በደቡብ ኦሞ ከ12 በላይ ሰዎች መሞታቸው ተገለፀ

(ሪፖርተር)- በደቡብ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን ሰኞ ማታ በተከሰተ ግጭት ከ12 በላይ ሰዎች ሲሞቱ ከ26 የሚበልጡ ሰዎች ደግሞ ጉዳት ደረሰባቸው፡፡

የግጭቱ መነሻ የቦዲ ብሔረሰብ አባል የሆነ ግለሰብ በመኪና ተገጭቷል በሚል ምክንያት ሲሆን፣ የብሔረሰቡ አባላት ያገኟቸውን መኪናዎች በሙሉ ሲያጠቁ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡

በተፈጠረው ግጭት ከተገደሉት ውስጥ ብዙዎቹ በአካባቢው ባሉ የግንባታ ሥራ ተቋራጭ ድርጅቶች ውስጥ በሾፌርነት ሲያገለግሉ የነበሩ እንደሆኑ፣ እንዲሁም ነዋሪነታቸውም ኃይል ውሃ በተባለ ሥፍራ እንደነበረም ለማወቅ ተችሏል፡፡

በግጭቱ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች በሶዶ ክርስቲያን ሆስፒታልና በጂንካ ሆስፒታል የሕክምና ዕርዳታ እየተደረገላቸው እንደሚገኝ የአካባቢው ምንጮች ገልጸዋል፡፡

የደቡብ ክልል የሕዝብ ግንኙነትና የሚዲያ ዳይሬክተር አቶ ሲሳይ በቀለ፣  << የተፈጠረውን ግጭት ሰምተን እየተከታተልነው ነው፣ >> ሲሉ ገልጸዋል፡፡

አካባቢው አሁን እየተረጋጋና ወደ ቀድሞው ሁኔታ እየተመለሰ እንደሆነም አቶ ሲሳይ አክለዋል፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.