በወባ በሽታ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር 60 በመቶ መቀነሱን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቀ

(ኢቢሲ)- በየዓመቱ ሚያዚያ 17 ቀን የሚከበረውን የአለም የወባ ቀን አስመልክቶ ሚኒስቴሩ ትናንት እንዳስታወቀው የወባ በሽታን ጨርሶ ለማጥፋት የሁሉም ህብረተሰብ ሚና ወሳኝ ነው።
75 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ክፍል አካባቢ ለወባ በሽታ መከሰት ምቹ መሆኑና  ለበሽታው ተጋላጭ የሆነው 60 በመቶ ህዝብ በበሽታው  እንዳይጠቃ አስፈላጊው ስራ አየተሰራ መሆኑን በሚኒስቴሩ  የወባ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ኬዝ ቲም አስተባባሪ ወ/ሮ ሕይወት ሰለሞን ተናግረዋል።

እስካሁን በተሰሩ ስራዎች የወባ በሽታው ስርጭቱ ከ1.3 በመቶ ወደ 0.5 በመቶ መውረዱንንም ነው አስተባባሪዋ  ያመለከቱት።

በወባ የሚያዙ ህሙማን ቁጥር በ50 በመቶ እንዲሁም በበሽታው የሚሞቱ ሰዎች ቁጥርም በ60 በመቶ መቀነሱንም ገልፀዋል።

በቀጣይም ወባን ለመከላከልና ለመቆጣጠር  እንዲሁም  ጨርሶ ለማስወገድ እንዲቻል የተለያዩ ስልቶች ተነድፈው እየተተገበሩ መሆናቸውን ያስታወቁት ወ/ሮ ህይወት ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል።

ዘንድሮ በሀገራችን ለ10ኛ ጊዜ ‹‹ወባን በጋራ ጨርሶ እናስወግድ›› በሚል መሪ ቃል በጋምቤላ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በጋምቤላ ከተማ የፊታችን ሚያዚያ 17፣ 2009  እንደሚከበር ሚኒስቴሩ  አስታውቋል፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.