ኢትዮጵያ የሁሉም መሆን ካቃታት የማንም አትሆንም

(Nahusenai) – ኢቢሲን ስንተቸው የነበረው ብዝሀነትን (Diversity) አያከብርም እያልን ነበር። ብዝሀነት ደግሞ የሀሳብም ነው። ጉልበት ስላለህ ብቻ የኔን ሀሳብ ብቻ ያስተጋባ ማለት ተቛሙን የኔ የፕሮፖጋንዳ ማሽን ይሁን ማለት ነው። ቴዲ አፍሮ በራሱ መንገድ ለዚህ ሀገር የሚጨነቅ ልጅ ነው። እዉነት ኢቢሲ ቴዲ አፍሮን እንደለመደው ሳይጎማምድ ካቀረበው ኢቢሲን በሂወቴ ሰጥቼው የማላውቅ ቦታ እሰጠዋለሁ። የግድ እንደኔ ሁን የሚል ሰገጤነት ነው ሀገሬን የጭቆና ማእከል ያደረጋት። የኔ ሀሳብ መደመጥ አለበት ብየ እንደማስበው ሁሉ የሌላዉም ሀሳብ የመደመጥ መብት እንዳለው መርሳት የለብንም ( ማወቅ ግድ ይለናል)።
.

አገሪትዋ የሁሉም ከሆነች የሁሉም ድምፅ መሰማት አለበት። ከኔ ዉጪ ወደ ዉጪ የሚል አምባገነንነት ግን የሌለ ድድብና ነው። ስልጣን ስለያዝክ አሁን የመናገር መብት አለኝ እምትል ከሆነ ግን ስልጣን ይቀያየራልና: ነገ አንተ የመናገር ዋስትና እንደለሌለህ እወቅ። ከህግ በታች ሁሉም እኩል ነው ሲባል የሀገሪትዋ ሀብቶች ለሁሉም እኩል ተደራሽ መሆን አለባቸው ማለት ነው። ኢቢሲ ቴዲን ማቅረቡ ሊያስመስግነው ይገባል። ነገም ስለ ኢህአዴግ ስብሰባ እንደሚዘግበው ሁሉ ስለ መድረክ፣ዓረና፣ ኦፌኮ፣ ኢዴፓና፣ ሰማያዊና ሌሎች ይዘግባል ብለን ተስፋ እንድናደርግ ያደርገናል። ፓርቲ፣ መንግስት እና ሀገር የተባሉ መዋቅሮች ለይቶ ይሰራል ብለን ተስፋ እንድናሳድር ያደርገናል።
.

ከ አንድ ተረክ እና ከ ግላጭ ዉገና ተላቆ የሀሳብ ብዝሃነትን ማክበር ቢጀምር ኢቢሲን የልደት ቀኑ አንድ ብለን እንጀምራለን።ከንጉሱ ዘመን ጀምሮ እስካሁን የ መንግስት አሽቃባጭ አቃጣሪ ጣብያ መሆኑ አንርሳ። ስጋቴ የቴዲንም ኢንተርቪው ቆራርጦ ለማቅረብ እንዳይሞክር ነው። በዚህ ግዙፍ ሀገር ያሉት የተለያዩ ሀሳቦች በእኩል መንፀባረቅ ሲችሉ ነው ኢቢሲ በእዉነትም የብዝሀነት ድምፅ ነኝ ማለት የሚችለው። ቴዲ አፍሮ ኢቢሲን አምኖ ቃለ መጠይቅ መስጠቱ በራሱ ጀግና ያስብለዋል።
.
አንድ ነገር ልጨምር:
.

ቴዲ ስለ ሚኒሊክ፣ ቴዎድሮስ፣ ሀይለስላሴና የ አፅያዊ ስርዓቱና ሰዎች መዝፈኑ ግፈኛን እንደ ማበራታት፣ በህዝቦች ቁስል ላይ እንጨት እንደመስደድ አድርጋቹህ ለምትመለከቱት አንድ ነገር ልበላቹህ። የትኛዉም ሀገር፣ እደግመዋለሁ፣ የትኛዉም ሀገር ፈንድሻ እየተበተነና ቄጤማ እየተጎዘጎዘ አልተሰራም። በቡና ሴሪሞኒ የተገነባ ሀገር የለም።ካለ ጦርነትና ፍጅት የተገነባ ሀገር የለም።
.

ዝምብለህ አትዉቀስ፤ ቴድሮስን፣ የዉሀንስን፣ ምኒልክን፣ እያሱን፣ ዘዉዲቱንና ሀይለስላሴን ከመዉቀስ በፊት:
.
አንድ፥ ሌሎች ሀገሮች እንዴት ተሰሩ ብለህ ጠይቅ::
.
ሁለት፥ ምን ያህል የነግስታቱ ታሪክ በቲቪ፣ ግምገማና ፕሮፖጋንዳ ከሚነገረኝ በላይ መርምርያለሁ? ብለህ ጠይቅ።
.

ከዛ

ከስህተታቸዉና ከስኬታቸው ተምረህ አጠገብህ ያለውን መሰሪ ታገል፤ መቃብር ቆፍረህ አስክሬን አዉጥተህ የምትገድለው ንጉስ የለም። በስሜት ተነድተህ ንጉስ እገሌ የተባለ ያንተ የግልህ ንብረት ወይም የግልህ ጠላት እሚመስልህ ጥርብ ካለህም ሂድና ስለዛ ንጉስ አንድ ሁለት ገፅ አንብብ፤ ታላቁን ሰው እንዴት አንሰህ ልታሳንሰው ሞክረህ እንደነበር ይገባሀል።
.
እናማ
.

ምንም ነገር ጠብ እሚል ነገር ሳትሰራ ሂወታቸዉን ለሀገራቸው ስለገበሩ ጀግኖች ፈራጅ ሁነህ “አርበኛ ሙድ” አትጫወት፤ ልክህን እወቅ። ካንተ የተለየ ሀሳብ ሲቀርብ ባትቀበለዉም፣ መብቱ እንደሆነ እመን። ይቺ ሀገር ያንድ ሀሳብ ወይም አመለካከት ሀገር አይደለችም። ብዝሀነት ከመዝሙር ባለፈ መንገድ ከገባህ የማይጥምህ ሀሳብ የመቅረብ መብት እንዳለው ማመን አለብህ፤ በኢቢሲ ባይሆንም ባታምንም ይቀርባል።
.

ኢቢሲ ቴዲን ማቅረቡ ቢገርመኝም፣ ቴዶ ኢቢሲን አምኖ መቅረቡ ደግሞ በጣም ገርሞኛል። ቀርበን አይተነዋል፣ ከ እና ፈ’ን ቀያይሮ ‘ጉድ’ እሚሰራ ተቛም ነው።ቴዲ በ ኢቢሲ ስለቀረበ ፌዴራሊዝም ወይም ብዝሀነት አይናድም (ከተናደም አልነበረም ማለት ነው)፣ ይልቁንስ የሀሳብ ብዝሀነት ተከበረ ማለት ነው።

ፈረንሳዊው ቮልቴክ (Voltaire) በ17ኛው ክፈለ ዘመን “እምትናገረው ነገር ባልቀበለዉም፣ የመናገር መብትህ እንዲከበር ግን እስከ ሞት ድረስ እታገልልሀለሁ” ቢልም አሁንም አንዳንድ ሰዎች እኛን ያልመሰለ የቲቪ ሽፋን ማግኘት የለበትም እያሉ ነው።
.
እኔ ደግሞ እላለሁ
.
ኢትዮጵያ የሁሉም መሆን ካቃታት የማንም አትሆንም።

2 Comments
  1. Henok says

    ሀገርን አሳልፎ ለባዕዶች መስጠት ስህተት ሳይሆን በሞት የሚያስቀጣ ክህደት ነው፡፡ ምንሊክ በዚህ ምድር የተፈጠረ የመጀመርያው ካሀዲ ንጉስ ነው፣ ሰሜን ኢትዮጵያን ቆርጦ ለአውረጳዊቷ ጣልያን አሳልፎ የሰጠ፡፡ ይህ በአብሲንያን የ3000 ዓመታት ሥርዓተ ባህል ያልታየ በምንሊክ የተፈፀመ ክህደት ነው፡፡ ምንሊክ በዘመናት መስዋእትነት የተገነባች ሀገር ቆርሶ ለባዕድ ያስረከበ፣ በኢትዮጵያ ለመጀመርያ ግዜ ዘረኝነትና አድልዎን የተከለ፣ ወራዳ ሰው ነው፡፡ የትግራይን መሬት ግማሹን ለጣልያን ገሚሱን ለአማራ የለጠፈ ወራዳና ፈሪ ያለአዋቂ ሰው ነው፡፡ የሀገሩን ግዛት አሳልፎ በመስጠት ያገኘውን የጦር መሳርያ በመጠቀም በደቡብና በኦሮሞ ሕዝቦችም ከፍተኛ ግፍ ፈጽሟል፡፡ ጀግና ቢሆን ንሮ ጣልያንን ተዋግቶ ያባርር ነበር እንጂ፣ ብረት ስላለው ወገኑን አይጨፈጭፍም ነበር፡፡ በሂወት ባይኖርም በታሪክ ቀንደኛው የኢትዮጵያ ህዝቦች ጠላትና ወራዳ ንጉስ ሁኖ መስፈር አለበት፡፡ አፄ ቴዎድሮስ ጨካኝ ቢኖሩም ዘረኛ ግን አልነበሩም፡፡ አፄ ሀይለስላሴም ጨቋኝና ምንሊክ የተከለውን ቆሻሻና ዘረኛ ሥርዓት ነው ያስቀጠሉት፡፡ ለ30-ዓመቱ የጀብሀ/ሻዕብያ ሀይለሥላሴ/ደርግ ደም መፋሰስ ፣ ለ17-ዓመታት የወያነ ደርግ ደም መፋሰስ፣ መሰረታዊ ምንጩ ምንሊክ ነው፡፡ ስለዚህ ቴዲ አፍሮም ይሁን ሌላ ጠባብ ጽንፈኛ ይህን ሀቅ መደበቅ ስለማይችሉ፣ በኢትዮጵያውያን አሁንም ለወደፊቱም ከባድ ቁጣ፣ ውግዘትና ተቃውሞ ይገጥማቸዋል!

  2. Esrael says

    Hahaha who are you first? Our unity is much stronger than tedy & Ebc…..and also menielk.tewdros,hailseslhse…..etc. no one can fear others,talk is cheap,doesn’t bring change.

Leave A Reply

Your email address will not be published.