ችግር ያስተማረን ኢህአዴግ ነው!

(በኡስማን ሰዒድ) –  እስቲ ችግር እንቁጠር! በደል እንደርድር! በዓይነት በዓይነት እንሰድረው! ከምን እንጀምር? ከራሳችን፡ ከቤተሰባችን፡ ከአገሪቱ፡ ከህዝብ…? የምን ችግር እንቁጠር? የፖለቲካ፡ የኢኮኖሚ፡ የማህበራዊ ፡ መንፈሳዊ…? ወይስ የሰውን፡ የእንስሳቱን፡ የእርሻውን፡ የወንዙን ተራራውን…? ፡ ነው የአስተሳሰባችንን፡ የአስተዳደራችንን፡ የአኗኗራችንን? የማንን ችግር እንቁጠር? የምሁሩን፡ የፖለቲከኛውን፡ የሓኪሙን፡ የጋዜጠኛውን፡ የወጣቱን፡ የሰራተኛውን….? ምኑን እንቁጠረው? የችግሩን ብዛት፡ጥልቀት፡ ተፅእኖውን …? አይይ… ሁሉም ሲያስቡት ያደክማል፡፡

ከአንድ የስልጣኔ ማማ ተፈጥፍጦ ለአንድ ክፍለ ዘመን ያህል በጦርነት ሲፋጅ ለኖረ ህዝብ፤ ድንቁርና፡ ችጋር እና ልመና መለያው ሆኖ ህልውናው ሊጠፋ የነበረ ህዝብ፤ የአስተዳደር ወግ ነጥፎበት የስልጣን ምንጭን ጥይት አርጎ ለኖረ፤ ጠኔ የደቆሰውን ህዝብ አምባገነን ልሂቃን ጭሰኛ እና ገባር አድርገውት ለኖረ ህዝብ ፡ ስንቱ ችግር ተቆጥሮ ያልቃል? በአምስት መቶ አመታት የቁልቁለት ጉዞ የችግሮች ሁሉ አለት ላይ በነበረ እና ባለ ህዝብ ውስጥ ችግር ‘ብርቅ’ ነው እንዴ? ከችግር ብዛት የተነሳ ችግርን ተላምዶ የመኖር አማራጭ ውስጥ የነበርን ህዝቦች እኮ ነን፡፡

ከድህነት መላመድ፡ ከድንቁርና መዋሃድ፡ ኢፍትሓዊነትን መቻል፡ ከብዝበዛና ጭቆና መስማማት የኖርንበት አይደለም እንዴ? ችግርን በችግርነት አልተረዳነውም ማለት አልተቸገርንም ማለት አይደለም፡፡ መብትን እንደ መብት አላወቅነውም ማለት አስፈላጊነቱን የሚያጎላ አስቻይ ሁኔታ የለ እንደሁ እንጂ የመብት ንፍገት ጉዳት አልደረሰብንም ማለት አይደለም፡፡ እናማ ለውጥ እና መፍትሔ እንጂ ችግርማ የኖርንበት ነው፡፡ ከግል እስከ አገር፤ ከአሰራር እስከ አኗኗር ችግራችን ተቆጥሮ አያልቅም፡፡ ከችግር አዘቅት ለመውጣት በሚታገል አገር፡ ችግር ቆጠራ ችግርን የመረዳት መጀመሪያ እንጂ የችግር መኖርን አስገራሚነት (‘ብርቅነት’) አያሳይም፡፡ ችግርን ማወቅ ለመፍትሄ እንጂ ለመሳለቅ መች ይጠቅማል፡፡ የችግር መኖር ‘ብርቅ’ የሚሆነው ለሞላለት ነው፡፡ በጨለማ ውስጥ አንዲት ጥግ ያለች ብርሃን ነች ብርቅ፡፡

በአዲሲቷ ኢትዮጵያ የተፈጠረው ምንድን ነው? ችግሮቻችንን እና በሽታዎቻችንን እንድናውቅ የሚያደርግ አገራዊ እና አለማቀፋዊ ሁኔታ ተፈጠረ፡፡ ችግርን እየተገላበጡ ከመሞቅ፡ ከችግር ከመስማማት፡ በበሽታነት ወደ መረዳት፤በምሬት ወደ መቁጠርና ማውገዝ ተሻገርን፡፡ እሰየው ነው፤ መቁጠር ጀምረናልና መጪው ጊዜ የመላመድ ሳይሆን የማስወገድ ነው፡፡ ኢህአዴግ ያረገውም ከመላመድ ብዛት ትክክል የመሰሉንን ችግሮች ፡ በችግርነት እንድንረዳ በር ከፈተ፡፡ በአጭሩ ችግር አስተማረን፡፡ ‘እኩል ነን’ ብሎ እኩል ያለመሆንን ችግር አሳየን፡ ‘ዲሞክራሲ መብቴ ነው’ እያልን የፀረ-ዲሞክራሲያዊነትን ችግር ተማርን፡፡ ‘ልማት እናልማ ፡ ድህነት ነው ጠላት‘ ተብሎ የድህነትን ችግር አጠናን፡፡ የአንድአይነትነትን መፈክር ለምደነው ኖረን ዛሬ ፡ብዙ ግን እኩል፡ መሆናችን ሲነገረን ደነገጥን፡፡ እናም ችግር ቆጠራውን ተያያዝነው፡፡ በአንድ በኩል ከለመድነውና ችግርነቱ ከማይሰማን ሁኔታ ላለመውጣት፡ የዛሬን ችግር ብቻ ሳይሆን ዛሬ ያወቅነውን ዛሬ የመጣ አስመስለን ፡በሌላ በኩል አዲሱ የችግር መረዳታችን በፈጠረብን ችግር አዋቂነት ፡ችግር ቆጣሪዎች ሆንን፡፡ ልክ ሁሉም ሞልቶለት እንደኖረ ህዝብ በአገር ችግር መገረም የማወቅ ውጤት ነው፡፡ ማወቅ ደጉ፡ የትናንት ችግር አላማጆችም ችግር ቆጣሪ ሆነዋል፡፡ ችግርን የተረዳነው ዛሬ ነው ማለት ትናንት ለምደነው ያልተረዳነው ችግር አልነበረም፤ ለዛሬ አልተረፈም ማለት አይደለም፡፡ “እየየም ሲደላ ነው” ያለው ያገሬ ሰው ወዶ አይመስለኝም፡፡ በበደል፤ በርዛት፤ በቸነፈር እና በጭቆና ውስጥ ሆነን ችግራችን መጠን ቢያጣም፡ ‘እየየ’ ለማለት ባይደላን ነበር ወልዶ መሳምን የረገምነው፡፡ ዛሬ ችግርን ማወቅ የበለጠ ድሎት ቢነሳም የችግሮች መኖር በፈጠረብን ብሶት ‘እየየ’ ማለት ብቻ አይጠቅምም፡፡ የመፍትሔ አካል እንሁን፡፡ ከችግር ያስተዋወቀን ስርዓት ጥቂት ችግሮች ቀርፎ ሲያሳየን ከበውን በቆሙት ሌሎች ችግሮች ብንገፈገፍም፡ ችግርን ለማወቅ የተገለጠው ዓይናችን መፍትሔም ያማትር፡፡

ሆኖም ችግሮቻችንን እንወቃቸው፤ ዋና ችግሮችን እና ተከታይ ጣጣዎቻቸውን እስከቻልነው እንቁጠራቸው፤ የቱ’ጋ እንዳጠፋንም እንለይ፡፡ ሁሉንም ችግሮቻችንን ማወቅ፤ በአይነት እና በወግ መለየት ለመፍትሔ ይበጃልና ጠቃሚ ነው፡፡ ባለቤቱም በውርርስ ያኖርነው የእኛ የህዝቦች እና የአገር መሆኑን እናገናዝብ፡፡ ያልተወራረደ የችግር ውርስ ያለበት ህዝብ ላይ ዘመን-አመጣሽ ችግሮች ሲደመሩበት ብዙ ነውና እንደ ችግሩ መፍትሔም እንቁጠር፤ መላ እናውራ፡፡ ለውጥ ብቻ እንቁጠር በጭራሽ አልልም፡፡ ለሌሎች መፍትሔ እንዲያግዘን ግን እናስባቸው፡፡ ማወቅ በፈጠረብን ድንጋጤ እንድናውቅ በር የከፈተው ስርዓት ላይ ብቻ መውረድ ግን ለመፍትሔ ማገዙን እያሰብን መሆን አለበት፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.