ብልሹ አሰራር በፈፀሙ ሰራተኞች ላይ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን የኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ

(ኤፍ.ቢ.ሲ):- የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የደምበኞችን መጉላላት ለማስቀረት ብልሹ አሰራር የፈጸሙ ሰራተኞችን ከስራ እስከማሰናበት የደረሰ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን አስታወቀ።

በሀገራቱ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ደንበኞች የሆኑት ከ25 አሰከ 30 በመቶ የህብረተሰብ ክፍል ብቻ እንደሆኑ መረጃዎች ያመለክታሉ።

ይህ አሃዝ በሀገሪቱ ከሚኖረው የህዝብ ብዛት አንፃር ሲመዘን ዝቅተኛ ቢሆንም በዘርፉ ቅሬታ ሲቀርብ መስማት የተለመደ ነው።

ለዚህም የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ፍላጎት እና የሀይል አለመመጣጠን የዘርፉ ተገዳሮቶች እንደሆኑ የሚገለፅ ሲሆን፥ ቅሬታዎቹ በአገልግሎት አሰጣጥ ወቅት ከሚታዩ ብልሹ አሰራሮች ጋር ተያይዞ ይቀርባሉ።

የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች የኤሌክትሪክ ብልሽት እና የሀይል መቆራረጥ ሲያጋጥማቸው በአንዳአንድ ሰራተኞች በጎን ክፍያ እንደሚጠየቁ ይነገራል።

ይህም አገልግሎቱን ፈልገው እና ክፍያ ፈጽመው ለረጅም አመታት የሚጠባበቁ ተገልጋዮች ደጅ እንዲጠኑ እና ፍትሀዊ አገልግሎት እንዳያገኙ በማድረግ አፋጣኝ ምላሽ እንዳያገኙ ያደረጋል ተብሏል።

ስለሆነም የኢትዮጵያ ኤሌትሪክ አገልግሎት ከህብረተሰቡ የሚነሱትን ቅሬታዎች ለመፍታት የሚያስችል የተቀናጀ የሙስና እና ብልሹ አሰራር መከላከያ ስትራቴጂ በመንደፍ ወደ ስራ ገብቷል።

የአገልግሎቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ጎሳዬ መንግስቴ፥ የኪራይ ሰብሳቢነት ችግር ከግለሰብ ባህሪ ጋር የሚያያዝ በመሆኑ በግለሰብ ደረጃ የአመለካከት ለውጥ ለማምጣት ሶስት ስትራቴጂዎችን በመንደፍ ወደ ተግባር መገባቱን ተናግረዋል።

ህብረተሰቡ አገልግሎቱን በፍትሃዊነት ማግኘት እንዳለበት ስለሚታመን በመላ ሀገሪቱ የቅድመ መከላከል ስራዎች ከመስራት ባሻገር ለብልሹ አሰራር የሚያጋልጡ ሁኔታዎችን የመለየት ስራ መከናወኑን ዋና ስራ አስፈጻሚው አስታውቀዋል።

የአገልግሎቱ የ”ቪጂላንስ” ስራ አስፈጻሚ አቶ ኪሮስ ሀዱሽ በበኩላቸው፥ ችግሩን ከስረ መስረቱ ለመቅረፍ ማስተማርን ጨምሮ ድጋፍ እና ክትትል ከማድረግ ባለፈ ድንገተኛ ፍተሻ በማድረግም ብዙ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

የኤሌክትሪከ መቆራረጥ፣ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር እና የሀይል አቅርቦት በህብረተሰብ ከሚነሱት ጥያቄዎች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው ብለዋል።

በተቋሙ ሰራተኞች በኩል ከሚታዩ ግድፈቶች መካከል ያልተፈቀደ ቆጣሪ መለጠፍ፣ ያለ ቅደም ተከተል ማስተናገድ እና ከትልልቅ ተቋማት ጋር መደራደር መሆናቸውን ያነሱት አቶ ኪሮስ፥ ችግሮችን ለመቅረፍ በውስጥ ከሚደርገው ቁጥጥር በተጓዳኝ ከተገልጋዩ የሚሰጠውን ጥቆማ እና ቅሬታ በመቀበል የማጣራት ስራ እንደተከናወነ ተናግራዋል።

በዚህም ባለፍት ሶስት አመታት 45 ሰራተኞች ሲሰናበቱ ሌሎች 206 ሰራተኞች ደግሞ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ፣ እስከ ሶስት ወር የሚደርስ የደመወዝ ቅጣት፣ ደረጃ ዝቅ ማድረግ እና ለሁለት አመት ለደረጃ እድገት እንዳይወዳደር በማድረግ ቅጣቱ ተፈፃሚ እንደሆነባቸው ታውቋል።

በተጨማሪም በተያዘው አመት ተቋሙ የፀረ ሙስና ትግሉን በማጠናከር በቅሬታ እና በጥቆማ የደረሰውን የ69 ሰዎች የስነምግባር ችግር እየመረመረ ይገኛል።

ከነዚህም ውስጥ 25ቱ ጉዳያቸው ተጣርቶ የተለያዩ ቅጣቶች ሲተላለፉባቸው 26ቱ ጥፋተኛ መሆናቸው ተረጋግጦ ውሳኔ እንዲሰጥ ለበላይ አካል ተላልፏል ተብሏል።

አራቱ ለፌዴራል ውንጀል ምርምራ የተላለፈ ሲሆን፥ ሁለቱ ደግሞ በፍርድ ቤት ክስ ተመስርቶባቸዋል።

ቀሪዎቹ ማስረጃ ያልተገኘባቸው እና በመጣራት ሂደት የሚገኙ መሆናቸው ነው የተገለጸው።

በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ ተቋሙ ከሚያደርገው እንቅስቃሴ ጎን ለጎን የህብረተሰቡ ሚና ከፍ ያለ መሆኑን ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ጎሳዬ መንግስቴ አስታውቀዋል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.