ነገሩ ያላመረለት ነገሬ

(www.EthiopiaFirst.com) – ከአሁን ቀደም እንዳነሳሁት ይህች ሃገር የኮምንኬሽን ሃላፊ ያላትም አይመስልም። ሀገሪቷ አሁን ባለችበት ውጥንቅጡ በበዛበት ወቅት፤ ወቅታዊ ጉዳዮችን ከስር-ከስር በትክክለኛው መንገድ (Perspective) የሚያቀርብና አጀንዳ የሚቀርፅ (Agenda setter) የኮምንኬሽን ሃላፊ ያስፈልጋት ነበር። ነገር ግን አለመታደል ሆኖ ሃላፊው ከህዝቡ ጋር “ኩኩሉ አልነጋም” የሚጫወቱ ይመስል ተደብቀው ነው የከረሙት። በአሁኑ ወቅት አጀንዳ የሚቀርፁትም ሆነ የመንግስትን እይታዎች በመሰላቸው ልክ ለመግለፅ እየሞከሩ የሚገኙት (በበጎውም ሆነ በአሉታዊ መልኩ) የፌስቡክ ጦማሪዎች ናቸው።

የኢፌድሪ የኮምኒኬሽን ሃላፊ ዶ/ር ነገሬ በሚፈለጉበት ወቅቶች በሙሉ ተደብቀው ከርመው ሰሞኑን “ህይወት አሳጥራለው” ብለው መምጣታቸውን ሰማን። እኛም ወቸ ጉድ! ከማለት አልፈን “ጮሃ የማታውቅ ዶሮ ብትጮህ … እለቁ፤ አለቁ!” የሚለውን ተረት ለማስታወስ ተገደድን።

የዶ/ር ነገሬ የሰሞኑ ንግግር የኮ/ል መንግስቱን ንግግር ያስታወሰ ነበር። ይህች ሃገር ህገ-መንግስትና ስርዓት ያላት በመሆኗ ማንም ሹመኛ እንደ ኮለኔሉ ዘመን ነሸጠኝ በማለት ያሻውን የማያደርግባት ሃገር ነች። እነዛ የትግሉ ዘመን ታጋዮች ውድ ህይወታቸውን የገበሩት የትኛውም ሹመኛ በነሸጠው ጊዜ እየተነሳ “ህይወት ማሳጠር” እንዳይችል ነው። የተዘነጋው ይሄ ጥሬ ሃቅ ነው።

ሰውየው ከየትኛውም ሀገራዊ ጉዳይ ይልቅ ነጋ-ጠባ ሲያነሱት የምንሰማው ከአሁን ቀደም የተናገሩት ጉዳይ የግል አመለካከታቸው መሆኑን በብሮድካስት ተቆጣጣሪ ሃላፊው መባሉ ነው። ይህ ንግግር ለምን እንቅልፍ እንደነሳቸው ሊገባኝ አልቻለም። እንኩዋን የኮምንኬሽን ሃላፊው ንግግር ይቅርና ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ ሳይቀሩ የተወሰኑ ጊዜያት ይሄ የግል አመለካከቴ ነው ብለው ነበር። ለአብነት ያህል በጀግናው ሃየሎም አርአያ ሃውልት ዙርያ ጥያቄ ቀርቦላቸው መልስ ሲሰጡ የግል አመለካከታቸው እንደሆነ ተናግረው ነበር። በአንድ ወቅትም የፖለቲካ ፓርቲዎች ክርክር ላይ እርሳቸው ለምን እንዳልቀረቡ ሲጠየቁ “ይመስለኛል” ብለው የግል እይታቸውን አቅርበዋል።

የትኛውም ሹመኛ በየትኛውም ወቅት የተናገረው በሙሉ እንዴት የመንግስት ቃል ይሆናል። ዶ/ር ነገሬ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዋንጫን የቅ/ጊዮርጊስ ክለብ ቢበላ ደስ ይለኛል፤ ወይንም አርሴናል የእንግሊዝን ዋንጫ መብላት አለበት ሲሉ ቢሰማ ይሄ የመንግስት ውሳኔ ነው ብለን ለማምን ልንገደድ ነው?? የኮምንኬሽን ሃላፊው የስራ ድርሻ አጀንዳ መቅረፅ ነው እንጂ የትኛውን ሚድያ መቼ መከሰስ እንዳለበት መወሰን አይደለም። ያ ሃላፊነት የብሮድካት ተቆጣጣሪው ነው። በግልባጩም የብሮድካት ተቆጣጣሪ ሃላፊው በህግ ከተሰጠው ሃላፊነት ወጥቶ አጀንዳ ቀራጭ ልሁን ካለም ስህተት ነው። ነገር ግን አቶ መለስ ከአሁን ቀደም ይሉት እንደነበረው የግል አመለካከትን መግለፅ ግን ይቻላል።

ስለዚህም መክሰስን በተመለከተ የኮምኒኬሽን ሃላፊው በአዋጅ የተሰጠው ስልጣን ስለሌለ በዛች ጉዳይ የሚንስትሩ ንግግር የግላቸው መሆን አለበት መባሉ ምንድን ነው እንቅልፍ የሚያሳጣው? ይሄንን ማለት ደግሞ የእሳቸው ንግግሮች በሙሉ መንግስትን የሚወክሉ አይደሉም ማለት አይደለም። “ይህች ለቅሶ ከፍየሏ ሞት በላይ ነው” እንደተባለው በግልፅ መነገር ያልተፈለገ ሌላ አጀንዳ ከጀርባ ካለ እሱ ሌላ ጉዳይ ነው፤ ሊፈታም የሚገባው በሌላ መድረክ ነው።

ነገር ግን ይሄንን ንዝንዝ ተከትሎ “ህይወት አሳጥራለው” እያሉ መፎከር በዚህ ስርዓት ዘመን የማይሞከር ነው። ይሄንን ፉከራ ደግሞ የሚኒሶታው ጃዋር ሲያጀገንነውና አንበሳዬ አይነት ሙገሳውን ሲችረው ስናይ “ይህች ለቅሶ ከፍየሏ ሞት በላይ ነው” ብለን እንድንጠራጠር ይገፋፋናል። ምክንያቱም ድሮ-ድሮ ስናስታውስ የፍላሚንጎ ሰፈሩ ኮምንኬሽን ቢሮና የሚንሶታው ሰውዬ ቢሮ ለየቅል ነበሩና !!

Leave A Reply

Your email address will not be published.