ብዙም አንድም ነን

(በኡስማን ሰይድ) – ኢትዮጵያዊ ማንነትን በተመለከተ የፖለቲካ ልሒቃንም ሆኑ መላው ህዝብ የሚግባባበት አገራዊ ማንነት አለ ለማለት አያስደፈርም፡፡ ብዙሃን ልሒቃን በኢትዮጵያዊ ማንነት ዙሪያ እንደ አጀንዳ ለመነጋገርም ትንፋሽ አግኝተው የሚያውቁ አይመስልም፡፡ ሁሉም በየራሳቸው ከሚያራምዱት ፖለቲካ ጋር ለውሰው ያቀርቡታል፡፡ ለረጅም ዘመን በዓለም ዙሪያም የተሰራበት የአገር ግንባታ ስርዓት ወጥ አገራዊ ማንነትን (Homogeneous identity) በማስረፅ ላይ ያተኮረ ነበርና አንድ ህዝብ፤ አንድ አገር፤ አንድ ሃይማኖት የሚል መርህ በዓለም ዙሪያ የነበሩ የዘውድ አገዛዞች ሁሉ መመሪያ ነበር፡፡

ዘውዱን የሚመሩ መሳፍንት ሁሉ የነሱን የማንነት መለያዎች በውርርስ አገራዊ ማንነት ለማድረግ ሰርተውበታል፡፡ በኢትዮያም ይህ አስተሳሰብ የዘውድ አገዛዝን ተከትለው የኖሩ ነገስታት ሁሉ ሲከተሉት የኖረ ነው፡፡ አገር ብዙ ማንነቶች ያሏቸው ህዝቦችም ሊኖሩባት የምትችል ስለመሆኗ ማሰብና እውቅና መስጠት አይፈልጉም፡፡ የተለያዩ ህዝቦች የጋራ መለያ ማንነት ብቻ ሳይሆን የግል መለያም ያላቸው ስለመሆኑ በመረዳት ለግልም ሆነ ለጋራ ባህሪያት እና መለያዎች ትኩረት አይሰጥም፡፡ የህዝቦችን የጋራ መለያ እንጂ ልዩነታቸውን ማንሳት አገር መለያየት ነው፤ አገር መበተን ነው የሚል እምነት መኖሩ የፈጠረው ነው፡፡ የአገር አንድነት በወጥ መለያዎች የሚመጣ እንጂ ልዩነትን እውቅና መስጠትና የህዝቦች የግል ማንነቶች እንዲዳብሩ ማድረግ የአገር አንድነት ስጋት ነው የሚለው አተያይ የግል ማንነቴን እውቅና የተነፈገው ልሒቅ ሳይቀር ተቀብሎት የኖረ ነው፡፡ አገራዊ ማንነት ማለት በገዢ ኃይሉ ተቀባይነት ያገኙትን መለያዎችና እሴቶች መውረስ ተደርጎ ሲታሰብ የኖረ ነው፡፡

የፖለቲካ ትግሎችም ቢደረጉ ብዝሃነትን ለማስተናገድ የህዝቦችን የማንነት እኩልነት ለማምጣት ሳይሆን ከማንነት ውጪ ያሉ አጀንዳዎችን በማንገብ ነው፡፡ የህዝቦችን ብሔራዊ ፍላጎቶች አንስቶ መታገል የአገር አንድነት ስጋት ተደርጎ ስለሚታይ ነው፡፡ ለግል ማንነቶች መከበርና እውቅና ዲሞክራሲያዊ ብሔራዊ ትግል አድርጎ እንደ አገር የግል እሴቶች እኩል እውቅና አግኝተው ሁሉም በአንድነት የሚቆረቆሩላቸውን የጋራ አገራዊ መለያዎች ለይቶ ለሁሉም እኩል እንዲያሳድጋቸው ማድረግ ስለመቻሉ ማሰብ ከባድ ሆኖ ኖሯል፡፡

 

የአንድ ወገን ኢትዮጵያዊ ማንነት

ለረጅም ዘመናት የኢትዮጵያ ማንነት መለያ ተደርጎ ይታሰብ የነበረው በአብዛኛው የሰሜን ኢትዮጵያ ህዝቦች እሴቶችና መለያዎች ናቸው፡፡ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን አንፃር ሲታይ የትግራይና አማራ ህዝብ እሴቶችና መለያዎች በገዢ መደቡ ተቀባይነት የነበራቸው ወይም የገዢ መደቡ መለያ የነበሩ ናቸው፡፡ እኔ የሰሜን ህዝቦች ማንነት እለዋለሁ፤ ሌላው የደገኛ/የሐበሻ/ ይለዋል፤ በአንድ በኩል ደግሞ የአማራ ማንነት (ገዢ መደብ) ይባላል፡፡ የትግራይና የአማራ ህዝቦች ከሌሎች ህዝቦች ይልቅ ሃይማኖታቸው፤ መጠሪያ ስማቸው፤ ታሪካቸው፤ አለባበሳቸውና ሌሎች ጥቃቅን እሴቶቻቸው የመንግስታት (የገዢ መደቦች) መለያዎች ስለነበሩ የአገራዊ ማንነት መለያ ተደርጎ ይወሰድ ነበረ፡፡ የአማራ ህዝብ ደግሞ ከትግራይም ይልቅ ቋንቋው የመንግስታት ቋንቋ ሆኖ አገራዊ ቋንቋ የመሆን እድል አግኝቷል፡፡ እነዚህን የመሰሉ ጉዳዮች ሲታይ የሰሜን ኢትዮጵያ ታሪክና ማንነት፤ የኢትዮጵያ ታሪክና ማንነት መገለጫ ሆኖ እንዲታይ ተደርጓል፡፡ የአንድ ወገን ማንነት የመላው ኢትዮጵያዊ ማንነት መገለጫ ሆኖ መኖሩን ያሳያል፡፡ ኢትዮጵያዊ ማንነትን የአንድ ወገን አድርጎት የኖረው የሌሎች ህዝቦችን ማንነት እውቅና የማይሰጥ በአማራውና ትግሬው እሴቶች የሚገለፅ ሆኖ በመኖሩ ነው፡፡ ሌላው ኢትዮጵያዊ ግን እነዚህን የመሰሉ እሴቶቹን ይዞ ከመቅረብ ይልቅ የራሱን ትቶ የሰሜን ኢትዮጵያ ማንነትን መላበስ የግድ ይለው ነበር፡፡ የ1960ዎቹ የተማሪዎች ንቅናቄ ባቀጣጠለው የብሔሮች እኩልነት መብት ጥያቄ ውስጥ ፋና ወጊ ተሟጋቾች ይደርስባቸው የነበረው ተቃውሞ ምንጩ የብሔሮች እኩልነት መብት ጥያቄ የአማራውንና የትግሬውን መብቶች የሚደግፍ ነው የሚል እንደነበር ይታወሳል፡፡ በቁንፅል ምሳሌ ሲታይ በወቅቱ ኢትዮጵያ የምትገለፅበት ምልክት የአማራን ጥልፍ ቀሚስ ለብሳ ፀጉሯን የትግሬ ሹርባ የተሰራች ሴት ተደርጋ ትታይ የነበረበት በመሆኑ ያንን የበላይነት የሚያጠፋ ከመሰላቸው ተማሪዎች የመጣ ትችት ነበር ማለት ይቻላል፡፡

እነ ዋለልኝ መኮንንና ጥላሁን ግዛው ግን የብሔሮች እኩልነት መብት ጥያቄን ከራሳቸው ብሔራዊ ማንነት በመነሳት ሳይሆን ከአገሪቱ የተለያዩ ህዝቦች የማንነት ሁኔታ በመነሳት ያነሱት ስለነበር፤ እነሱም የሚጋሩትን የራሳቸውን ማንነት ለማኮሰስ ሳይሆን እንደ አገር የሌላውም የማንነት መብት ሊከበር እንደሚገባው ከማመን ተከራክረዋል፡፡ ዋለልኝ መኮንን ለተነሳው ትችት ምላሽ ሲሰጥ “እኔም እኮ አማራ ነኝ…” ማለቱ ኢትዮጵያዊነት በአንድ ወገን ማንነት የሚገለፅበትን ሁኔታ በመቃወም አገራዊ ማንነት አገራዊ የህዝቦችን ገፅታዎች በእኩል ያስተናገደ እንዲሆን ከመሻት እንደነበር ማሳያ ነው፡፡

የዚያ ዘመን ተማሪዎች የፖለቲካ ትግል ልዩ ባህሪ የበላይነት ከነበረው ማንነት የተነሱ ወጣቶች ያነሱት የብሔሮች እኩልነት ጥያቄ መሆኑ ብቻ ሳይሆን በርዕዮተ ዓለማዊ ትንተናቸውም የማንነት ጥብቅና ትግላቸው በፀረ-ኢምፔራሊዝም አረዳዳቸው ውስጥ ተካቶ ይተች የነበረ መሆኑም ነው፡፡ በውስጥ ለብሔሮች እኩልነት ብቻ ሳይሆን ለውጪ የባህል ወረራ እንዳይጋለጥም ይታገሉ የነበሩ መሆናቸው ልዩ ነው፡፡ በውጫዊ ገፅታ እንኳ ኢምፔራሊዝምን አንፀባርቀሃል/ሻል/ የሚለውን ትችት ልብ ይሏል፡፡ ዛሬ ምንም ያህል ኒዮ-ሊበራሊዝም ቢወገዝ በሰዎች አኳኋን ከማንነት አኳያ ኒዮ-ሊበራሊዝምን አንፀበርቀሃል/ሻል/ ብሎ ለመተቸት የዘመኑ የነፃነት መብትና ዲሞክራሲ የሚፈቅዱ አይመስለኝም፡፡ ሆኖም የሰሜን ኢትዮጵያ ህዝቦችም ቢሆኑ እሴቶቻቸውንና ማንነታቸውን ገዢ መደቡ ወርሶላቸው ነበር ማለት ልዩ ተጠቃሚ ነበሩ ማለት አይደለም፡፡ ከራሳቸው በተነሱ መሳፍንት ሲመዘበሩ የኖሩ መሆናቸው ሐቅ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ግን በኢትዮጵያ በግል ማንነት ዙሪያ የመደራጀት እና የግል መለያን የማዳበር መብት እንደ ህዝብ ሁሉም ተነፍጎት የኖረ ነው፡፡

የገዢ መደቡም ቢሆን የኔ ከሚላቸው ማንነቶችና እሴቶች ውጪ ያሉትን ማንነቶች ከማጣጣልና ከማግለል አልፎ የኔ ያላቸውን እሴቶች እንኳ ለማዳበር የሚያስችሉ ስራዎችን ለመስራት አልቻለም፡፡ የነበረው ጉዳይ ቢታይ የገዢ ኃይል እሴቶች ምንጭ የሆኑት ህዝቦች በተለይ የአማራ ልሒቃን (ሰፊው የአማራ አርሶ አደር ሌሎች ህዝቦችና ማንነቶች ስለመኖራቸውም የሚያውቅበት እድል ነበረው ማለት አይቻልም) ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ይልቅ በማንነቱ አይሸማቀቅም፤ አያፍርም ነበር፡፡ ስሙን ለመቀየር የሚገደድ የትግራይም ሆነ የአማራ ተወላጅ ነበረ ማለት አያስደፍርም፡፡ በዚህ የተነሳ እንደ ገዢ መደቡ ሁሉ እሱን የማይመስለውን ሌላውን ኢትዮጵያዊ ሁሉ የበታች አድርጎ እንዲያስብ፤ የእሱ እሴቶች የአገዛዙ እሴቶች በመሆናቸው የተለየ እንደሆነ እንዲሰማው ሆኖ ተቀርፆ እንዲኖር (ትምክህት) ከመደረግ ያለፈ የኑሮና ኢኮኖሚ ጥቅም ነበረው ማለት በፍፁም አይቻልም፡፡ አንኮበርም ፣ ተንቤንም ምስክር ናቸው፡፡ ሆኖም በአንድ ወገን ማንነት የሚገለፅ ኢትዮጵያዊነት ከዚያው ወገን በተነሱ ተማሪ ወጣቶች በገጠመው ተቃውሞ ተጀምሮ፤ ከዚያው ወገን በተነሱ ታጋዮች ፍፃሜ ቢያገኝም ኢትዮጵያዊ ማንነትና ብሔራዊ ማንነት ዛሬም በትናንትና በነገ፤ የስጋትና ተስፋ ትንታኔ አነጋጋሪነቱ ቀጥሏል፡፡

 

የኢትዮጵያዊ ማንነት ስጋቶች

በአገራዊ ማንነትና ብሔራዊ ማንነት መካከል ያለው ልዩነት በአንድ በኩል ያለፈው ኢትዮጵያዊነት የአንድ ወገን ኢትዮጵያዊነት ስለመሆኑ ያለመግባባት ችግር ነው፡፡ ያለፈው ኢትዮጵያዊነት በአገራዊ ማንነትና ብሔራዊ ማንነት መካከል ያለውን ልዩነት አይረዳም ነበር፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞም የኢትዮጵያዊነት ስሜት /መንፈስ/ ይጎልብት ሲባል ፡ ያንኑ ሌሎች ኢትዮጵያውያን በአግላይነት የአንድ ወገን ያደረጉትን የገዢ መደብ ማንነት የመመለስ ፍላጎት መሆኑ ያለመግባባት ምንጭ እንዲሆን አድርጓል፡፡ በተለይ ኢትዮጵያዊ ማንነትን ከቀደመው ኢትዮጵዊነት ጋር አያይዞ የሚመለከተው ወገን በብሔራዊ ማንነቱ እና አገራዊ/ኢትዮጵያዊ/ ማንነቱ መካከል ልዩነት ያለም አይመስለው፡፡ የእሱ ማንነት መለያዎች የአገራዊ ማንነት መገለጫ ተደርገው ሲኖር ነው የሚያውቀው፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያዊ ማንነት ሲል አንድም ቀድሞ የነበረው (የአንድ ወገን ) ኢትዮጵያዊነት ወይም ዛሬ እሱ ነኝ ብሎ የሚያስበው ማንነት ይመስለዋል፡፡

በሌላ በኩልም የአንድ ወገን ኢትዮጵያዊነትን ያወገዘውና ታግሎ የሻረው ኃይል የግል ለሆኑት ብሔራዊ ማንነቶች እንጂ የጋራ ለሆኑት አገራዊ ማንነቶች ትኩረት አለመስጠቱ ወትሮም ብሔር ተኮር ፖለቲካን የአገር አንድነት ስጋት አድርገው ለሚመለከቱት ትክክለኛ መነሻ ሆኗቸዋል፡፡ ከላይ የተመለከትናቸውን ጉዳዮች ስናይ በአገራዊ ማንነት ላይ ግልፅ መግባባት የለም፡፡ ሁለቱንም ለያይተን እናውራቸው፡፡

አንደኛው ኢትዮጵያዊ ማንነትን ሲያስብ በዚህች አገር ያሉ ህዝቦች የግል ማንነት እንጂ የጋራ ማንነት መገለጫዎች አይታዩትም፡፡ ብሔራዊ ማንነትን ቀዳሚ ጉዳይ ሲያደርግ ኢትዮጵያዊ ማንነትን ተከታይ ጉዳይ አድርጎ የሚያየው አስመስሎታል፡፡ አንድነትን ማቀንቀን ልዩነቶችን የሚደፍቅ ነው ብሎ ብዙ ማንነቶችን እንጂ ከህዝቦች ማንነት መካከል አንድ የጋራ አገራዊ ማንነትን [national culture and identity] መለየት ከብዶታል፡፡ ከሁሉም ህዝቦች እሴቶች የሚውጣጣ፤ ሁሉም ህዝቦች የሚወዱትና የሚጠሉት፤ የሚጠብቁትና የሚያከብሩት፤የሚያርሙትና የሚያበለፅጉት የጋራ ታሪክ፤ ባህል፤ እሴቶች፤ ልማዶች፤ ወጎች፤ ስነልቦና፤ ወዘተ ያላቸው መሆኑን አይቶና አጥንቶ በመለየት የጋራ ኢትዮጵያዊ መለያ [Ethiopian brand] እንዲኖረን ማድረግ አልቻለም፡፡ አገራዊ አንድነትን ለመፍጠር ልማት ያለው ድርሻ ቢታወቅም ፤ አገራዊ አንድነት በዚሁ ሳያበቃ ከሚያስተሳስሩንና አብረን ከምንፈልጋቸው የጋራ አገራዊ መለያዎች ሊመጣ እንደሚችልም አልተስተዋለም፡፡ በዚህም ምክንያት ህዝቦችን የሚያቀራርብና የሚያስተዋውቅ ልማት እየመጣም ስዎች ብሔሬ እንጂ አገሬ የማለት ነገራቸው እየሳሳ ነው፡፡ ምንም የሚያገናኘን የጋራ መለያ የሌለን ይመስል ስለግል መለያ እንጂ ስለምንጋራቸው መለያዎቻችን ማንሳት ይሳነዋል፡፡ አንዳንዴም በጥልቅ መስተጋብርም ባይሆን በነበረን ስስ መስተጋብር አብረን እንዳልኖርን፤ በተለያየ አገር እንደሚኖር ህዝብ እየተያየን: እነሱ እና እኛ የምንባባል የአንድ አገር ህዝቦች እየሆንን መጥተናል፡፡ በአጠቃላይ የአንዳችን ጉዳትና ጥቅም የሌላችን ጉዳትና ጥቅም ሆኖ የመታየቱ ነገር በአሳሳቢ ደረጃ እያሽቆለቆለ ነው፡፡ የጋራችን ኢትዮጵያዊ ማንነትን በተመለከተ ከብዝሃነት ውስጥ የሚቀዳ የጋራ አገራዊ መለያ ስለመኖሩ አውቆ አይሰራበትም፡፡ የጋራ አገራዊ መለያ መኖር የአገር አንድነት ዋስትና ነው ማለት እንዳልሆነ ግን ሊሰመርበት ይገባል፡፡ ከተለያዩ ብሔራዊ ማንነቶች በመወለድ ራሳቸውን በአንድ ብሔራዊ ማንነት ለመጥራት ስለሚቸገሩት ሰዎች የተሟላ መልስ የለውም፡፡ ጭራሹኑ በቅንነትም ብሔራዊ ማንነታቸውን ለመግለፅ የማይችሉትን፡ ከመፈረጅ አልፎ በብዝሃነት ውስጥ ያላቸውን ስፍራ አያስረዳም፡፡ ለህዝቦች ብሔራዊ ማንነት የሚጨነቀውን ያህል ከብሔራዊም አገራዊም ማንነቱ እየተነጠቀ የስደት ማንነትን በመላበስ ከራሱ እየሸሸ ያለው ትውልድ ሁኔታ አያሳስበውም፡፡ አዲሱን የከተሜ ትውልድ አገራዊ ስሜት እየናደ ካለው የምዕራቡ ዓለም ልቅ ማንነት ይልቅ ኢትዮጵያዊ ለዛ ያለው ቀረርቶና ሽለላ ያንገሸግሸዋል፡፡ የቀረርቶና ሽለላ ይዘትን የመተቸት ቢሆን አንድ ነገር ነው፤ ሆኖም ቢያንስ የአንድ ህዝብ ባህልና ወግ መሆኑን ዘንግቶ ከቀደሙት ሥርዓቶች እየተዛመደ በጥላቻ ዓይን ይታያል፡፡ መንፈሱና ልቡ እየተሰደደ ባለ ትውልድ፣ የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት ውስጥ ውስጡን በሚለበልባት አገር ኢትዮጵያዊ ማንነት ብሎ ነገር ፈተናው ብዙ ነው፡፡

በሌላ በኩል ያለው ወገን ደግሞ ኢትዮጵያዊ ማንነትን ሲያስብ ቀድሞ ከነበረው ኢትዮጵያዊነት የሚቀዳ ወጥ ኢትዮጵያዊ ማንነት አድርጎ እንጂ ህዝቦች ላሏቸው የግል መለያዎች ደንታ ቢስ ነው፡፡ አሁን አሁን ሌሎች ኢትዮጵያዊያን ህዝቦችና ማንነቶች ስለመኖራቸው አውቂያለሁ ቢልም የግል ማንነታቸውን ለማወቅ የሚያደርገው ጥረትና ፍላጎት አነስተኛ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የብዙ ማንነቶች አገር ስለመሆኗ በውል አይረዳውም፡፡ በነዚህ አካላት ኢትዮጵያዊነት ውስጥ የሶማሌው ድርሻ፤ የአኝዋክ፡ ኑየሩ…ወዘተ ድርሻ ምን እንደሆነ አያሳይም፡፡ የግልና የጋራ መለያዎች ያለን ብዙ ህዝቦች ሆነን ከግልም ሆነ ከጋራ ጉዳያችን በመነሳት አንድ አገር መመስረት ይቻል እንደሁ አያስበውም፡፡ ኢትዮጵያዊነትን ከአገራዊ ብዝሃነት ተነስቶ አያየውም፡፡ ስለ ኢትዮጵያዊነት እና አገራዊ አንድነት ሲያነሳ ለግል ጉዳዮች ተገቢውን እውቅና በመስጠት ከጋራና ከግል ጉዳዮቻችን የሚመነጭ ኢትዮጵያዊ መለያን አያሳይም፡፡ የራሱንም ሆነ ከእሱ ውጭ ያሉትን ህዝቦች ማንነት የተመለከተ ጉዳይ እንደትርፍ ጉዳይ ያየዋል፡፡ ብሔራዊ ማንነትን ማንሳት ከኢትዮጵያዊነት መውረድ ያደርገዋል፡፡ የህዝቦች ብሔራዊ ማንነት ላይ ማተኮር የአገር አንድነት ስጋት ነው ብሎ ያምናል፡፡ ያለፈውን ኢፍትሓዊነትና በደል ማንሳትና እውቅና ሰጥቶ የማረምን ጉዳይ አያነሳውም፡፡ የህዝቦች እኩልነት እና እኩል የመብት ባለቤትነትን ይሉኝታ ከሸበበው አባባል አልፎ አይታገልለትም፡፡ የኢትዮጵያዊነት ልዩ ተቆርቋሪ መስሎ ይታያል፡፡ በዚህም አንዱ የበለጠ ሌላው ያነሰ የኢትዮጵያዊነት ፍቅር ያለው አድርጎ እንደሚገነዘብ ይታይበታል፡፡ የአገር አንድነት ስጋት የሚለው ለብሔራዊ ማንነት የሚሰጥ ትኩረት እንጂ ከማንነቱ እየሸፈተ ያለው ከተሜ ትውልድ ጉዳይ አይደለም፡፡ ግሎባላይዜሽን እያስከተለው ካለው የማንነት ውርርስ ይልቅ ለብዝሃነት የሚሰጠው እውቅናና ትኩረት ያሰጋዋል፡፡ በነዋለልኝና ጥላሁን ዓይን ቢሆን የኢትዮጵያዊ ማንነት ስጋት የቱ እንደሆነ ግልፅ ነው፡፡

ስለሆነም የኢትዮጵያዊ ማንነት ስጋቶች ስንል በህዝቦች የግል ማንነት ላይ ማተኮር፤ የትናንቱን የአንድ ወገን ኢትዮጵያዊነት በመመኘት የብዙ ማንነት ባለቤቶች መሆናችንን አለመቀበል እንዲሁም ግሎባላይዜሽን የወለደው ከራስ የመሸሽ መለያዎች ናቸው፡፡

በአጠቃላይ የኢትዮጵያዊ ማንነት ግንባታ ጉዳይ እነዚህን እይታዎች የሚያስታርቅ ትርጉም እና ጥናት ሲኖረን የሚመጣ ይመስለኛል፡፡ አገራዊ መለያን ማበጀትና ማንነትን መለየት ብቻቸውን የአገር አንድነት ዋስትና ይሆናሉ ማለት ሳይሆን እንደህዝብና አገር በጋራ የምንቆምላቸውና የምንቆረቆርላቸው የጋራ ጉዳዮች ይኖሩናል ማለት ነው፡፡ ብዙም አንድም ነንና! የኢትዮጵያ አገራዊ አንድነት የብዙ ማንነት ባለቤት በመሆናችን አሊያም አንድ ማንነት እንዲኖረን በመፈለጋችን ብቻ የሚረጋገጥ አይደለም፡፡ ብዙ ማንነትም ሆነ ወጥ ማንነት ብቻቸውን የአብሮነት ዋስትና አይደሉም፡፡ የግልና የጋራ መብቶቻችንን በሚያስተናግድ ዲሞክራሲና በግልና በጋራ እኩል ተጠቃሚ በሚያደርግ ልማት መበልፀግ ብቻ ህልውናችን ነው፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.