ሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ለኦሮሚያ ተፈናቃዮች የገነባውን 121 ቤቶች አስረከበ

(ሰንደቅ)- ሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ በኦሮሚያና በሶማሌ ግጭት ለተፈናቀሉ ወገኖች መጠለያ የሚሆኑ በቢሾፍቱ ከተማ የገነባቸውን 121 ቤቶችን ቅዳሜ መጋቢት 1 ቀን 2010 ዓ.ም ለከተማ አስተዳደሩ አስረከበ።

የቤቶቹን ቁልፍ ለቢሾፍቱ ከተማ ከንቲባ ወ/ሮ ገነት አብደላ ያስረከቡት ዶ/ር አረጋ ይርዳው የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ቺፍ ኤግዚኪዩቲቭ ኦፊሰር ናቸው።

ቴክኖሎጂ ግሩፑ ቤቶቹን በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ ገንብቶ ለማጠናቀቅ 12 ሚሊየን ብር ያህል ብር ወጪ አድርጓል።

ቤቶቹ በከተማ አስተዳደሩ የተቀመጠውን ስታንዳርድ (ስፋትና የመሥሪያ ግብአቶች) ጠብቀው በጥያቄው መሠረት በቆርቆሮ የተገነቡ ቢሆንም ወደፊት ወደግንብ መቀየር ቢፈለግ መሠረቱ ጠንካራ ተደርጎ መገንባቱን፣ በዚህም ምክንያት የቤቶቹ ዋጋ አስተዳደሩ ከተመነው መጠነኛ ጭማሪ ሊያሳይ መቻሉን ዶ/ር አረጋ ጠቁመዋል።

እያንዳንዱ ቤት በጠቅላላ 105 ካሬ ሜትር ይዞታ ያለው ሲሆን መታጠቢያና መጸዳጃ ቤቶችን ጨምሮ ቤቶቹ በ50 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ እንዲያርፍ መደረጉንም ለማወቅ ተችሏል።

አቶ ቶሎሳ ደገፉ የኦሮሚያ ክልል ተወካይ በሥነሥርዓቱ ላይ ሲናገሩ ሼህ ሙሐመድ ቀደም ሲል 40 ሚሊየን ብር ለኦሮሚያ ክልል ለተፈናቃዮች የማቋቋሚያ ሥራ መለገሳቸውንና ድጋፉ እንደሚቀጥል ለፕሬዚደንታችን ለአቶ ለማ መገርሳ በገቡት ቃል መሠረት አሁንም ከድርጅቶቻቸው መካከል አንዱ በሆነው በሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ በቢሾፍቱ ከተማ የገነባው ቤቶች እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል። ቤት ማግኘት አንድ ነገር ቢሆንም በቀጣይም ተፈናቃይ ወገኖች መደገፍ ይገባል ያሉት አቶ ቶሎሳ በቀጣይም መሰል ድጋፎች እንዳይለዩ አደራ ብለዋል። በዚህ ወሳኝ ወቅት ከጎናችን የቆሙ ወገኖች ሁሉ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስትና ሕዝብ መቼም አይረሳቸውም ሲሉ ተናግረዋል።

የተከበሩ ወ/ሮ ገነት አብደላ የቢሾፍቱ ከተማ ከንቲባ በርክክብ ሥነሥርዓቱ ላይ እንደተናገሩት ሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ የተደረገለትን ጥሪ አዎንታዊ ምላሽ በመስጠት ይህን የመሰለ ጥራቱን የጠበቀ ቤቶችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ገንብተውልናል። ለተደረገልን ድጋፍ በቢሾፍቱ ከተማ ሕዝብና በተፈናቃይ ወገኖች ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ዶ/ር አበራ ደሬሳ የኦሮሚያ ክልል ተፈናቃዮች መልሶ ማቋቋም ኮምቴ ሰብሳቢ በበኩላቸው የማንፈልገው፣ የማንወደው፣ መሆን የሌለበት አሳዛኝ ድርጊት በአገራችን ሆኗል። ይህን ያህል ቁጥር ያለው ሕዝብ ከሚኖርበት አካባቢ በአንድ ጊዜ ሲፈናቀል ይህ የመጀመሪያው ሳይሆን አይቀርም ብለዋል። ችግሩ ካጋጠመ በኋላ የኦሮሞ ተወላጆች ብቻ ሳይሆኑ ሌሎችም ኢትዮጵያዊያን ወገኖች መልሶ ለማቋቋም ያደረጉት ጥረት በማድነቅ ችግሩ በሌላ በኩል አንድነትንና መረዳዳትን ያስቀደመ መልካም ነገር ይዞልን መጥቷል ሲሉ ተናግረዋል።

የሼህ ሙሐመድ ስም በተገቢው መሠረት በጥሩ ሲነሳ መስማታቸው እንዳስደሰታቸው የገለጹት ዶ/ር አረጋ ሼህ ሙሐመድ ችግር ቢገጥማቸውም ለወገናቸው የሚያደርጉት አስተዋጽኦ በምንም ምክንያት እንዲስተጓጐል ስለማይፈልጉ ሥራዎቻችን ተጠናክረው ቀጥለዋል በማለት በቀጣይም አቅም በፈቀደ መጠን ወገናዊ ድጋፍ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

ዶ/ር አረጋ ይርዳው የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ቺፍ ኤግዚኪዩቲቭ ኦፊሰር ስለግንባታው በሰጡት አስተያየት ቤቶቹን የገነቡት የቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር ያቀረበላቸውን ወገናዊ ጥሪ ምላሽ መሠረት መሆኑን አስታውሰዋል። መጀመሪያ ላይ 50 ያህል ቤቶችን ለመሥራት አቅደን ነበር። ለዚህ መስሪያ የተረከብነው ቦታ ስናየው ከዚህም በላይ ሊያሰራን እንደሚችል በመገንዘባችን በጥቅሉ ወደ 121 ቤቶችን በቀረበው ዲዛይንና የግንባታ ቁሳቁስ ለመገንባት ችለናል ብለዋል።

ዶ/ር አረጋ የቤቶቹን መገንባት አስመልክቶ ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው አጭር የቃለምልልስ ቆይታ የተደበላለቀ ስሜት እንደተሰማቸው ገልጸዋል። በአንድ በኩል ለወገኖቻችን ጥሪ ምላሽ በመስጠት ቤቶቹን መገንባታችን የሚያስደስተኝ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ እንዲህ ዓይነት መፈናቀል ለምን ሊከሰት ቻለ የሚለው ጥያቄ ዘወትር በውስጤ እየተመላለሰ ያሳዝነኛል ብለዋል። ወደፊትም እንዲህ ዓይነት ነገር ዳግም ያጋጥማል ብዬ አልገምትም ሲሉም አክለዋል። ዶ/ር አረጋ ጨምረውም በሻሸመኔ፣ በአዳማ፣ በቡራዩ፣ በወንጂ ለተመሳሳይ ተግባር ከአስተዳደሮቹ ለቀረቡ የዕርዳታ ጥያቄዎች የገንዘብ ዕርዳታ በቴክኖሎጂ ግሩፑ ኩባንያዎች የተበረከተ መሆኑን ገልጸዋል።

ዶ/ር አረጋ አይይዘውም በግንባታ ሥራው ወቅት ደከመን ሰለቸኝ ሳይሉ አስተዋጽኦ ያደረጉ የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ በቢሾፍቱ የሚገኙ አምስት አባል ኩባንያዎች ሠራተኞችና የሥራ መሪዎችን አመስግነዋል።

በዕለቱ የቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር ለሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፑ የቀረበን ሽልማት በዶ/ር አረጋ ይርዳው አማካይነት አበርክቷል።

ከሶማሌ ክልል የተፈናቀሉ የኦሮሚያ ተወላጅ ወገኖች በሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ የእራት ግብዣ ከተደረገላቸው በኋላ አዲስ ወደተሰራላቸው ቤቶች መግባት መጀመራቸውን ለመመልከት ችለናል።
ባሳለፍነው ቅዳሜ ዕለት በቢሾፍቱ ከተማ በተካሄደው የርክክብ ሥነሥርዓት ላይ የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የቢሾፍቱ ከተማ ከንቲባ፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎችና የቢሾፍቱ ከተማ ጥሪ የተደረገላቸው ነዋሪዎች እና የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ የሥራ መሪዎች ተገኝተዋል።

የቢሾፍቱ የቤቶች ግንባታ የመሠረት ድንጋይ በወ/ሮ ገነት እና በዶ/ር አረጋ የተቀመጠው ታህሳስ 11 ቀን 2010 ዓ.ም ነበር። 

Leave A Reply

Your email address will not be published.