በአፋር ክልል የሴት ልጅ ግርዛት አሁንም በድብቅ እንደሚፈጸም ተጠቆመ

(ኢዜአ)- በአፋር ክልል የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስቆም ጥረቶች ቢደረጉም በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ግርዛት በድብቅ እየተፈጸመ መሆኑን ክልሉ ሴቶችና ሕጻናት ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ዘሀራ መሀመድ እንደተናገሩት ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የአርብቶአደር ሴቶችን ተጠቃሚነትና ተሳትፎ ለማሳደግ በተከናወኑ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች አበረታች ውጤት ተገኝቷል።

የሴት ልጅ ግርዛትን ጨምሮ ሌሎች ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስቆም ሰፊ የማህበረሰብ ንቅናቄ ከማድረግ ጀምሮ ግርዛትን የሚከለከል የህግ ማዕቀፍ እስከማውጣት ሥራዎች ተከናውነዋል።

ሕብረተሰቡ በሕጉ ላይ ግንዛቤ አንዲኖረው ችግሩ ጎልቶ በሚታይባቸው 11 የክልሉ ወረዳዎች ቢሮው እስከ ቀበሌና ጎጥ ድረስ ወርዶ በየደረጃው የማስተማርና የማህበረሰብ ውይይት አድርጓል።

ይሁንና እነዚህ ወረዳዎችን ጨምሮ በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ዛሬም ግርዛት በድብቅ እየተፈጸመ መሆኑን ተናግረዋል።

በድብቅ የሚፈጸመውን ግርዛት ለመከላከል ቢሮው የሚሰራው ተከታታይ የግንዛብ ማስጨበጫ ሥራዎች ቢኖሩም የድርጊቱን ፈጻሚዎች  አሳልፎ ለህግ ለማቅረብ በሚደረገው ጥረት ውስጥ የሕብረተሰቡ ንቁ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ወይዘሮ ዘሀራ አስታውቀዋል።

የክልሉ ፍትህ ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ፋጡማ መሃመድ በበኩላቸው፣ ቢሮው ግርዛትን ጨምሮ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመከላከል በክልሉ ሁሉም ወረዳዎች ለሕብረተሰቡ የንቃተ ህግ ትምህርትና ለአቃቢ ህጎች የተለያዩ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን ሲሰጥ መቆየቱን ገልጸዋል።

ቢሮው ከሚሰጠው የንቃተህግ ስልጠና በተጨማሪ በዚህ ዓመት በደዌ እና አሚበራ ወረዳዎች የሴት ልጅ ግርዛት ሲፈጽሙ የተገኙ ሁለት ሰዎች በቀላል እስርና በገንዘብ ቅጣት እንዲቀጡ ማድረጉን አመልክተዋል።

እንደ ወይዘሮ ፋጡማ ገለጻ፣ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ከመከላከል አንጻር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት ለመስራት የሚደረገው ጥረት ውስንነቶች አሉበት።

ይህንን ችግር ለመፍታት 13 ከሚሆኑ ባለድርሻ አካላት ጋር ቢሮው በቅንጅት ለመስራት ባለፈው መጋቢት ወር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሞ ወደስራ መገባቱን ተናግረዋል።

በሰመራ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ10ኛ ክፍልተማሪ ፋጡማ እድሪስ በበኩሏ ባለፉት ዓመታት ግርዛትን አስመልክቶ በተከናወኑ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች በህብረተሰቡ የአመለካከት ለውጥ እየተፈጠረ መሆኑን ገልጻለች።

ይሁንና አሁንም ድረስ አንዳንድ ሰዎች ልጆቻቸውን ከማስገረዝ ያልታቀቡ መኖራቸውንና ይህም ሴቶችን በተለይም በወሊድ ወቅት ለከፋ ስቃይ እየዳረገ በመሆኑ ድርጊቱን የሚፈጽሙ ሰዎችን አጋልጣ ለመስጠት መዘጋጀቷን ተናግራለች።

የክልሉ እስልምና ጉዳይ ፕሬዚዳንት ሼህ መሃመድ ደርሳ በበኩላቸው፣ በክልሉ በአስከፊ ሁኔታ ይፈጸም የነበረዉን የሴትልጅ ግርዛት ለማስቆም የሃይማኖት አባቶች ግርዛት ሃይማኖታዊ መሰረት እንደሌለዉ በማስተማር ጉልህ ሚና ሲጫወቱ መቆየታቸውን ጠቁመዋል።

በእዚህም የተወሰነ ለውጥ ቢመጣም አሁንም በየደረጃዉ ከሃይማኖት መሪዎች እስከ ፖለቲካ አመራሩ ድረስ ግርዛትን በተመለከተ የግንዛቤ ልዩነት መኖር የሚፈለገው ውጤት እንዳይመጣ አድርጓል ብለዋል፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.