ትራይባስ ግሩፕ በኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ ፋብሪካ ሊነገባ ነው

(ኤፍ.ቢ.ሲ)- ተቀማጭነቱን በአሜሪካ ያደረገው ትራይባስ ግሩፕ በኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ የጨርቃ ጨርቅ እና አልባሳት ፋብሪካ ሊገነባ ነው።

ኩባንያው ፋብሪካውን መገንባት የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ጋር ተፈራርሟል።

የመግባቢያ ስምምነቱን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ፍጹም አረጋ እና የትራይባስ ግሩፕ ዋና ዳይሬክተር ሊሹን ዋንግ ናቸው የተፈራረሙት።

በስምምነቱ መሰረት ትራይባስ ግሩፕ በፓርኩ ውስጥ ለሚገነባው ፋብሪካ 5 ሺህ 500 ካሬ ሜትር ቦታ የሚይዝ ሲሆን፥ በመጀመሪያው ምዕራፍ ለ1 ሺህ 500 ኢትዮጵያውያን የስራ እድል ይፈጥራል።

ኩባንያው በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ ሲገቡም 5 ሺህ 500 ሰራተኞችን ቀጥሮ ለማሰራት ነው ያቀደው።

ባለፈው ሀምሌ ወር በይፋ በተመረቀውና በ90 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በተገነባው የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ከአሜሪካ፣ ደቡብ ኮሪያ እና ጣሊያን የመጡ ግዙፍ ኩባንያዎች ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን ያመርታሉ።

በ75 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው የኢንዱስትሪ ፓርኩ በመጀመሪያ ምዕራፉ 13 ሼዶችን ይዟል።

የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ በዘጠኝ ወራት ውስጥ የተጠናቀቀ ሲሆን፥ በቀጣይም እስከ 1 ሺህ ሄክታር መሬት ለማስፋት መታቀዱን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር አርከበ እቁባይ በፓርኩ ምረቃ ወቅት መናገራቸው ይታወሳል።

ሁለተኛው ምዕራፍ የኢንዱስትሪ ፓርኩ ማስፋፊያ ደሴን ጨምሮ ሌሎች የዞኑ አካባቢዎችን የሚያካትት የኢንቨስትመንት ኮሪደር ልማት ጥናትን መሰረት በማድረግ እንደሚከናወንም ነው የጠቆሙት።

በተያያዘ የባህር ዳር ኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ በ2010 ዓ.ም ሚያዚያ ወር ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑ መገለፁ አይዘነጋም።

ከአዲስ አበባ ከተማ አጠቃላይ እድገት ጋር የሚቆራኝ ሰፊ የኢንቨስትመንት ኮሪደር ልማት አካል የሆኑት፥ የአረርቲ እና የደብረ ብርሃን ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ግንባታ በ2010 ዓ.ም ሰኔ ወር ለማጠናቀቅ መታቀዱን ዶክተር አርከበ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን መረጃ እንደሚያሳየው ሀገሪቱ ከጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ምርቶች በየአመቱ 150 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ታገኛለች።

በዘርፉ ሰፊ ስራ ከተሰራ ግን ሀገሪቱ በየአመቱ እስከ 1 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ድረስ ገቢ ማግኘት እንደምትችል ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት።

Leave A Reply

Your email address will not be published.