በበጀት ዓመቱ የአገሪቱ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ስራ ስኬታማ ነበር- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

(ኤፍ ቢ ሲ)- ሀገሪቱ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስመንትን ከመሳብ፣ ወደ ውጭ ለሚካሉ ምርቶች ገበያ ከማፈላለግ እና የቱሪስት ፍሰቱ እንዲጨምር ከማድረግ አኳያ ከዘርፍ መስሪያ ቤቶች ጋር በመተባበር በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም ዛሬ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ መንግስት ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲው ስኬታማ እንድትሆን እየሰራ መሆኑንም ገልፀዋል።

በተለያዩ ክፍለ ዓለማት የሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች የሙሉ ጊዜ ስራቸው አድርገው እየሰሩት መሆኑንም ነው ያነሱት።

የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ስኬት መለኪያ ዲፕሎማሲው የሀገሪቱን የልማት ፍላጎት ምን ያህል አግዟል የሚል መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ከዚህ አንፃር በተጠናቀቀው የ2009 በጀት ዓመት 84 ትላልቅ የውጭ ኩባንያዎች በሀገሪቱ ስራ እንዲጀምሩ የተደረገ ሲሆን፥ የካፒታል አቅማቸው እስከ 1 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር የሚደረስ ኩባንያዎች እንደሚገኙ አቶ መለስ አብራርተዋል።

984 አነስተኛ እና መካከለኛ ኩባንያዎች ኢትዮጵያን እንዲጎበኙና የኢንቨስትመንት አዋጭ ጥናት እንዲያካሂዱ መደረጉንም ጠቁመዋል።

በቱርክ፣ ጃፓን፣ ሞሮኮ፣ ብራዚል እና በሌሎች ሀገራት 31 የቢዝነስ ትስሰር መድረኮች መካሄዳቸውን የጠቀሱት ቃል አቀባዩ፥ የሚመለከታቸውን የዘርፍ መስሪያ ቤቶች ያካተተ ሀገራዊ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ የቅንጅት መድረክ ተቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱን አንስተዋል።

ከዚህ ባሻገር 672 የኢትዮጵያ ኩባንያዎች የውጭ የገበያ ትስስር እንደተፈጠረላቸውም ነው የገለፁት።

በበጀት ዓመቱ በተሰራው የዲፕሎማሲ ስራ በህዋ ሳይንስ፣ ህክምና፣ ንፁኅ መጠጥ ውሃ፣ ቡናና ሻይ፣ ቤት ግንባታ እና በሌሎችም ዘርፎች 60 የቴክሎጂ ሽግግርና 236 የቴክኒክና ሙያ ስልጠና እድል መፈጠሩን ተናግረዋል።

ለውጭ ምርት የገበያ እድሎችን በማመቻቸት ረገድ በተሰራው ስራ ከ494 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ እንደተገኘ ነው ያብራሩት።

በሌላ በኩል የኢትዮጵያን ቱሪዝም በማስተዋወቅ ረገድ 55 የቱሪዝም ትርኢቶችና ኤግዚቢሽኖች መዘጋጀታቸው ተነግሯል።

በበጀት ዓመቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ቆንስላ ፅህፈት ቤቶች ባከናወኗቸው ተግባራት ለተለያዩ ፕሮጀክቶች ከ2 ቢሊየን ብር በላይ የሚያስገኙ 21 የልማት ፋይናንስ ምንጮች መገኘታቸውን አቶ መለስ አመላክተዋል።

ከሶማሊያ መንግስት የተውጣጡ የልዑካን አባላት ከኢትዮጵያ የፌደራሊዝም ስርዓት ተሞክሮ ለመውሰድ በሀገሪቱ የተለያዩ ጉብኝቶችን እያደረጉ እንደሚገኙ ገልፀዋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሲወጣም ሆነ ሲነሳ እንዲሁም በቀጣይ በሚሰሩ ስራዎች ላይ በአዲስ አበባ የሚገኙ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላትን የማወያየት ተግባራት መከናወናቸውም ነው የተጠቀሰው።

መንግስት አዋጁን ለማንሳት ያድረገውን ጥረት የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ በማድነቅ ኢትዮጵያ ለሰላምና መረጋጋት የምታደርገውን ጥረት እንደሚደግፉ መግለጻቸውንም አነስተዋል።

ከሰሜን ኮሪያ ጋር በተያያዘ የባንክ ሂሳብ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን የመንግስታቱ ድርጅት በጣለው ማዕቀብ መሰረት ሌሎች ሀገራትም የራሳቸውን እርምጃ እንደሚወስዱ መገንዘብ ያስፈልጋል ብለዋል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.