አርማ ያላረፈበት የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማን መያዝ እኩልነትን ያለመቀበል መገለጫ ነው -የተለያዩ ብሄር ተወላጆች

(ኢዜአ)- አርማ ያላረፈበት የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማን መያዝ የብሔር ብሔረሰቦችን እኩልነት ያለመቀበል አንዱ መገለጫ መሆኑን የተለያዩ ብሄር ተወላጆች ተናገሩ።

የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ከላይ አረንጓዴ ፣ ከመሃል ቢጫ፣ ከታች ቀይ ሆኖ በመሐሉ ብሔራዊ አርማ እንደሚኖረው በህገ መንግስቱ አንቀጽ 3 ንኡስ አንቀጽ 2 ተደንግጓል።

በሰንደቅ አላማው ላይ የተቀመጠው ብሔራዊ አርማ የኢትዮጵያ ብሔሮች ፣ ብሔረሰቦች ፣ሕዝቦች እና ሃይማኖቶች በእኩልነትና በአንድነት ለመኖር ያላቸውን ተስፋ የሚያንፀባርቅ መሆኑን ይገልፃል፡፡

ነገር ግን ኢትዮጵያ ቀደም ሲል በተለያዩ ስርአቶች  ስትጠቀምባቸው የነበሩና በአሁኑ ሰአት በህግ የተከለከሉ አርማዎች ያለባቸው ሰንደቅ አላማዎችን ይዘው የሚገኙ ግለሰቦች የእኛን እኩልነት የማይቀበሉ ናቸው ሲሉ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ የተለያዩ ብሄር ተወላጆች ይናገራሉ።

የጉራጌ፤ ወላይታ፤ ጋሞ፤ ኦሮሞና አማራ ብሄር ተወላጆች ጉዳዩን አስመልክቶ በሰጡን አስተያየት  በህገ መንግስቱ የጸደቀውና መሃሉ ላይ የብሄር ብሄረሰቦችን እኩልነትና ተስፋን የሚያንጸባርቅ አርማ ያረፈበት ሰንደቅ አላማ የነጻነታችን መገለጫ ነው ብለዋል።

ይህንን ድንጋጌ በመሻር የተለያየ አርማ ያላቸውና አርማ የሌለው ሰንደቅ አላማዎችን ይዘው የሚገኙ ግለሰቦች በብሔር እኩልነት የማያምኑና ነጻነታችንን የሚሽሩ ናቸው ይላሉ።

የጋሞ ብሔር ተወላጅ አቶ መክብብ ኬኒቶ እንደሚሉት ባንዲራችን የብዙ ብሔር ብሔረሰቦች ቋንቋ፤ የሃይማኖት እንዲሁም የብሔረሰቦችን እኩልነት ያመላከተ በመሆኑ ለኔ ነጻነቴ ነው።

አርማ ያላረፈበትን ሰንደቅ አላማ ይዘው የሚገኙት ግን የአንድን ብሔርና ሃይማኖት የበላይነት የሚፈልጉ  ናቸው የሚል ሃሳብ አላቸው።

ሌላዋ አስተያየት ሰጪ የአማራ ብሔር ተወላጅ የሆኑት ወይዘሮ አስቴር ለማ ሰንደቅ አላማችን በህገ መንግስቱ ህዝቡ አምኖበት የጸደቀ በመሆኑ የማንነታችን መገለጫ ነው ብለዋል።

“ሰንደቅ አላማ ሲሰቀልና ብሔራዊ መዝሙር ሲዘመር የኔን ብሔር ጨምሮ ሁሉንም በውስጡ አያለሁ” የሚለው ደግሞ የጉራጌ ብሔረሰብ ተወላጁ ወጣት መሰለ ይትባረክ ነው።

የዛሬዋ ሰንደቅ አላማ ለብሔሮች እኩልነት መስዋዕት የተከፈለበት በመሆኑ የነጻነት ተምሳሌት፤ የማንነታችን መገለጫ ነው፤ ይህን እኩልነት የማይቀበልና ብሄር ብሄረሰቦችን የማይወክል ሰንደቅ ዓላማ ይዞ መገኘት ማንነታችንን መርገጥ ነው የሚል ሃሳብ ሰጥቷል።

በመሆኑም በህገ መንግስቱ ከጸደቀው ሰንደቅ አላማ ውጪ ይዞ መገኘት አጠቃላይ የኢትዮጵያን ህዝቦች ማንነት አለመቀበል በመሆኑ ለሰንደቅ አላማ ተገቢውን  ክብር መስጠት አለብን የሚል አስተያየት ሰጥቷል።

የወላይታ ብሔረሰብ ተወላጁ ኮሎኔል ብርሃኑ መርጋ የአብዛኛውን ህዝብ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጠውን ሰንደቅ አላማ መቀበል ይገባል ብለዋል።

የኦሮሞ ብሔረሰብ ተወላጅ ወጣት ደሳለኝ ሃይሉ እንደሚለው ደግሞ በማህበራዊ ድረ ገጾችና በተለያዩ የመረጃ ምንጮች በሰንደቅ አላማ ላይ የተለያዩ ሃሳቦች ይሰጣሉ።

በመሆኑም መንግስት የግንዛቤ መፍጠር ተግባር በተጠናከረ መልኩ ሊሰራ ይገባል ብሏል።

ወጣቱ ትውልድም ከመሰል ድርጊቶች ተቆጥቦ መስዕት ለተከፈለለትና በህገ መንግስቱ እውቅና ለተሰጠው  ሰንደቅ አላማ መጠበቅ አለበት የሚል ምክር ይሰጣል።

አስረኛው የሰንደቅ አላማ ቀን የፊታችን ሰኞ በአገር አቀፍ ደረጃ ይከበራል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.