በእነ ኢንጂነር ፍቃደ ሀይሌ መዝገብ 3 ተከሳሾችና 7 የስኳር ኮርፖሬሽን ተከሳሾች ማሪሚያ ቤት እንዲወርዱ ታዘዘ

(ኤፍ.ቢ.ሲ)- በአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን የቀድሞ ስራ አስኪያጅ በእነ ኢንጂነር ፍቃደ ሃይሌ መዝገብ 3 ተከሳሾችና የሰኳር ኮርፔሬሽን የአገዳ ልማትና የፋብሪካ ግንበታ ምክትል ዋና ዳይሬክተር እነ አቶ አበበ ተስፋዬን ጨምሮ 7 ተከሳሾች ማሪሚያ ቤት እንዲወርዱ ታዘዘ።

ተከሳሾቹ ላይ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ክስ የመሰረተ ሲሆን፥ ክሱ በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ መድብ 2ኛ ተረኛ የወንጀል ችሎት ተነቦ ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል።

በዛሬው እለት በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ መድብ 2ኛ ተረኛ የወንጀል ችሎት ክስ የቀረበባቸው የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን የቀድሞ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ፍቃደ ሃይሌ መዝገብ ያሉ 5 ተከሳሾች ናቸው።

የአቃቤ ህግ ክስ እንደሚያመለክተው፥በሌላ ወንጀል ማረሚያ ቤት የሚገኙት 4ኛ ተከሳሽ ሚስተር ሚናሼ እና ካልታየዙት 5ኛ ተከሳሽ ኢንጂነር ሙሉጌታ ሀጎስ ጋር በመመሳጠር ባለስልጣኑ በግንቦት ወር 2005 ዓ.ም ከማእድን ሚኒስቴር፣ መገናኛ ለም ሆቴል ለሚያስገነባው የመንገድ ፕሮጀክት የግዢ አስተዳደር ህግን ባልጠበቀ መልኩ የመያዣ ዋስትና ሳይቀርብ ያለ አግባብ ለትድሃር ኮንስትራክሽን ውል በመስጠት ከ132 ሚሊየን ብር በላይ መንግስትን አሳጥተዋል።

በዚህም በአጠቃላይ በዋና ወንጀል አድራጊነት እና በልዩ ተካፋይ የሙስና ወንጀል ክስ ቀርቦባቸዋል።

ክሱ በችሎቱ ቀርቦ የተነበበላቸው ሲሆን፥ ተከሳሾች የቀረበብን አንድ ነጠላ ክስ በመሆኑ ዋስትና ሊፈቀድልን ይገባል ሲሉ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል።

አቃቤ ህግ በበኩሉ የወንጀል ደርጊቱ ከ10 ዓመት በላይ የሚያስቀጣ በመሆኑ ዋስትና ሊፈቀድ አገባም በማለት ተቃውሟል።

የግራ ቀኙን ክርክር ያደመጠው ፍርድ ቤቱም የተከሳሾቹን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ በማድረግ ተከሳሾቹ ወደ አዲስ አበባ ማረሚያ ቤት እንዲወርዱ ትእዛዝ አስተላልፏል።

4ኛ ተከሳሽ ሚስተር ሚናሼ እና በቁጥጥር ስር ያልዋሉት 5ኛ ተከሳሽ ኢንጂነር ሙልጌታ ሀጎስን የፌደራል ፖሊስ በክትትል ይዞ እንዲያቀርብ ለጥቅምት 9 ቀን 2010 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል።

በሌላ ዜና በከሰም እና በተንዳሆ ፕሮጀክት ስራ የኮንትራት ውል በመቀማት እና ላልተገባ ሰው በመስጠት እንዲሁም የመሬት ዝግጅት ኮንትራትን ክፍያን ከፍ አደርጎ በመፈፀም ተጠርጥረው የነበሩት የስኳር ኮርፖሬሽን የአገዳ ልማት እና የፋብሪካ ግንባታ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አበበ ተስፋዬን ጨምሮ 7 ተከሳሾች ላይ ክስ ቀርቦባቸዋል።

የአቃቤ ህግ መዝገብ እንደሚያመለክተው ተከሳሾቹ ላይ በዋና ወንጀል አድራጊነት እና በልዩ ተካፋይ የሙስና ወንጀል ነው ክስ የቀረበባቸው።

ክሱ በችሎቱ ቀርቦ የተነበበ ሲሆን፥ ተከሳሾቹ የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው ለፍረድ ቤቱ ጠይቀዋል።

አቃቤ ህግ በበኩሉ የወንጀል ደርጊቱ እስከ 25 ዓመት የሚያስቀጣ በመሆኑ ዋስትና ሊፈቀድላቸው አይገባም ሲል ተቃውሟል።

የሁለቱን ወገን ክርክር የተከታተለው ፍርድ ቤቱ የዋስትና ጥያቄውን ወድቅ በማድረግ ወደ አዲስ አበባ ማረሚያ ቤት እንዲወርዱ አዟል።

ለጥቅምት 8 ቀን 2010 ተለዋጭ ቀጠሮ የሰጠው ፍርድ ቤቱ፥ በሌላ መዝገብ ምርመራቸው የተካተተው የስኳር ኮርፖሬሽን የአገዳ ልማት እና የፋብሪካ ግንባታ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አበበ ተስፋዬ ጉዳይ ባለበት እንዲቀጥል አዟል።

በኦሞ ኩራዝ ቁጥር አምሰት የፕሮጀክት ሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ምርመራ እየተደረገባቸው ላሉ የጄ.ጄ.አይ.ሲ የተባለ የቻይና ኩባንያ ስራ እሰኪያጅ ሚስተር ዢዋን እና የእነ መስል መላኩ የ7 ተጠርጣሪዎች ምርመራ ተጠናቆ ፖሊስ መዝገቡን ለአቃቤ ህግ ማስረከቡን አስታውቋል።
አቃቤ ህግ ለክስ መመስረቻ ጊዜ 15 ቀን የጠየቀ ቢሆንም፤ ፍርድ ቤቱ የ8 ቀን የክስ መመስረቻ ጊዜ በመስጠት ለመስከረም 11 ቀን 2009 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

እንዲሁም መርማሪ ፖሊስ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የቀድሞ ዋና ዳይሬክተር በእነ አቶ ዛይድ ወልደገብሬል መዝገብ ያሉ 12 ተጠርጣሪዎች እና በስኳር ኮርፖሬሽን በሌላ መዝገብ የሚገኙ 14 ተጠርጣሪዎች ምርመራ አጠናቆ ለአቃቤ ህግ ማስረከቡን ለፍርድ ቤቱ ገልጿል።

አቃቤ ህግ ለክስ መመስረቻ ለጠየቀው የክስ መመስረቻ ጊዜም ፍርድ ቤቱ የ9 ቀን በመስጠት ለመስከረም 12 ቀን 2010 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.