ታስፈሩኛላችሁ!!!

(Wasihun Tesfaye) አንዳንዴ ዝም ብዬ ሳስበው ይህችን ሃገር ወደ አዘቅት ለመጣል ……. ቁልቁል ወደ ጨለማው ለመፈጥፈጥ ከአንድ እስከ ሶስት ለመቁጠር የተዘጋጃችሁ ሲመስለኝ እፈራችኋለሁ !!!

በረሃብ የዛሉ ኢትዮጵያውያን ሻንጣና ህፃናት ይዘው በረጅሙ ተሰልፈው ሲሰደዱ …….. የዋና ዋና ከተሞች ህንፃዎች ፈራርሰው ሰው ኣልባው ከተማ የአይጥ መጫወቻ ሲሆን እያሰብኩ እቃዣለሁ።

በትላልቅና ሹል ጥርሶቻችሁ ይህችን ሃገር ብጭቅጭቅ ልታደርጓት የጎመዣችሁ መስሎ ሲሰማኝ በፍርሃት ጉልበቴ ይርዳል።

በጀመራችሁት የብሄር ጥላቻ ምክንያት በሚነሳ የርስበርስ ጦርነት ወላጆቻቸውን የናፈቁ … የተቀዳደደ ልብስ የለበሱ ጎስቋላ ኢትዮጵያውያን ህፃናት በወላጆቻቸው መቃብር ላይ ውለው ሲያድሩ በሃሳብ እያየሁ በድንጋጤ ላብ ያጠምቀኛል።

ልብሳቸው በደም የቆሸሸ በዘረኝነት ያበዱ ጎረምሶች … ህፃናትና ሴት ሽማግሌና አሮጊት ሳይመርጡ ከነሱ ዘር ውጭ የሆነውን ሁሉ ለማረድ ሲሯሯጡ ማየት አስፈሪ ነገር ነው።

ይህ ሟርት አይደለም መጥፎ ምኞትም አይደለም ይህ በሁሉም ብሄር ውስጥ ያሉ ጥቂት ዘረኞች ከዚህ አካሄዳቸው ካልተገቱ እና ቆም ብለው ማሰብ ካልጀመሩ በሃገራችን ተከስቶ የማናይበት ምክንያት የለም ። በእቅድ የፈረሰ ሃገር የለም።

ይሄ ተራ የሚመስል ዘር ለይቶ ማጥቃት ። ይሄ ዛሬ በጥቂቶች ልብ ውስጥ ነብስ የዘራ ጥላቻ … ነገ የማያድግበትና ሃገር የማያጠፋበት ምክንያት የለም ። ወደ ልቦናችን እንመለስ። የተሻለች ነገን ለልጆቻችን ለማውረስ ጥላቻን እንተው።

ማንም አሸናፊ በማይሆንበትና ወደ የትም በማያደርሰው የጥላቻና የዘረኝነት መንገድ መጓዙ ይብቃን።

እጣ ፈንታ ያስተሳሰረን ያንድ ሃገር ልጆች ነን እርስ በርስ መዋደድና መተባበር ለኛ የምርጫ ጉዳይ አይደለም!!!

Leave A Reply

Your email address will not be published.