በቡራዩ በፋብሪካ ላይ በደረሰ የእሳት አደጋ በ13 ሰዎች ላይ የቃጠሎ ጉዳት ደረሰ

(ኤፍ.ቢ.ሲ)- በቡራዩ ከተማ የሚገኝ የምግብ መያዥያ ፕላስቲክ ምርት ለመጀመር በዝግጀት የነበረ አንድ ፋብሪካ ላይ ባጋጠመ የሲሊንደር መፈንዳት 13 ሰዎች የእሳት ቃጠሎ ጉዳት እንደደረሰባቸው ተነገረ።

የቡራዩ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የወንጀልና የፍትህ አሰጣጥ አስተባባሪ ኮማንደር በቃና ሚዴቅሳ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት፥ የእአደጋው ስራ ለመጀመር ኤሌትሪክና ግብዓት በመገጣጠም ላይ የሚገኝ ፋብሪካ ላይ ነው የደረሰው።

ትናት ከቀኑ 10 ሰዓት ከ20 አካባቢ ሰራተቾች በመኪና ላይ የተጫነ እቃና ክብደት ያለው ሲሊንደር በማውረድ ላይ እያሉ ሲሊንደሩ መሬት ላይ ወድቆ መፈንዳቱን ተናግረዋል።

ሲሊንደሩ መፈንዳቱን ተከትሎ ፋብሪካው ላይ ከፍተኛ እሳት በመነሳቱ በፋብሪካው ውስጥ የነበሩ 13 ሰራተኞች ላይ በእሳት መቃጠል አደጋ እንደደረሰባቸው ገልፀዋል።

በዚህ የእሳት አደጋ አካላቸው በእሳት የተቃጠሉ ሰዎች አለርት፣ ጳውሎስ፣ ሚኒሊክ፣ ራስ ደስታና የካቲት ሆስፒታሎች
ህክምና እየተከታተኩ ነው ብለዋል።

በአደጋው የሰው ህይወት እንዳልጠፋ የገለፁት ኮማንደሩ በፋብሪካው ላይ የተነሳው እሳት ለማጥፋት አስቸጋሪ እንደነበር ጠቁመዋል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.