መንግስት “እያሽሟቀቀ” ይሆን?

(አልአሚን ተስፋዬ) – “ሟሽሟቀቅ” ደግሞ ምንድን ነው? ምን ማለትስ ነው ለምትሉ አንባቢዎች የቃሉን ታሪካዊ አመጣጥ አጠር አድርጌ ለማቅረብ ያህል ሀገራችን ካፈራቻቸው ደራሲያን መካከል ባሴ ሀብቴ የተባለ ፀሐፊ እና ተርጓሚ አንዱ ነበር፡፡

ታዲያ ባሴ ሀብቴ አንድ ቀን ከስብሐት ገ/እግዛብሔር ጋር ሲያወጋ እና ሲጫወቱ ቆይቶ የልጅነት ትዝታውን እንዲህ ሲል ማውራት ጀመረ “በልጅነቴ የአማርኛ አስተማሪያችን “ቆቅ” በሚል ርዕስ ግጥም አሁኑኑ ፃፉ ከሀያ የሚያዝ ነው አሉን፡፡ እኔም የመጀመሪያውን የግጥም መስመር “አንዲት ቆቅ” ብዬ ብጀምርም በቅ የሚያልቅ ሌላ ቃል ስፈልግ ሰዓቱ ሊጠናቀቅ ሆነ መምህሩ ወረቀቶቹን መሰብሰብ ከመጀመራቸው በፊት “አንዲት ቆቅ፣ ገደል ለገደል ስታሽሟቅቅ” ብዬ የፈተና ወረቀቱን አስረከብኩኝ፡፡ በነጋታው አስተማሪው ስሜን ጠርተው ሟሽሟቀቅ ስትል ምን ለማለት ፈልገህ ነው? በሚል ተማሪ ፊት አፈጠጡብኝ እኔ ግን መልስ አልነበረኝም፡፡

ይህን ወሬ ያደመጠው ስብሀት ገ/እግዚብሔር በጣም በመገረም “እኔ አስተማሪውን ብሆን ሃያ ከሃያ ነበር የምሰጥህ ምክንያቱም ሁልጊዜ የኢትዮጵያ ህዝብ ምን እያደረገ ነው? ኢትዮጵያ ራሷ ያለችበት ሁኔታ በምን ይገለፃል? ብዬ ሳስብ መልሱ ይጠፋኝ ነበር፡፡ የምገልፅበትም ቃል አልነበረኝም፤  ለካ” እያሸሟቀቅን ነው” አለ፡፡

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የዚህ ፅሑፍ ፀሐፊ ደራሲያን እና ጋዜጠኛ ጓደኞቹ በሙሉ ምን እየተደረገ ወይም ምን እየሆንን እንደሆነ ባልገባን እና ግልፅ ባልሆነልን ጊዜ ሁሉ “እያሽሟቀቅኩ ነው” የሚል መግባቢያ ፈጥረን እነሆ እስከዛሬም በማሽሟቀቅ ላይ እንገኛለን፡፡

ታዲያ አሁን ሀገራችን ያለችበት ሁኔታ ሀገራችንን እየመራ ያለው መንግስት መክረሚያውን እያሳየ  ያለው ባህሪ አልገባ ቢለን በኢህአዴግ የሚመራው መንግስት በእርግጥ እያሽሟቀቀ መሆን አለበት ለማለት የተገደድንባቸውን አንዳንድ ነጥቦች እንደሚከተለው ላነሳላችሁ ወደድኩ፡፡

በህግ አውጭው (ፓርላማ) እና በህግ አስፈፃሚው የሚኒስትሮች ም/ቤት መካከል ያለው የተዋረድ ስልጣን በአስፈፃሚው ከፍተኛ የበላይነት ተውጧል የሚል ጥናት በኢፌዲሪ ፖሊስ ጥናትና ምርምር ተቋም ቀርቦ ሕዝቡ እና መገናኛ ብዙሀን ጥናቱ ትክክል ነው ፓርላማው የሚጠበቅበትን የህዝብ ተወካይነት ድርሻ በተሰጠው ስልጣን እየተጠቀመበት አይደለም ይልቅስ የሚኒስትሮች ማህተም መምቻ (Rubber Stamp) ነው የሆነው በሚል በርካታ የማስተካከያ እርምጃዎች ይወሰዳሉ ብለን ስንጠብቅ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መጡና “ጥናቱን አላውቀውም በወሬ ነው የሰማሁት ከጥናት የሚቆጠርም አይደለም” ሲሉን የጥናት ተቋሙ ተጠሪነቱ ለሳቸው ቢሮ ሆኖ ሳለ እንኳን እሳቸው እኛ ሚስኪኖቹ ጥናቱን አገላብጠን ባየንበት ሀገር ይህን ማለታቸው በእርግጥ መንግስት የማሽሟቀቅ ባህሪ እያሳየ ለመሆኑ አንዱ ምልክት ነው ማለት እንችላለን፡፡

ሌላው የሀገራችን ሰላም እና ፀጥታ በማስከበር ረገድ የመከላከያ ሰራዊት የፌዴራል ፖሊስ እና የክልል የፖሊስ ሰራዊቶች የማይተካ ሚና እንዳላቸው ይታወቃል አሁን አሁን ግን ከእነዚህ ተቋማት ባለፈ በየክልሉ ልዩ ኃይል (Special Force)በሚል የተቋቋሙ ጦር ያነገቡ የየክልሉ ሠራዊቶች ከመጠናከር አልፈው በሁለት ክልሎች መካከል ግጭት እስከመፍጠር ሄደው በርካቶች ሞተው እና ቆስለው (ምርኮኛ ስለመኖሩ አልተነገረንም) የሁለቱ ክልል ባለሥልጣኖች ከፌዴራል መንግስት በተውጣጡ ባለስልጣናት አማካኝነት ድርድር አካሂደው እርቅ ፈፀሙ የሚል ዜና መመልከታችን በእርግጥም ሀገራችን እንደሀገር እያሽሟቀቀች ለመሆኗ ሌላው ማሳያ ነው፡፡

በአጠቃላይ በርካታ የማሽሟቀቅ ምልክቶችን መደርደር ቢቻልም የሰብአዊ መብት ሪፖርት፣ ፓርላማው በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ኢቢሲ ላይ የሰጠው አስተያየት እና የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ የሰጡትን መልስ ተከትሎ ሊወሰድ እየተዘጋጀ ያለ እርምጃ፣ “የትግራይ አክቲቪስት ነን” በሚል ያልተሰረዘን የባቡር ፕሮጀክት ተሰርዟል ከማለት አልፈው የትግራይን ተጠቃሚነት ከሌላው የኢትዮጵያ ክልሎች ጋር ሳያገናዝቡ ያልተጠበቀ የበዛ ክልላዊ ስሜት ማሳየታቸው፣ የትግራይ ክልልም ለሚዲያ ያለው ተደራሽነት ግልፅ ያለመሆኑ ብቻ ሳይሆን ማንኛውንም አስተያየት ለመፈረጅ የሚያሳየው ችኮላ፣ በአንድ በኩል የፌደራል ስርዓቱን ለማጠናከር ሀገራዊ አንድነት ላይ ትኩረት መደረግ አለበት የሚሉ ትላልቅ ባለሥልጣናት በሌላ በኩል የየድርጅታቸውን እና የየክልላቸውን ጉዳይ ብቻ ለማሳለጥ መሬት ሕገ-መንግስቱ ላይ በተቀመጠው መሠረት የሁሉም የኢትዮጵያ ህዝቦች መሆኑ የቀረ ይመስል መሬት የክልሎች ሉዓላዊ ይዘት የሚያስመስል አሰራሮች አዚህም እዚያም መታየታቸው እና መጪው ጊዜ ላይ ዜጐች ከተወለዱበት እና ካደጉበት አካባቢ ወጥተው እንደልብ በመላው ሀገሪቱ ተዘዋውረው የመኖር የመስራት እና የመንቀሳቀስ መብታቸው ከመቼውም ጊዜ በላይ አደጋ ላይ መውደቁን ስንመለከት ምንድን ነው እየሆነ ያለው? በምን ቃል ነው ይህ ሁኔታ የሚገለፀው? ብለን ብንጠይቅ ለጊዜው ያለን አማራጭ ቃል “እያሽሟቀቅን” ነው የሚለው ብቻ ነው፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.