መቱ ዩንቨርስቲ: ችግሩን አምኖ መፍትሄ መፈለግ ያሻል

መቱ ዩንቨርስቲ ትልቅ ችግር እንደሌለ አስመስሎ መነታረክ አደጋውን አላይም ብላ አሸዋ ውስጥ ጭንቅላቷን የቀበረችውን ሰጎን አይነት መሆን ነው:: በዚህ ጉዳይ ብዙ ተጠያቂ አካላት እንደሚኖሩ ቢጠበቅም የዩንቨርስቲው ከፍተኛ አመራሮች ከግንባር ቀደም ተጠያቂነት አያመልጡም::

የተጠያቂነት ነገር ወደፊት በስፋትም ሆነ በጥልቀት እንደሚመጣ እየተመኘን ዛሬ ላይ ጥርሱን አግጦ ስለተከሰተው ችግር በመፍትሄዎቹ ዙርያ እንምከር::

(እዚህ ላይ የቀረቡት ችግሮችም ሆነ መፍትሄዎች ሌሎች ተመሳሳይ ችግር ውስጥ ላሉ ዩንቨርስቲዎች ተግባራዊ ሊሆን የሚችል ነው::)

እውነታ 1 – ትምህርት ተቋርጧል

እውነታ 2 – ከሌሎች ክልል የመጡ ተማሪዎች ትልቅ ስጋት ላይ ሲሆኑ ቤተሰቦቻቸውም በስጋት ውስጥ ይገኛሉ

እውነታ 3 – እንደ አዲስ የተደራጀው የፀጥታ ም/ቤትም ከላይ እስከ ታች እስከሚቀናጅ የራሱ የሆነ ጊዜ መውሰዱ አይቀሬ ነው

ስለዚህ ጊዜያዊ መፍትሄ የሚሆነው …

1) ዩንቨርስቲውን በጊዜያዊነት ዘግቶ ሁሉም ተማሪ ወደየቤተሰቡ እንዲሄድ ማመቻቸት

2) ዩንቨርስቲዎች የፌደራል ተቋም ስለሆኑ በሃገሪቷ ያሉ ዩንቨርስቲዎች በሙሉ በቋሚነት በፌደራል ፖሊስ ብቻ እንዲጠበቁ ማድረግ

3) በሁሉም ሚድያዎች ተገቢውን የማረጋግያ ስራዎች መስራት

4) በዩንቨርስቲዎች አካባቢ በግርግሮቹ ዙርያ እጃቸው እንዳለበት የሚጠረጠሩ አካላትን በጊዜያዊነት ገሸሽ አድርጎ በስክነት ጥልቀት ያለው ምርመራ ማካሄድ

5) የዚህ ብሄር ተወላጅ ተማሪዎች በዚህ ክልል አይማሩ የሚለውን የሰሞኑን መመሪያ አይሉት እብደት አስተካክሎ ሁሉም ተማሪ ችግሮቹ ከመከሰታቸው በፊት ወደነበሩበት ዩንቨርስቲ እንዲመለሱ ማድረግ

እነዚህ በአጭር ጊዜ ሊከናወኑ የሚችሉ መፍትሄዎች ሲሆኑ በረጅሙ ሊከናወኑ የሚገባቸው ሌሎች ስር-ነቀል መፍትሄዎች አሉ:: ከእነዚህም ውስጥ በዋናነት የሚጠቀሰው በኢትዮጵያዊነት ዙርያ እጅግ በጣም ብዙ ስራዎች እንደሚቀሩ ነው:: የኢትዮጵያዊነት መሸርሸር ነው ዘንድሮ የዚህ ብሄር ተወላጆች እዛ ክልል አይማሩ ወደሚል ዝቅታ ያወረደን::

ከዚህም በላይ ብዙ ስራዎች ስለሚጠብቀን ለጊዜው ከፍ ሲል የጠቀስኳቸውን ጊዜያዊ መፍትሄዎች ቢተገበሩ ጠቃሚ ይመስለኛል::

እናንተስ ምን ትዘይዳላችህ?

Leave A Reply

Your email address will not be published.