በትግራይ ክልል ሴክተር መስሪያ ቤቶች የፋይናንስ ህግና ስርአትን ተከትለው በመስራት በኩል መሻሻል አሳይተዋል – የክልሉ ዋና ኦዲተር

( ኢዜአ)- ሴክተር መስሪያ ቤቶች የሚመደብላቸውን በጀት የፋይናንስ ህግና ስርአት ተከትለው ለታለመለት አላማ እንዲውል በማድረግ በኩል የተሻለ አፈፃፀም ማሳየታቸውን የትግራይ ክልል ዋና ኦዲተር አስታወቀ፡፡

ዋና ኦዲተሩ ዶክተር ረዳኢ በርኸ ትናንት በሰጡት መግለጫ በክልሉ በበጀት ከሚተዳደሩ 689 ሴክተር መስሪያ ቤቶች መካከል ግማሽ ያህሉ በተጠናቀቀው በጀት አመት የሂሳብ ምርመራ ተደርጎላቸዋል፡፡

የሂሳብ ምርመራ ከተደረገባቸው 333 በበጀት የሚተዳደሩ መስሪያ ቤቶች መካከል 76 በመቶ የሚሆኑት ከተወሰነ የአሰራር ክፍተት በስተቀር የፋይናንስ ህግን ተከተለው የሚሰሩ መሆናቸው ተረጋግጧል፡፡

ቀሪዎቹ 22 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ በሂሳብ አያያዛቸው ላይ ክፍተት የታየባቸው መሆኑን  ተናግረዋል፡፡

ተቋማቱ  የተገኘባቸው ግድፈት በፍጥነት እንዲያስተካክሉ በገደብ የተቀመጠ ጊዜ እንደተሰጣቸውም አስታውቀዋል፡፡

ሰባት በገጠር የሚገኙ ጤና ጣቢያዎችና የመጠጥ ውሀ አገልግሎት ፅህፈት ቤቶች ደግሞ በባለሙያ የታገዘ የሂሳብ  ስርአት ያልተከተሉ በመሆናቸው ኦዲት ለማድረግ ማስቸገሩን ገልፀዋል፡፡

ተቋማቱ በቀጣይ ሙያን መሰረት ያደረገ ስራ እንዲያከናወኑ ባለሙያ እንዲቀጠርላቸው ለሚመለከተው አካል ምክረ ሀሳብ ማቅረባቸውን ገልፀዋል፡፡

በየደረጃው ያሉት የምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴዎች በተለያየ ጊዜ የሚያደርጉት ክትትል ለፋይናንስ አስተዳደሩ መሻሻል የጎላ አስተዋፅኦ ማበርከቱን ዋና ኦዲተሩ ተናግረዋል፡፡

በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በክልሉ 17 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር የወጪና ገቢ ገንዘብ የኦዲት ሽፋን ማግኘቱን ከኃላፊው ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል።

በተያዘው የበጀት ዓመትም ለ415 የመንግስት ተቋማት በጽህፈት ቤቱ ሰራተኞችና  ፈቃድ ባላቸው የግል ኦዲተሮች የሂሳብ ምርመራ ለማካሄድ እቅድ መያዙን ዶክተር ረዳኢ አስረድተዋል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.