በጋሞ ጐፋ ዞን ከ35 ሚሊየን ብር በላይ የመንግስትና የህዝብ ሀብት መመዝበሩ በኦዲት ተረጋግጧል

(ኤፍ ቢ ሲ)- በደቡብ ክልል በጋሞ ጐፋ ዞን ከ2002 እስከ 2009 በጀት ዓመት ድረስ በ17 መስሪያ ቤቶች ላይ በተደረገ የኦዲት ምርምራ ከ35 ሚሊየን ብር በላይ የመንግስትና የህዝብ ሀብት መመዝበሩ ተደርሶበታል፡፡

ከተመዘበረው ገንዘብ ውስጥ ከ17 ሚሊየን በላይ የሚሆነው በጤና መምሪያ ውስጥ የተገኘ ጉድለት መሆኑን የዞኑ የፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት መምሪያ ሃላፊ አቶ አብርሃም አልቤኒ ገልጸዋል፡፡

አቶ አብርሃም በህክምና መገልገያ መሳሪያዎች ስርጭት በተፈጠረው ክፍተት፥ በሚሊየን የሚቆጠር ገንዘብ ለግል ጥቅማቸው ያዋሉ ሁለት ግለሰቦች በእስራት መቀጣታቸውን ነው የተናገሩት፡፡

ቀሪው ገንዘብ ደግሞ በየመዋቅሩ በግለሰቦች መመዝበሩን የሚያሳዩ ዝርዝር መረጃዎች አሉን ብለዋል፡፡

በዞኑ በግለሰቦች የተመዘበሩ የህዝብ ሀብትና ንብረቶችን የማስመለስና ሕጋዊ እርምጃ የመውሰድ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙም ጠቅሰዋል፡፡

በጋሞ ጎፋ ዞን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ የሚመራ አስመላሽ ግብረ ሃይል የማስመለስ ስራዎችን በቅንጅት እያከናወነ እንደሚገኝ የምክር ቤቱ ዋና አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ልሳነወርቅ ካሳዬ ገልፀዋል።

እስካሁን በተሰራው ስራ በሙስና ከተመዘበረው ገንዘብ ውስጥ 3 ሚሊየን ያህሉ ተመላሽ ተደርጓል ነው ያሉት።

ሆኖም የተመለሰው ገንዘብ እጅግ አነስተኛ በመሆኑ በ2010 በጀት ዓመት በዞን፣ በወረዳና በከተማ አስተዳደሮች ደረጃ የተዘመበረውን የልማት ገንዘብ የማስመለስ ስራ ለመስራት ማቀዳቸውን ጠቁመዋል፡፡

የዞኑ ዋና አስተዳደር የስነ ምግባር መከታተያ ክፍል ሃላፊ አቶ ግርማ ከተማ በበኩላቸው፥ ለልማት የሚመደብ የመንግስት ሀብት በግለሰቦች እንዳይመዘበር በሁሉም ወረዳዎች፣ ከተማ አስተዳደሮችና በዞን ተቋማት ላይ እየተሰራ ነው ብለዋል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.