በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች ከወሰን ጋር ተያይዞ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት የፌደራል መንግስት ከክልሎቹ ጋር በጋራ እየሰራ መሆኑን ገለፀ

(ኤፍ.ቢ.ሲ)- የፌደራል መንግስት በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች ከወሰን ጋር በተያያዘ ያለውን ችግር ለመፍታት ከክልሎቹ አመራሮች ጋር በጋራ በመሆን ለመፍታት እየሰራ መሆኑን ገለፀ።

የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ዶክተር ነገሪ ሌንጮ እንደገለፁት፥ በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች ከወሰን ጋር ተያይዞ የነበሩ ችግሮችን ለመፍታት ክልሎቹ የጋራ ስምምነት ላይ ደርሰው ችግሩም እየተፈታ ባለበት ወቅት ትናንት በተፈጠረ ግጭት በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል።

የፌደራል መንግስት ከክልሎቹ አመራር ጋር በጋራ በመሆን ችግሩን ለመፍታት እየሰራ ሲሆን፥ በአሁኑ ወቅትም የሀገር መከላከያ ሰራዊት በአካባቢው ያሉ ታጣቂ ሀሎችን ትጥቅ የማስፈታት ስራ እያከናወነ ነው ብለዋል።

የፌደራል ፖሊስም በሰዎች ላይ ጉዳት ያደረሱትን ሀይሎች የማጣራትና በቁጥጥር ስር የማዋል ስራዎችን እያከናወነ መሆኑንም ነው የገለፁት።

የፌደራል ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንም በቦታው በመገኘት በዜጎች ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የማጣራት ስራ እንዲሰራ ትእዛዝ መሰጠቱን አመልክተዋል።

በግጭቱ ምክንያት በጅጅጋና አወዳይ ከተማ አካባቢ የሚኖሩ 600 የሚሆኑ የሁለቱም ክልል ነዋሪዎች ተፈናቅለው በሀረር ከተማ ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን ሀላፊ ሚኒስትሩ በመግለጫቸው አመልክተዋል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.