በመዲናዋ በክረምቱ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ከ900 ሺህ በላይ ወጣቶች ተሰማርተዋል

(ኤፍ ቢ ሲ)- በአዲስ አበባ በዘንድሮው የክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ከ900 ሺህ በላይ ወጣቶች የተለያዩ አገልግሎቶችን በመስጠት ላይ ይገኛሉ።

ወጣቶቹ በዋናነት በትራፊክ ደህንነት እና በማጠናከሪያ ትምህርት በጎ ፍቃድ አገልገሎት ላይ ነው የተሰማሩት።

በከተማዋ የክረምት የማጠናከሪያ ትምህርት በሚሰጥባቸዉ ማዕከላት፥ በጎ ፍቃደኛ ወጣቶች ከ5ኛ ክፍል ጀምሮ ላሉ ተማሪዎች ነጻ የማጠናከሪያ ትምህርት እየሰጡ ነው።

ከ85 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተጠቃሚ እየደረገ የሚገኘው የክረምት የማጠናከሪያ ትምህርትም በ100 ማዕከላት እየተሰጠ ሲሆን፥ ከተለያዩ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ ከ2 ሺህ በላይ መምህራን ተሳታፊ ናቸው።

በእድሉ ተጠቃሚ የሆኑ ተማሪዎችም የማጠናከሪያ ትምህርቱ ለመደበኛው የትምህርት መርሃ ግብር ውጤታቸው አጋዥ መሆኑን ተናግረዋል።

የተማሪዎቹ ወላጆች በበኩላቸው ልጆቻቸው፥ ለቀጣይ የበጋ የትምህርት መርሃ ግብር በቂ ዝግጅት እንዲያደርጉ እንደሚያግዛቸውና ከወጪ እንዳዳናቸውም ነው የተናገሩት።

በጎ ፍቃደኛ ወጣቶች ደግሞ አገልግሎቱን በመስጠታቸው ጊዜያቸውን በአግባቡ ለመጠቀምና እውቀታቸውን ለማዳበር እንደረዳቸው ይናገራሉ።

በከተማዋ ከማጠናከሪያ ትምህርቱ ባለፈም በመንገድ ትራፊክ ደህንነት ከ6 ሺህ በላይ ወጣቶች ስልጠና ወስደው፥ ሰላማዊ የትራፊክ ፍሰት እንዲኖር የማስተናበርና የግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ እየሰሩ ይገኛሉ።

የበጎ ፍቃደኞቹ ተሳትፎ በተለይ በእግረኞች መንገድ አጠቃቀም ላይ ለውጥ እንደፈጠረ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

በአራዳ ክፍለ ከተማ ትራፊክና ቁጥጥር ዲቪዚዮን ሽፍት ሃላፊ ተወካይ ዋና ሳጂን ዳኜ ጥላሁን እንደሚሉት፥ አገልግሎቱ በሰላማዊ የትራፊክ ደህንነቱ ላይ አስተዋጽኦ አድርጓል።

ከአዲስ አበባ ስፖርትና ወጣቶች ቢሮ በተገኘው መረጃ በክረምት በጎ ፍቃድ የተለያየ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የሚሰጡ፥ ከ9 መቶ ሺ በላይ በጎ ፍቃደኞች ተሰማርተዋል።

የበጎ ፍቃደኞቹ አገልግሎት ከ50 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ገንዘብ ለማዳን የሚያስችል እንደሆነም ይገመታል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.