ በላይ ሃብት እንዲያካብቱ የሚያደርጉ እንደነበሩ ምሁራን ፅፈዋል፡፡

የዜጎች አገራዊ እና ህዝባዊ ስሜት ከህዝብ አስተዳደር ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አለው፡፡ ኢትዮጵውያን በዚህ ረገድ ያለንበት ሁኔታ ተገቢ ጥናት እና ምልከታ ይፈልጋል፡፡ የኢህአዴግ ህዝባዊነት እና የአገር ፍቅር በዛሬው አመራርና ትውልድ ውስጥ ሊፈተሸ ይገባል፡፡

3. ጎደሎ ባህል

በርካታ ምሁራን ለቢሮክራሲያዊ ሙስና መፈፀም ጎጂ ባህላዊ ወጎች ምክንያት እንደሚሆኑ ፅፈዋል፡፡ ጃብራን(1976) የተባሉ ምሁር ‘በሶስተኛው ዓለም የሙስና ምክንያት እና ትርፍ’ ዙሪያ በፃፉት ጥናት ሰንካላ ባህላዊ እምነቶች የሙስና ምንጭ ስለ መሆናቸው ያትታሉ፡፡ ሌሎች በአንፃሩ ከዘመናዊነት ጋር የሚመጣ የነባር እና መጤ ባህል ግጭት የሙስና ምንጭ ነው ይላሉ፡፡ እንዲያውም በዘመናዊነት ሂደት ውስጥ የኢኮኖሚ እና ፖለቲካ ለውጥ እና እድገት እስካለ ሙስና አይቀሬ ነው ባይ ናቸው፡፡

ከነባር ባህል ጋር በተያያዘ በአንዳንድ ማህበረሰብ ዘንድ የግለሰብ መብቶች ፡የቡድን መብቶች ቅጥያ ተደርገው ይታሰባሉ፡፡ በመሆኑም ለቡድኑ የሚኖር ታማኝነት ትልቅ ስፍራ አለው፡፡ ግለሰቡ ከግል መብቶቹ እና የግል ተጠያቂነት ይልቅ ለቡድኑ የሚኖረው ታማኝነት ጠቃሚ ተደርጎ ይታሰባል፡፡ ከግለሰቡ ጉዳይ ይልቅ የቡድኑ (የጎሳው) ጉዳይ ይበልጣል፡፡ በመሆኑም ለቡድኑ የሚኖር ታማኝነት ትልቅ ስፍራ አለው፡፡

በመሆኑም በመንግስታዊ ተቋማት ውስጥም ሆነ መሰል የህዝብ አገልግሎት ኃላፊነቶች ላይ መቀጠር /መሾም/ የቻለ የጎሳ አባል የሚያገኘውን ጥቅም ወይንም የሚያዝበትን የህዝብ ሃብት ከቡድኑ የሚጠበቅበትን ግዴታ ለመወጣት ሲል ለአባሎቹ የማካፈል ባህላዊ ግዴታ አለበት፡፡ ከግል ተጠያቂነት ይልቅ የቡድን ታማኝነት ይበልጣልና ለኔ ለሚላቸው ሰዎች የግል ግዴታውን ለመወጣት ቢሮክራሲያዊ ሙስናን ይፈፅማል፡፡ ከቡድኑ አባላት ውጭ ባሉት ላይ መድሎ ይፈፅማል፡፡ የአስተዳደር በደል ነው፡፡

ይሄንን ሁኔታ ከኢትዮጵያ አንፃር ለማየት ግለሰቦች ለቡድን፤ ጎሳ፤ ብሔርን መሰረት ያደረጉ፡ ከግለሰብ ተጠያቂነት ይልቅ ለወል ፍላጎቶች ተገዢ የሚሆኑበት ባህላዊ ውቅር አለ፡፡ ይህ ከቢሮክራሲዊ አስተዳደር አንፃር ሰፊ ጥናት የሚፈልግ ቢሆንም የጎሳ ስርዓት ባለባቸው እና ከ70 በላይ አናሳ ብሔር ብሔረሰብ ባለበት አገር፡ የግለሰብ መብቶች እንዳሉ ሁሉ አባላት ለወል ግዴታዎች ተገዢ እንዲሆኑ የሚያሰገድዱ ነባር ባህሎች አሉ፡፡ ከአባል አንዱ የፖለቲካም ሆነ ቢሮክራሲዊ ኃላፊነት ሲይዝ ለቡድኑ እና አባሎቹ እንዲሰራ ይጠበቃል፡፡ ያን ባያደርግ መገለል እና ቤተሰባዊ እርግማን ይመጣል በሚል ለጎሳው እና ብሔረሰቡ ባህላዊ ወጎች(ህጎች) ተገዥ መሆን ግዴታ ነው፡፡ ለቡድኑ ወይም ለጎሳው እና ንዑስ ጎሳው የወል ጥቅሞች ተገዢነት ሲባል ስልጣንን ያላግባብ የመጠቀም እና በሙስና የህዝብ ሃብትን የመበዝበዝ ተግባር ይፈፀማል፡፡ ከላይ እንዳየነው የጎሳው አባል በመሆኑ ብቻ አቅም የሌለው ሰራተኛ በአስፈፃሚነት እንዲቀጥር ይገደዳል፡፡ ሙስና፤ መድሎ እና የአስተደደር በደል ይደራል፡፡

በበርካታ የጎሳ እና አናሳ ብሔር ብሔረሰቦች ዘንድ የትዳር አጋር በቤተዘመድ ታጭታ እስከማቅረብ እና የሃብት ክፍፍልም በዚሁ መረብ የሚፈፀም በመሆኑ መተሳሰቡ ጠንካራ ነው፡፡ በነገራችን ላይ እንደ አገር የቡድን መብቶች እና የግለሰብ መብቶችን በተመለከተ በሚደረገው ፖለቲካዊ ሙግት በግለሰብ የተንጠለጠለው አመለካከት እነዚህን ነባራዊ እውነታዎች ከግምት ያላስገባ ነው፡፡ ወደፊት የምንለው ይኖራል፡፡ እዚህ ላይ መረዳት ያለብን ግን ከአናሳ የመጣ ሁሉ፡ ለመጣበት ቡድን ያደላል፤ የህዝብን ሃብት ይበዘብዛል የሚል መደምደሚያ ላይ አያደርስም፡፡ ለቡድን ጥቅሞች እና መብቶች ተገዢነቱ ላላ ባለበት አካባቢ ሐቀኛ አገልጋይ አለ፡፡ ዞሮዞሮ ከባህል ጋር የተያያዙት የስራ እና አስተዳደራዊ ችግሮች ከቡድን ወግ እና አስገዳጅ የወል ጉዳዮች አንፃር ብቻ የሚታይ አይደለም፡፡ ሌሎችንም መሰረታዊ የስራ ባህል፤ ልማዳዊ ወጎች እና ተያያዥ ጉዳዮችን ታሳቢ ያደረገ ጥናት እና መፍትሔ ማድረግ ከልማድ፤ ወጎች እና ባህሎች አንፃር ለሚነሱ የአስተዳደር በደሎች መፍትሔነት ያገለግላል፡፡

4. ልጓም የለሽ ደካማ ህጎች

ሌላው የቢሮክራሲዊ ሙስና ምንጭ በመሆን የአስተዳደር በደል ምክንያት የሚሆነው መንግስት ከሚያወጣቸው የቁጥጥር እና አስተዳደር ህጎች እና መመሪያዎች ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ ከመንግስት የቁጥጥር ህጎች ጋር በተያያዘ የሚፈጠረው ባህሪ የኪራይ ፈላጊነት ነው፡፡ ቢሮክራሲያዊ ሙስና ደግሞ በቀዳሚነት የኪራይ ፈላጊነት ነው፡፡

አገር የሚተዳደረው በህግ ነው፡፡ ተቋም የሚተገብረው በአዋጅ እና መመሪያ ነው፡፡ ለአስተዳደር እና ቁጥጥር የሚወጡ ህጎች ደካማ፤ ክፍተት ያለባቸው፤ ግልፅነት የሚጎላቸው እና ጎታች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ተገልጋዮችን እንጂ ፈፃሚያቸውን ታሳቢ ያላደረጉ ይሆናሉ፡፡ ያኔ በአገልጋይ እና ተገልጋይ ዘንድ ኪራይ ፈላጊነት እና ሙስና እንዲነግስ ምክንያት ይሆናሉ፡፡

ሃብት ለመፍጠርም ሆነ ሃብት ለማደል (ለማሰራጨት) መንግስት ሁሉንም የኪራይ አስተዳደር ስራዎች በህግ እና መመሪያ የሚሰራ መዋቅር በማበጀት ነው፡፡ ለእያንዳንዱ አገራዊ ችግር አዋጅ እና መመሪያ እናዘጋጃለን ሲባል የምንሰማውም ለዚያ ነው፡፡ የኪራይ ትግሉም እነዚህን ህግና መመሪያዎች ሰብሮ ጥቅምን የማረጋገጥ ነው፡፡ በተለይም በኢኮኖሚው ውስጥ የብቸኝነት መብት [monopoly right] የሚያጎናፅፉ ህግና መመሪያዎች እንዲወጡ ከፈፃሚም ከተገልጋይም የጋለ ትግል ይደረጋል፡፡

ህጎች ክፍተት ያለባቸው፤ ደካማ እና ፈፃሚያቸውን የማይቆጣጠሩ ሲሆኑ (በሌላ አባባል ፈፃሚዎች ለሚፈጥሩት ማስተጓጎል ተጠያቂነትን ያልያዙ እና ደንበኛ ተኮር ብቻ ከሆኑ) የፈፃሚዎች መደራደሪያ ይሆናሉ፡፡ አንድ ህግ/አዋጅ/መመሪያ/ አንድን አገራዊ ኢኮኖሚያዊ/አስተዳደራዊ/ ሁኔታ ለመግራት ሲባል በከፍተኛ የመንግስት አካላት (ሚኒስትሮች ምክር ቤት፤ የህ/ተ/ም/ቤት..ወዘተ) ፀድቀው፡ ለፈፃሚ ተቋማት ሲወርዱ፡ ዞሮዞሮ ወደ አንድ ፈፃሚ ግለሰብ ጠረጴዛ መሄዱ አይቀርም፡፡ ተጠያቂነትን የማያስከትል ደካማ ህግ ነውና ለዚያ ፈፃሚ እና ደንበኞች የሙስና በር ይከፍታል፡፡ ህጉ አስገዳጅ ነውና የግድ በዚያች ቢሮ የሚያልፉ ደንበኞች ይኖሩታል፡፡ የህጎችን ክፍተት የሚያውቅ ደንበኛም እንዴት ከዚያ ፈፃሚ ጉዳይ እንደሚያልቅለት ያውቃል፡፡ የመንግስት ሰራተኞችም ህጉ በደንበኞች ላይ ያለውን አስገዳጅነት ያውቃልና ጉዳይን በማጓተት፤ ተገልጋይን በማማረር፤ ወደ ሙስና ድርድር ይጎትታቸዋል፡፡

ፈፃሚው የቡድን/ጎሳ/ ግዴታዎች ካለበት፤ ያለብቃቱ የተቀጠረ ከሆነ፤ ደካማ አገራዊ ስሜት ካለው ደግሞ አፈፃፀሙ ምን ያህል የሞተ የሙስና ማዕድ እንደሚሆን መገመት ይቻላል፡፡ በየወሩ ከሚያገኘው ደመወዝ (ቢሮክራሲያዊ ካሳ) የተሻለ የሚገኝበት በመሆኑ ፈፃሚው ይሄንኑ ጥቅም የሚያሳድግበትን መንገድ ማፈላለግ ላይ ይተጋል፡፡ ህጎቹ ክፍተት አለባቸውና ፤ ደካማ ናቸውና ለምዝበራ ክፍት ናቸው፡፡ ደንበኞችም በቀላል ክፍያ ጉዳይ እንደሚያልቅላቸው የሚረዱ ይሆናሉ፡፡ ከፈፃሚ በላይ ህግ አውጭውን ለመጠምዘዝ ያማትራሉ፡፡

 5. ስር የሰደደ ድህነት

ስር የሰደደ ድህነት እና ኢ-ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል እንዲሁ ለቢሮክራሲዊ ሙስና እና የአስተዳደር በደል መንስኤ ነው፡፡ የመንግስትን ፖሊሲዎች እና ህጎች እንዲያስፈፅሙ የተቀጠሩ ሰራተኞች የሚያገኙት ደመወዝ (ቢሮክራሲያዊ ካሳ) መሰረታዊ ፍልጎቶቻቸውን ለማሟላት የማይበቃቸው ሲሆን እና ኑሯቸው በችግር ውስጥ ሲሆን ለአደጉበት የስነምግባር መርህ እና ብሔራዊ ስሜት ተገዢነታቸው እየቀነሰ ይሄዳል፡፡ ኑሮው በከበደው ቁጥር ቢሮክራሲያዊ ሙስናን ለመፈፀም እየተገደደ ይሄዳል፡፡ የአለም ባንክ በ1979 በቀድሞዋ ዛየር ላይ አጠናሁት ባለው ዘገባ 92 በመቶ የመንግስት ሰራተኞች የሚያገኙት ወርሃዊ ደመወዝ ምግብ፤ መጠልያ እና ልብስ የመሳሰሉ መሰረታዊ ፍጆታዎችን ለመሸፈን አይችሉም ነበር፡፡ እናም አነስተኛ ደረጃ ላይ ያሉ የመንግስት ሰራተኞች በከተሞች ያለ የዋጋ ግሽበት ታክሎበት በተፈጠረው የኑሮ ጫና ራሳቸውን እና የሚያስተዳድሯቸውን ሰዎች ለመርዳት ሲሳናቸው በሙስና ተግባር ላይ ይሰማራሉ፡፡

ይህ ግን ኑሮ የከበደው ድሃ ሁሉ ወደ ዝርፊያ መግባት አለበት በፍፁም ማለት አይደለም፡፡ ከባድ ኑሮ አማራጭ ስራዎችን እንጂ ህዝብ መጉዳትን አይጠይቅም፡፡ ማጣት በስራ እንጂ በዝርፊያ አይወገድም፡፡ ከበቂ በላይ ሃብት ያለው፤ ኑሮው የተመቻቸለትስ በሙስና አይዘፈቅም ወይ፤ የአስተዳደር በድል ምንጭ አይሆንም ወይ? አሳምሮ ይሆናል!፡፡ ድህነት አንዱ እንጂ ብቸኛ ምክንያት አይደለም፡፡ አቅመ ቢስ ከሆነ፤ ደካማ የህዝብና የአገር ፍቅር ካለው፤ የሚቆጣጠረው ህግ ሽባ ከሆነ ያለው ሃብት አያግደውም፡፡

ስር የሰደደ ድህነት ለሰራተኞች ሙስና መፈፀም አስገዳጅ ነው አይደለም የሚለውን ሙግት ከስራ ባህል፤ ስነምግባር እና የአገር ፍቅር አኳያ ለመሞገት ቢቻልም፡ የህልውና ፈተና ላይ የሚያደርስ ማጣት በአንድ በኩል ከአገልግሎት ፈላጊ መድሎን የሚፈልጉ አካላት ይሄንን ደካማ ጎን ተጠቅመው ወደ ሙስና ሲመሯቸው በሌላ በኩል የተቀጠሩበትን የመንግስት ስራ ተጠቅመው ከደንበኞቻቸው ጥቅምን ፍለጋ እንዲሰሩ ይገደዳሉ፡፡ ባያምኑበት እንኳ ለጊዜያዊ ችግር ማስታገሻነት የጀመሩትን አቋራጭ ይለማመዱታል፡፡ ሙሰኛ አመራር በአገሪቱ በሚታይበት ወቅት ደግሞ ‘እኔ ማን ነኝና ነው?’ በማለት ከራሱ ጋር ሙግት ውስጥ ሊገባ ይችላል፡፡ ተጠያቂ የማያደርጉ ህጎች ባሉበት ደግሞ ምቹ ሁኔታን ይፈጥርለታል፡፡

በመሆኑም የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ስናነሳ በሰሞነኛ የንቅናቄ ስራ ብቻ የሚፈታ አይደለም፡፡ ከማስታገሻነት አልፎ ፈዋሽ የመልካም አስተዳደር እመርታ ማማጣት የሚቻለው በአንድ በኩል ከላይ ባነሳናቸውና ሌሎች ምንጭ የሚሆኑና አባባሽ ባህሪያትን እና ሁኔታዎችን በመመርመርና መፍትሔ በማበጀት ነው፡፡ በአገር ደረጃ ያለ የወደቀ የጥራት አስተሳሰብ (ደንበኛን ያለማወቅ እና ለደንበኛ እርካታ ግድ ማጣት) በህዝባዊ አገልግሎት ላይ ያለውን ችግር እና የአስተዳደር በደል መንስኤነት በሌላ ፅሁፍ ለማየት እሞክራሁ፡፡

       

Leave A Reply

Your email address will not be published.