ተጠያቂነት ይለምልም!

(ጦማሪ አንሙት አብርሃም)
**
ሰሞኑን በተካሄደው የብሮድካስት ድርጅቶች ‘…አዝማሚያ’ ዙሪያ ብዙ ሊነሱ የሚገባቸው ጉዳዮች ነበሩ :: ይበልጥ ቀልቤን የሳበው የአቶ ንጉሱ ጥላሁን የተጠና (well rehersed) ንግግር ነው:: ENN ቴሌቪዥን በኢሉአባቦራ ብሔር ተኮር ጥቃት ዙሪያ የዘገበውን ዜና ተከትሎ ብዙዎች ዛሬም ከብስጭት ሊወጡ አለመቻላቸውን ያሳያል:: የዘገባው ስህተትና በጎ ነገር እንዳለ ሆኖ የብዐዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ንጉሱ የጣቢያው ዘገባ ‘በቃጣው ህዝብን የመጉዳት ሙከራ ስልጣን መለቀቅ ነበረበት ብለዋል:: እንደሬጉሌተር ይህን የጥቃት ሙከራ ማለፍ አይገባም ነበር ማለታቸው መሰለኝ:: እኔም እስማማለሁ:: ግን ከአቶ ንጉሱ ድርጅት ብዐዴንም ጉዳት ያደረሰ ስልጣን ቢለቅስ!? :: በህዝብ ላይ ጉዳት ያደረሰ ይቅርና potentially ለማጥቃት የሚያስችል ሙከራ ያደረገም ስልጣን ይልቀቅ ካልን ጉዳት እንለይ! ሆኖም ፍረጃችን ፈር እንዲይዝ እንዲህ ያደረገው አመራርስ ስልጣን ለምኑ?
***
1, ህዝብን ለግጭት የሚዳርግ የጥቃት ሙከራ ሳይሆን የወጣት እልቂት የሰርክ መርዶ በሆነበት አገርና ክልልዎስ ማን ስልጣን ይልቀቅ?
*
2, ከባህርዳር እስከ ወልድያ ፣ ከጎንደር እስከ መርሳ ባለፍት 3 ዓመታት ላለቀው ወጣት ፣ለዚያውም ‘በእኔ የመምራት ችግር (የህዝብ ጥያቄ ምላሽ አለመስጠት ምክንያት) ነው’ ያለ ድርጅት እና አመራር ዛሬም ስልጣን ላይ ነው?
*
3,ባለፍት 4 ዓመታት 3 ጊዜ የካቢኔ ሹምሽር ያደረገ፣ ፖሊሲ የማስፈፀም ስራን ከፖለቲከኞች አንስቶ ለባለአደራ የጆርናል አሳታሚዎች የሰጠ፣ ነጋ ጠባ የወጣት ሞት መርዶ የደርግን ዘመን ሲያስታውሰን ይህን ያደረገ ግንባር ፓርቲና አመራርስ ምን ይሁን?
*
4, ሩብ ክፍለዘመን ክልል የመራው ብዐዴን ዛሬም እበት ለቅልቆ፣ ጀንዲና ቁርበት የአፈር መደቡ ላይ አንጥፎ ከመኖር ያልተላቀቀ ህዝብ አለው ፣ ዛሬም በባዶ እግር መርፌ የሰለቻት ቁምጣውን ታጥቆ የሚለፋ አርሶ አደር አለ፣ ዛሬም ሞዲየስ ብርቅ የሆነባት እናት የትም አለች:: ይህን የኑሮ ዘይቤ ያልቀየረ ድርጅት ከ26 አመት ስልጣን በላይ ምን ቢሆን ይሻላል? ይህንን ሪያሊቲ 26 ዓመት ካልለወጠው ምን ይለውጠዋል?
*
5, የክልሉ ወጣትና ህዝብ ምን ያህል የስብዕና መሸርሸር እንዳለበት (dehumanization) አስተውለናል? ዛሬ እኮ በብዙ ከተሞች እቃ ተሸካሚ ሲፈለግ “ተሸካሚ.. ተሸካሚ/ ወዝአደር: ወዝአደር..” ተብሎ አይጠራም፣ “ጎጄ..ጎጄ..” ነው የሚባል፣ “ቆምጨ ጥራ” ነው የሚል፣ ትናንት ሌሎች ይመኙት የነበረ ነባሩ የአማራው መጠሪያ ስም ማሾፊያ ሲሆን፣ ትናንት የሁሉም ግብ አማርኛን ማቀላጠፍ እንዳልነበር: ዛሬ የንግግር ዘዬ ተለይቶ መሳለቂያ ሲሆን እወክልሃለሁ የሚል ድርጅት የዚህን ህዝብ ስነልቦና እና ክብር ለማሳደግ ባለመስራቱ ከ26 ዓመት በላይ ስልጣን ስንት ቢሆን ይሰራል?
*
6, እስኪ ድራማውን፣ ዘፈን ማድመቂያውን እንየው የዃላ ቀር የቤት ሰራተኛ ፣ ዘመናዊነት የራቀው ዘበኛ ፣ የባላገርነት ማሳያ የሚደረገው ማን ነው? ለምን? እስከመቼ? ይህንን የሚያይ አመራር በስልጣን ይቆይ? ስንት ዓመት?
*
7, በአማራ ክልል ይኖራል ከሚባለው 22 ሚሊዮን ህዝብ ውስጥ 26 ዓመት መርታችሁት ዛሬም 18ና 19 ሚሊዮን አርሶአደር ተይዞ ስለግሎባላይዜሽንና ዘመናዊው ዲጅታል ዓለም የውድድር ዘመን ሊያስብ ይችላል??? ኢንደስትሪን፣ ከተሜነትን፣ ዘመናዊነትን ለሚመራው ህዝብ ብርቅ ያደረገ አመራርስ ምን ይደረግ?
*
8, ይህን ያህል የስልጣን ዘመን እኩልና ፍትሐዊ ተጠቃሚ ያደረገ እድገት አመጥተናል፣ እንደግንባር አብረን መክረን: ተሟግተን፣ ተግባብተን አብረን አገራዊ እቅድ ወስነን አፅድቀን እንሰራለን ያለን ድርጅትና አመራር ዛሬ : “የአንድ ህዝብና ክልል የበላይነትና ተጠቃሚነት አለ” ሲለን ምን እንበል? 26 ዓመት ሙሉ ‘ወክሎን ስለእኛ ይሰራል፣ ፍትሕዊ ተጠቃሚ ያደርገናል ብሎ ያስብ ለነበረ ህዝብ ምላሹ ምንድን ሆነና ነው መደምደሚያው የአንድ አካል የበላይነት የተባለው? ለአንድ ወገን ጥቅም ነው 26 አመት ሙሉ እየወሰንን :እያፀደቅን የኖርነው ነው የምትሉን? ወይስ የድርሻችንን አልተወጣንም: ለስልጣናችን ስንል በህዝቡ ስም ነገድን ነው የሚባል? እንዲህ ያለ ድርጅትና አመራርስ እስከመቼ በወንበሩ ይሰንብት? በዚህ ምክንያት ለተነዛው አገራዊ ብሔር ተኮር ጥላቻና ፍረጃ ብሎም ሞትና ውድመት ምክንያት የሆነ አመራርስ በስልጣን ይቆይ?
*
9, በENN ዜና ችግር እንስማማ! ፣ ግን በዚያ ዜና ምክንያት ሰው አልተፈናቀለም፣ የዜጎች ብሔር ተኮር ጥቃት አልተፈፀመም፣ የታረደ ህዝብ የለም .. ወዘተ..ግን ግን እንዲህ ያለ አዝማሚያ ሊፈጥር ስለሚችል ENN ውስጥ ስልጣን የሚያስለቅቅ ከሆነ፣ ….ብሔር: አመራር እና ተቋም ተኮር ጥላቻ የሰበከ የኮሚንኬሽን ኃላፊና አመራርስ ምንም አይሆንም?
**

Leave A Reply

Your email address will not be published.