ንስር አሞራው ከፍ ብሎ መብረር መጀመሩ ይሆን?

TPLF-Completed-Its-Meeting (Read PDF Version)

————————————————–

(www.EthiopiaFirst.com) – ንስር አሞራ በአርባኛ አመቱ ሁለት አማራጭች አሉት። የመጀመሪያው አማራጭ ጥፍሩና ማንቁርቱ አርጅቶ መሞት ሲሆን ሌላኛው እንደአዲስ ታድሶ ቀጣይ አርባ አመት ከፍ ብሎ መብረር ነው።

ህወሓትም በአርባኛ አመቱ ገደማ ተመሳሳይ አማራጭ ቀርቦለት በመታደስ ከፍ ብሎ መብረርን የመረጠ ይመስላል።

በትላንትናው እለት ከተጠናቀቀው የህወሓት ማራቶን ስብሰባዎች ምን ተገኙ? ለድርጅቱም ሆነ ለሀገር ምን መፈየድ ይችላል?

  • የአሁነኛው ስብሰባ ከዚህ ቀደሞቹ የተለየ የሚመስለው ችግሮቹን በሙሉ አምኖ መቀበሉ ነው። እንደተለመደው የውሸት ሪፖርቶች በመስማት ወደተሳሳተ ድምዳሜ አልነጎደም። ወይንም ደግሞ ውጪያዊ ሃይሎችን በመወንጀል እራሱን ከተጠያቂነት አልሸሸገም። ችግሩ እኔና እኔ ጋር ነው በማለት እራሱን መርምሮ ለበሽታው መድሃኒት ወደመፈለጉ ነው የሄደው።

ህወሓቶች ብሎም ኢህአዴጎች ዘንድ ችግሮችን ማመን ብዙም አስገራሚ ላይሆን ይችላል። ይሄኛውን የተለየ ያደረገው ለችግሮቹ ባለቤት መስጠት መቻሉ ነው። ለአብነት ያህል ከአሁን ቀደም እንደምንሰማው ድርጅቱ ውስጥ የትምክህት፣ የጥበት፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮች … አሉ ብሎ ሾላ-ድፍን እርግማን አውግዞ ከማለፍ ይልቅ የእነዚህ መገለጫዎቹ በማንና በምን ታይቷል በማለት ተጠያቂነት ያሰፈነ ነበር። ግምገማዎቹ በጣም ጠጣር በመሆናቸው እንደውም አንዳንዶች ህወሓቶች “ተባሉ” ብለው እስከመፃፍ ደርሰው ነበር። እውነታው ግን ህወሓቶች ወደ ድሮ ማንነታቸው መመለሳቸው ነበር። ሲገማገሙ ውለው ማታ-ማታ “ብፃይ በጃሂ …” እየተባባሉ እራት ከአንድ ማዕድ ይበሉ ነበር። ችግሮቹን እንዳለ አምኖ ለችግሮቹ ተጠያቂነት ማስፈኑ ዘንድሮ ያየነው አዲስ ክስተት ነው።

  • ውይይቶቹ ህዝብን ማዕከል በማድረግ የተካሄዱ በመሆናቸው አንዳንዶች እንደፈሩት/እንደተመኙት አንጃነት ሳይፈጠር ሁሉም ወገን ተደስቶበት የተጠናቀቀ ነበር። ለዚህም ማሳያ የድርጅቱ ሊ/መንበር የነበሩት አቶ አባይ ወልዱን መመልከት ይቻላል። አቶ አባይ ልክ እንደሌሎች አባላት በአይምሬው ሂስ/ግለሂስ ያለፉ ናቸው። ያንን ሂደት ተከትሎ ሁሉም ነገር ሚዛን ላይ ሲወጣ የሰውየው ከሃላፊነታቸው መነሳታቸው ተመራጭ ሆነ። ነገር ግን ትላንትና ማታ ስብሰባው እስከሚጠናቀቅ ድረስ ሁሉንም ስብሰባ በሃላፊነት ይመሩ የነበሩት አቶ አባይ ወልዱ ነበሩ። የዚህ ምስጢሩ የውይይቶቹ አልፋና ኦሜጋ ህዝብን ማዕከል በማድረግ የተሰራ ስለነበር ነው።

በውይይቶቹ ወቅት ተከስቶ የነበረው የወ/ሮ አዜብ መስፍን ስብሰባውን ረግጦ መውጣትም በትክክለኛው መንገድ መስተካከል ችሎ ነበር። ይህም ሴትየዋ ያደረጉት ነገር በፍፁም ተቀባይነት የሌለውና፤ በድርጅቱም የሚወገዝ ድርጊት መሆኑን እራሳቸው አምነው በደብዳቤ ይቅርታ የጠየቁበት ነበር። ያንን የይቅርታ ደብዳቤን ተከትሎም ወደ ስብሰባው በመመለስ የሂደቱ ተካፋይ ነበሩ። ከፍ ሲል አንዳነሳሁት በሁሉም ላይ የነበረው ግምገማ በጣም ጠንካራ እንደመሆኑ የወይዘሮ አዜብ ስራዎችም ሚዛን ላይ ሲቀመጥ በስራ አስፈፃሚውም ሆነ በማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት እንዳይቀጥሉ የጋራ ውሳኔ ላይ ተደረሰ። ይህ ውሳኔ ላይ የተደረሰው ለምን ስብሰባውን ጥለው ወጡ በሚለው ሳይሆን እስከዛሬ የተሰሩት ስራዎችን በመገምገም ነው። አንድን አባል ከማዕከላዊ ኮሚቴ የመቀነስ ስልጣን ያለው የድርጅቱ ጉባዔ በመሆኑ እስከዛው ድረስ ከሁለቱም መድረክ ርቀው እንዲቆዩ (to be suspended) በጋራ ተወሰነ። ይህም ውሳኔ የጋራ የነበርና አንድነት የተንፀባረቀበት አቁዋም ነበር።

እዚህ ላይ ሊስተዋል የሚገባው በዚህ ስብሰባ ወቅት ማዕከል የተደረገው አመለካከቶች እና ሂደቶች እንጂ በግለሰቦች ዙርያ ያጠነጠነ አለመሆኑ ነው። ጉባዔተኛው ወይዘሮዋ ስብሰባውን ረግጠው በመውጣታቸው ተመልሰው እንዳይገቡ በማለት መወሰን ይችል ነበር። ነገር ግን አትኩሮቱ በግለሰቦች ዙርያ ባለመሆኑ ወ/ሮ አዜብ ትልቅ ስህተት ፈፅሜያለሁ፤ ይቅርታ ይደረግልኝ ሲሉ ወድያውኑ ተቀብሏቸው ወደ ውይይቱ ነው ያመራው።

ትላንትና ማታ መቀሌ አክሱም ሆቴል አዳራሽ ውስጥ ስብሰባው አልቆ ተሰብሳቢው በሙሉ በጋራ አየተሳሳቁና እየተቀላለዱ እራታቸውን በጋራ ሲመገቡ ላያቸው፤ እንኩዋንስ ሁለት ወር የፈጀ የሰላ ግምገማ ውስጥ የቆዩ ሳይሆን ከረጅም ጊዜ የእረፍት ቆይታ የተመለሱ ስብስቦች ይመስሉ ነበር። ከእራት ግብዣው ቀጥሎ የነበረው እስክስታና ጭፈራን የተመለከተም ድል ያለ ሰርግ ሊመስለውም ይችል ነበር። ህዝብን ማዕከል ያደረጉ ስብሰባዎች ጥቅማቸው ግላዊ ስለማይሆኑ ነው።

  • ሌላኛው በዚህ ስብሰባ የተስተዋለው መልካም ነገር ተመልሶ ወደ አዙሪቱ ላለመግባት ስርአቶችን (Systems) መዘርጋት ነበር። የማዕከላዊ ኮሚቴው ያስቀመጠው ዋነኛው አቅጣጫ በፍጥነት ወደ ህዝቡ እንዲወረድ ነው። ህዝብ ነው ሁሌ በቅጡ መሞረድና መቅረፅን የሚችልበት። ስለዚህም ከህዝቡ ጋር ተጣብቆ እሱ የሚያዘውን ለመተግበር መጣርና በቀጣይ ግምገማዎች እራስን መፈተሽ አማራጭ የሌለው መፍትሄ አድርጎ ወስዶታል።

እነዚህ ሂደቶች ህወሓትን የታደጋት ይመስላል።

አንዳንዶች የዚህን ስብሰባ ስኬት ወደ ማዕከላዊ ኮሚቴው ተመልሰው ለመጡት የተወሰኑ የቀድሞው አመራሮች ሲሰጡ ይታያል። እንደ እውነቱ ከሆነ የእነዛ የቀድሞው አመራሮች አስተዋፅዖ ቀላል የሚባል ባይሆንም በዋነኝነት የሂደቱ ባለቤቶች ግን የማዕከላዊ ኮሚቴው አባላቶች ናቸው። እነኚህ አባላት ሙሉ በሙሉ ለለውጥ ሂደቱ ፈቃደኛ ባይሆኑ ኖሮ ሌላው ቢቀር እንቅፋት መሆን ይችሉ ነበር። ስለዚህም ስኬቱ የጥቂቶች ሳይሆን የምልዓተ ጉባዔተኛው ነው።

እንግዲህ ዋናው መመዘኛ የሚሆነው በቀጣይ የምናያቸው ስራዎች ናቸው። ሌሎች ድርጅቶችም ይጠቅመኛል ካሉ የህወሓትን መንገድ ሊከተሉ ይችላሉ። ነገር ግን ህወሓቶች ይኸው በአርባኛው አመታችን እራሳችንን አድሰን ከፍ ብለን መብረሩን ጀምረናል ይላሉ።

እርስዎ ምን ይላሉ? አስተያየቶትን ያጋሩን። (EthiopiaFirst@gmail.com)

Leave A Reply

Your email address will not be published.