ሬክስ ቲለርሰን በኢትዮጵያ ቆይታቸው በሁለትዮሽ እና ቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ ይመክራሉ

(ኤፍ ቢ ሲ)- የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክስ ቲለርሰን በኢትዮጵያ ጉብኝታቸው በሁለትዮሽ እና ቀጠናዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከሃገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ይወያያሉ።

በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳይ ተጠባባቂ ረዳት ሚኒስትር አምባሳደር ዶናልድ ያማማቶ ዛሬ በሚኒስትሩ የኢትዮጵያ ጉብኝት ዙሪያ ለጋዜጠኞች በስልክ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም የሬክስ ቲለርሰን የኢትዮጵያ ቆይታ በዋናነት በሁለት ጉዳዮች ዙሪያ ያተኮረ ነው ብለዋል።

በቀዳሚነትም ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር በሁለትዮሽ እና ቀጠናዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

በተለይም ሁለቱ ሀገራት በመካከላቸው ያለውን የንግድ እና ኢንቨስትመንት ትስስር ማጠናከር የሚያስችሉ ውይይቶች ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል ነው ያሉት።

እንደ እርሳቸው ገለጻ ቲለርሰን በአዲስ አበባ በሚኖራቸው ቆይታ ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ መሃማት ጋር በወቅታዊ የአፍሪካ የደህንነት ስጋቶች እና የምጣኔ ሀብት አማራጮች ዙሪያም ይወያያሉ።

በተለይ የደቡብ ሱዳን፣ የሶማሊያ እና የቻድ ሃይቅ አካባቢ ሀገራት የፀጥታ ጉዳይ ቀዳሚ የመወያያ ነጥቦች ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ሬክስ ቲለርሰን አሜሪካ በአፍሪካ ላይ የምትከተለውን ፖሊሲ ነገ በጆርጅ ማሶን ዩኒቨርሲቲ ይፋ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.