በሀገሪቱ በቀጣይ አንድ ዓመት 7 ነጥብ 8 ሚሊየን ዜጎች የምግብ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል ተባለ

(ኤፍ.ቢ.ሲ):-  በኢትዮጵያ ከጥር 2010 እስከ ታህሳስ 2011 ዓመተ ምህረት የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች ቁጥር 7 ነጥብ 8 ሚሊየን መሆኑ ተገለፀ።

መንግስት እና ለጋሽ ድርጅቶች ዛሬ በጋራ ባዘጋጁት መድረክ ላይ የሰብአዊ እርዳታና የአደጋ አይበገሬነት ሰነድ ይፋ ሆኗል።

የብሄራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ እንደገለፁት፥ በሀገሪቱ በተለይም ከቅርብ አመታት ወዲህ የድርቅ ክስተት እንደቀድሞው በየአስር እና አምስት አመቱ ሳይሆን ተደጋጋሚነቱ እየጨመረ ነው።

በዚህም በኢኮኖሚውና በህዝባችን የአኗኗር ዘይቤ ላይ አሉታዊ ተፅእኖን በማሳረፍ ላይ መሆኑን የጠቀሱት ኮሚሽነሩ፥ በቀጣይ ለአንድ አመት የሚቆይ የተረጂ ቁጥር 7 ሚሊየን 880 ሺህ 446 መሆኑን አስታውቀዋል።

ለእነዚህ ዜጎች የሰብዓዊ እርዳታ ለማቅረብም 1 ነጥብ 4 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር እንደሚያስፈልግ ነው የገለፁት።

በአሁኑ ወቅት በአለም ላይ የሚታየው የአየር ንብረት ለውጥ በኢትዮጵያ ላይ አሉታዊ ተፅኖውን በማሳረፍ የድርቁን ድግግሞሽ እያፋጠነው እንደሚገኝ ተነግሯል።

ይህም ጉዳቱን በመቋቋምና በመከላከል ረገድ መንግስት ከፍተኛ በጀት በመመደብ ከህብረተሰቡ እንዲሁም ከለጋሽ ድርጅቶችና አጋሮች ጋር በመሆን ወቅታዊ ምላሽ በመስጠት ላይ ነው ብለዋል።

ከዚህ ጎን ለጎንም በዘላቂ ልማት አደጋውን ለመከላከልና ለመቀነስ የሚያስችሉ የልማት ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን አስረድተዋል።

በመኸር ወቅት ጥናት መሰረት በአሁኑ ሰዓት የተለየው የተረጂው ቁጥር 7 ነጥብ 8 ሚሊየን መሆኑ ከባለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ37 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።

ለዚህም በመኸር ጥናት የተሸፈኑ የሰብል አብቃይና አርብቶ አደር አካባቢዎች ለተከታታይ አመታት በድርቅ የተጠቁ መሆናቸውና ለማገገም አለመቻላቸው እንዲሁም በተወሰኑ ኪስ ቦታዎች የዘነበው ዝናብ በመጠንና በስርጭት በቂ አለመሆኑ እንደምክንያት ተጠቁሟል።

በተጨማሪም በቆሎ አብቃይ በሆኑ አካባቢዎች የበቆሎ ማሳ በተምች መጎዳትና የምርት መቀነስ መታየቱ፣ በአንዳንድ አካባቢዎች የደረሰው የጎርፍ ክስተት ጉዳት ማስከተሉ እንዲሁም በድንበር አካባቢ በተፈጠሩ ግጭቶች በርካታ ሰዎች በመፈናቀላቸው መሆኑ ነው የተገለፀው።

በሌላ በኩል ደግሞ የተረጂው ቁጥር በ2009 በጀት አመት የበልግ ጥናት ተለይቶ ከነሀሴ 2009 ዓ.ም እስከ ታህሳስ 2010 ዓ.ም ድረስ የእለት ደራሽ እርዳታ ሲቀርብለት ከነበረው 8 ነጥብ 5 ሚሊየን ተረጂ ቁጥር ጋር ሲነፃፀር በ8 ነጥብ 4 በመቶ ቀንሶ መታየቱ ተነግሯል።

ለዚህ የድርቅና ሌሎች ድንገተኛ አደጋዎች የአስቸኳይ ጊዜ ምላሽ በመስጠት ለመከላከል እንዲቻል መንግስት ብር 5 ሚሊየን በጀት በመመደብ እንቅስቃሴ ላይ መገኘቱን የገለጹት ኮሚሽነር ምትኩ፥ ቀደም ሲል የተከሰተውን ድርቅ በመቋቋም ሂደት የሰብአዊ አጋሮች በቅንጅት ይሰሩ እንደነበር ሁሉ አሁንም በተረጂዎች ላይ የተጋረጠውን የድርቅ ስጋት በመቀልበስ ረገድ ድጋፋቸው እንዳይለይ ጥሪ አስተላልፈዋል።

ይፋ በተደረገው የሰብአዊ ፍላጎት ሰነድ የእለት ደራሽ ምግብ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ጤናና ስርዓተ ምግብ ትምህርት እንዲሁም መጠለያ ቅድሚያ ትኩረት ተሰጥቷቸዋል።

በዚህም ለድርቁ ምላሽ ለመስጠት የሚያስፈልገው 1 ነጥብ 44 ቢሊየን ዶላር ለምግብ፣ ለጤና፣ ለተመጣጠነ ምግብ፣ ለትምህርት እና ለንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት የሚውል ነው።

Leave A Reply

Your email address will not be published.