ባለስልጣናት ከአገር ውጭ የሚያደርጉት ጉዞ ላይ ቁጥጥር ይደረጋል -ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ

(ኢዜአ)-  የመንግስት ባለስልጣናት ከአገር ውጭ የሚያደርጉት ጉዞና መዳረሻዎች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እንደሚደረግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገለፁ።

ከአገር ውጭ ያላቸው የባንክ አካውንት ላይም ምርመራ እየተደረገ ነው ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒትሩ ትላንት ለአዲሱ ካቢኔ በቀጣይ ጊዜያት እንዴት ውጤታማ ስራ መስራት እንደሚቻል በሰጡት ማብራሪያ ላይ አፅንኦት ከሰጡባቸው ጉዳዮች መካከል ከውጭ ጉዞ ጋር ተያይዞ እየመጣ ያለ ብክነት አንዱ ነው።

በአንድ አመት ከ10 ጊዜ በላይ ውጭ አገር የሚመላለስ ሚኒስትር፣ ሚኒስትር ዴኤታ እና ከዛ በታች ያሉ ግለሰቦች መኖራቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል።

ብዙም አስፈላጊ ላልሆኑ ጉዳዮች ወደ ውጭ አገር የሚመላለሱና ከሚሄዱበት አገር በተጨማሪ ሌላ አገር ጎራ የሚሉት ባለስልጣናት በርካታ መሆናቸውን በመግለጽም የሚሄዱበት ምክንያትና መዳረሻቸው ላይ ጥብቅ ክትትል ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

ከዚህም ሌላ የአገሪቱ ባለስልጣናት ውጭ አገር ያላቸው የባንክ አካውንት ላይ ጥናት እየተደረገ መሆኑንና ሲጠናቀቅም የተገኘው ውጤት ለህዝብ ይፋ እንደሚደረግ ገልጸዋል።

ለዚህም የተለያዩ አገራት ትብብር እያደረጉ መሆኑን ነው የተናገሩት።

የውጭ ጉዞ አያስፈልግም የሚል እሳቤም እንዳይያዝ ኃላፊዎቹ ማቻቻልና ብክነትን በሚቀንስ መልኩ አመጣጥኖ መሰማራት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.