አስቸኳይ የምግብ እህል ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች ድጋፍ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው-ም/ጠ/ሚ ደመቀ

(ኤፍ ቢ ሲ)- አስቸኳይ የምግብ እህል ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች ድጋፍ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የኢፌዲሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ተናገሩ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሀገሪቱ ቆላማ እና አርብቶ አደር አካባቢዎች ከተከሰተው ድርቅ ጋር በተያያዘ በሰብዓዊ ድጋፍ ዙሪያ ከልማት አጋር ድርጅቶች ተወካዮች ጋር በጽህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል፡፡

በውይይቱ ላይ ቀደም ሲል ከኤልኒኖ የአየር ንብረት ለውጥ ክስተት ጋር በሀገሪቱ የተፈጠረውን የከፋ የድርቅ አደጋ ለመከላከልና ለመቆጣጠር መንግስት ከፍተኛ ርብርብ ማድረጉን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ አስታውሰዋል፡፡

ከኤልኒኖ ክስተት ማግስት በኢትዮጵያ ቆላማና አርብቶ አደር አካባቢዎች በተፈጠረው የድርቅ አደጋ ምክንያት አንድም ዜጋ ህይወቱ እንዳያልፍ አስፈላጊውን ሁሉ ለማድረግ መንግስት ሁልጊዜ ዝግጁ እንደሆነ ነው ያስረዱት፡፡

በበልግ ዝናብ መዛባትና በእንስሳት መኖ እጥረት ምክንያት አስቸኳይ የምግብ እህል ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች አስፈላጊውን ሁሉ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው ያሉት አቶ ደመቀ፥ የልማት አጋር ድርጅቶች ተሳትፏቸው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በውይይቱ ላይ የተካፈሉት የልማት አጋር ድርጅቶች ተወካዮች በበኩላቸው፥ ከድርቁ አደጋ ጋር በተያያዘ መንግስት ዜጎቹን ለመታደግ የሚያደርገው ጥብቅ አመራርና የማይዋዥቅ ቁርጠኝነት የሚደነቅ ነው ብለዋል፡፡

ከዚህ በፊት በአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍና ትብብር ማዕቀፍ መንግስት ለሚያቀርባቸው ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት ጥረት ማድረጋቸውን አስታውሰዋል፡፡

ተወካዮቹ በቀጣይም በሚኖረው የድጋፍና የትብብር ማዕቀፍ ተግባራዊ ምላሻቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ማረጋገጣቸውን የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት አስታውቋል፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.