በአብየ ግዛት የተሰማራው የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ሃይል ቆይታ ተራዘመ

(ኤፍ ቢ ሲ)- በአብየ ግዛት የተሰማራው የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ሃይል ቆይታ ለተጨማሪ ስድስት ወራት ተራዘመ።

የመንግስታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በስፍራው የሚገኘው የኢትዮጵያ ጊዜያዊ ሰላም አስከባሪ ሃይል ተጨማሪ ስድስት ወራትን እንዲቆይ ወስኗል።

የስፍራውን አጠቃላይ ሁኔታ የሚቆጣጠረውን ሰራዊት የላከችው ኢትዮጵያም ውሳኔውን በመደገፍ ምስጋና አቅርባለች።

ሁለቱ ሱዳኖችም የገቡትን ስምምነት ያከብሩ ዘንድ ጥሪዋን አቅርባለች።

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ተቀዳ አለሙ፥ አሜሪካ የሰላም አስከባሪ ሃይሉ ተልዕኮ እንዲራዘምና የጋራ መግባባት ላይ እንዲደረስ ላደረገችው አስተዋጽኦ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በቀጠናው አካባቢ ያለውን ሁኔታ በአንክሮ ለመከታተል የሰላም አስከባሪ ሃይሉ ቆይታ መራዘም አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።

አምባሳደሩ መላው የፀጥታው ምክር ቤት አባላት ለሰላም አስከባሪ ሃይሉ ቆይታ መራዘም ላደረጉት ድጋፍም አመስግነዋል።

በአብየ ግዛት የተሰማራው ጊዜያዊ ሰላም አስከባሪ ሃይል ከፈረንጆቹ 2011 ጀምሮ በስፍራው ይገኛል።

በኢትዮጵያ ሰራዊት የሚመራው ሰላም አስከባሪ ሃይልም በሁለቱ ሱዳኖች ድንበር አቅራቢያ ያለውን ሁኔታ መከታተልና የአካባቢውን ሰላም የማስከበር ሃላፊነት ተጥሎበታል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.