ኖርዌይ ለኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ከአንድ ቢሊየን ብር በላይ ድጋፍ አደረገች

(ኤፍ ቢ ሲ)- ኖርዌይ ኢትዮጵያ ለምታከናውነው የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ማስፈጸሚያ የ1 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ድጋፍ አደረገች።

የድጋፍ ስምምነቱን የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ትብብር ሚኒስትር ዲኤታ አቶ አድማሱ ነበበ እና በኢትዮጵያ የኖርዌይ አምባሳደር አንድሬስ ጋርደር ተፈራርመዋል።

ሚኒስትር ዲኤታው በዚህ ወቅት እንዳሉት፥ የገንዘብ ድጋፉ በደቡብ፣ ጋምቤላና ኦሮሚያ ክልሎች የተራቆቱ አካባቢዎችን ለመንከባከብና የአፈር መሸርሸርን ለመከላከል ጥቅም ላይ ይውላል።

ኢትዮጵያ የካርበን ልቀትን በመቀነስና የአየር ንብረት ለውጥን በመቋቋም እ.ኤ.አ. በ2025 መካከለኛ ገቢ ያላት ሃገር ለመገንባት ያላትን ራዕይ ለማሳካት የኖርዌይ መንግስት ድጋፍ እያደረገ መሆኑንም አቶ አድማሱ ተናግረዋል።

በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመንም፥ ለደን ጭፍጨፋ፣ መሬት መራቆት እና የባዮ ጋዝ ልቀትን መከላከል ስራዎች ትኩረት በመስጠት አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት ጥረት እያደረገች እንደሆነም ገልጸዋል።

የባዮ ጋዝ ልቀትን መከላከል ስራዎች የተደረገው ድጋፍ በደን መጨፍጨፍና በመሬት መራቆት የሚመጣውን የካርበን ልቀት ለመቀነስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለውም ነው የተናገሩት።

ኢትየጵያ የአረንጓዴ ልማት ኢኮኖሚ ለመገንባት ለምታደርገው ጥረት፥ ኖርዌይና ሌሎች አጋር ድርጅቶች የሚያደርጉት ድጋፍ ቀጣይነት አስፈላጊ እንደሆነም አንስተዋል።

በኢትዮጵያ የኖርዌይ አምባሳደር አንድሬስ ጋርደር በበኩላቸው፥ የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ በአካባቢ ጥበቃና የአየር ንብረት ለውጥ ስራዎች ላይ የሚያደርገው እንቅስቃሴ ለሌሎች ሃገራት አርዓያ የሚሆን ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን በመቋቋም አረንጓዴ ልማት ለመገንባት የሚደረግላትን ድጋፍ በትክክል ለታለመለት አላማ በማዋል ረገድም መሪ እንደሆነች ጠቁመዋል።

ሃገራቸው ኢትዮጵያ የጀመረችውን የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ለመደገፍ መስራት እንደምትፈልግ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የአረንጓዴው ልማት ስትራቴጂዋን በትክክል በመተግበር የካርበን ልቀትን መቀነስ የምትችልበት ተስፋ ሰጭ እንቅስቃሴ እያደረገች መሆኑንም አስረድተዋል።

የኖርዌይ መንግስት ኢትዮጵያ በአካባቢ ጥበቃ ዘርፍ ለያዘችው የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ያደርጋልም ነው ያሉት።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.