በአማራ ክልል ከባህር ዳር ማረሚያ ቤት 283 ታራሚዎች ዛሬ በይቅርታ ተለቀቁ

(ኤፍ ቢ ሲ)- በአማራ ክልል ከባህር ዳር ማረሚያ ቤት 283 ታራሚዎች ዛሬ በይቅርታ መለቀቃቸው ተገለፀ።

የክልሉ መንግስት ከሰሞኑ 2 ሺህ 905 ታራሚዎችን በይቅርታ እንደሚለቅ ማስታወቁን ተከትሎ ነው ማረሚያ ቤቱ ታራሚዎችን የለቀቀው።

ታራሚዎች በተለያዩ ወንጀሎች ውሳኔ ተላልፎባቸው የነበሩ ሲሆን፥ ዝቅተኛ የእርማት ጊዜያቸውን አጠናቀው በስነ-ምግባራቸው አርአያ የሆኑ ስለመሆናቸው በአጣሪ ኮሚቴ ተረጋግጦ መለቀቃቸውን የባህር ዳር ማረሚያ ቤት መምሪያ ሀላፊ ዋና ኢንስፔክተር ሹመት ሞላ ተናግረዋል።

የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት እንደዘገበው፥ ይቅርታ የተደረገላቸው ታራሚዎችም በፈፀሙት ድርጊት ተፀፅተው ከማረሚያ ቤቱ ባገኙት የሙያ መስክ በመሰማራት ህብረተሰቡን ለመካስ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

በቅርቡ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ያካሄደውን ግምገማ ተከትሎ አራቱ የግንባሩ አባል ድርጅቶች ሊቃነ መናብርት በሰጡት መግለጫ ላይ “በፈፀሙት ወንጀል ምክንያት በፍርድ ቤት የተፈረደባቸው ወይም ደግሞ ወንጀል በመፈፀም ድርጊት ተጠርጥረው በአቃቤ ህግ ጉዳያቸው ተይዞ በእስር የሚገኙ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትን ጨምሮ ሌሎች ግለሰቦች የተሻለ ሃገራዊ መግባባት ለመፍጠርና የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት በማሰብ ክሳቸው ተቋርጦ ወይም በምህረት ህግና ህገመንግሥቱ በሚፈቅደው መልኩ ተገቢው ማጣራት ተደርጎ እንዲፈቱ ይደረጋል።” መባሉ ይታወሳል።

ይህን ተከትሎም ባለፈው ሳምንት በአማራ ክልል የ598 ተጠርጣሪዎች ክስ ሲቋረጥ ለ2 ሺህ 905 ታራሚዎች ይቅርታ ተደርጓል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.