በጋምቤላ ክልል በህገወጥ መንገድ መሬት ሸጠዋል የተባሉ አራት ግለሰቦች ተከሰሱ

(ኤፍ.ቢ.ሲ)- በጋምቤላ ክልል በማጃንግ ዞን በህገወጥ መንገድ መሬት በመውረር 20 ሺህ 300 ካሬ ሜትር ይዞታን ሸጠው ተጠቀመዋል ተብለው የተጠረጠሩ አራት ግለሰቦች ክስ ቀረበባቸው።

ተከሳሾቹ የማጃንግ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሬጀስትራር ሀላፊ አቶ ተስፋዬ ዘውዴ፣ የሚጤ ከተማ ማዘጋጃ ቤት የቦታና አስተዳደር ሃላፊ ተወካይ አቶ እምሩ ሃይለሚካኤልን ጨምሮ አራት ግለሰቦች ናቸው።

የክልሉ የስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን አቃቤ ህግ ክስ እንደሚያመላክተው፥ የሚጤ ከተማ ማዘጋጃ ቤት የቦታና አስተዳደር ሃላፊ ተወካይ በ2004 ዓ.ም 300 ሄክታር መሬት የከተማ ይዞታን በሌላ ግለሰብ ስም በመውሰድ በ2008 ዓ.ም ሸጠው ለግላቸው ተጠቅመዋል።

በተመሳሳይ ወቅት የማጃንግ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሬጀስትራር ሀላፊ አቶ ተስፋዬ ዘውዴ፥ የስራ ሃላፊነታቸውን ተጠቅመው በቡና ተክል ይዞታ የሁለት ሰዎች የፍታብሄር ክርክር ላይ ጣልቃ በመግባት ከሌላ ሰው ጋር በመመሳጠር 3ኛ ተከሳሽ መስፍን መንገሻ በጨረታ ይዞታውን እንዲገዛ እገዛ በማደረግ 20 ሺህ ካሬ ሜትር የቡና ተክል ይዞታን በህገወጥ መንገድ እንዲጠቀም ማድረጉ በክሱ ተዘርዝሯል።

በተጨማሪም አራተኛ ተከሳሸ ሳህሉ በዛ የተባለው ግለሰብ ይዞታው በውል ያልተጠቀሰ ሰፊ የሚጤ ከተማ መሬትን በህገወጥ መንገድ ይዞ መገኘቱን በክሱ የጠቀሰው አቃቤ ህግ፥ የሁሉም ወንጀል በተያዘው 2009 ዓ.ም በተደረገ ምርመራ መገኘቱን አመላከቷል።

በአጠቃላይ ተከሳሾቹ ከ20 ሺህ 300 ካሬ ሜትር በላይ ይዞታን ሸጠው በመጠቀም እና ወሮ በመያዝ በፈጸሙት በከባድ እምነት ማጉደል ሙስና ወንጀል ክሰ ቀርቦባቸዋል።

ተከሳሾቹ በጋምቤላ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ወንጀል ችሎት ቀርበው ክሱ የተነበበላቸው ሲሆን፥ ደርጊቱን አልፈጸምንም ብለው የእምነት ክህደት ቃላቸውን ለፍርድ ቤቱ ሰጥተዋል።

ተከሳሾቹ ያቀረቡትን የዋስትና ይፈቀድልን ጥያቄ ፍርድ ቤቱ ውድቅ በማድረግ በክሱ ላይ የተከሳሾቹን መቃወሚያ ለመስማት ለሰኔ 6 ቀን 2009 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.