አባይ ኢንዱስትሪ ልማት አክሲዮን ማህበር በ7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር የሲሚንቶ ፋብሪካ ሊገነባ ነው

(ኢዜአ)- አባይ ኢንዱስትሪ ልማት አክሲዮን ማህበር በ7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ወጭ ለሚያስገነባው ሲሚንቶ ፋብሪካ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ ባለስልጣናት በተገኙበት የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ።

በደጀን ከተማ አካባቢ ልዩ ስሙ ኮንቸር ሳሳበራይ እና ሜንጅየበዛ ቀበሌዎች የሚገነባው ፋብሪካ ሲጠናቀቅም ለ1ሺህ 690 ሰዎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ አድል ይፈጥራል ተብሏል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ዛሬ የመሰረት ድንጋዩን ባስቀመጡበት ወቅት እንደገለጹት ፋብሪካው የኢንዱስትሪ ልማት ሽግግርን ከማፋጠን ባሻገር መዋቅራዊ ለውጥ ለማማምጣት የሚያስችል ነው።

አክሲዮን ማህበሩ ባጭር ጊዜ ውስጥ ራሱን በማደራጀት ለሚገነባው ስሚንቶ ፋብሪካ 250 ሄክታር መሬት ከሶስተኛ ወገን ነጻ በማድረግ በኩል ከአካባቢው መስተዳድሮች ጋር መስራቱን ተናግረዋል።

ለፋብሪካው ጥሬ እቃ ማምረቻ የሚውል 3ሺህ 600 ሄክታር ቦታ በአባይ ሸለቆ የተፈቀደለት ሲሆን ከአካባቢው ልማት ጋር ተጣጥሞ እንዲሄድ አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግም አስረድተዋል።

የፋብሪካው ግንባታም በአራት ዓመት ከአራት ወራት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ የገለጹት ደግሞ የአማራ ክልል ንግድ፣ ኢንዱስትሪና ገበያ ልማት ቢሮ ሃላፊና የፋብሪካው የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ጌታቸው ናቸው።

“ፋብሪካው ተገንብቶ ሲጠናቀቅም በቀን 5ሺህ ቶን ሲሚንቶ በማምረት የክልሉንና የአገራችንን የመሰረተ ልማት ለማሟላት የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ ነው”ብለዋል።

በግንባታና በማምረት ሂደት ለበርካታ ወገኖች የስራ እድል ከመፍጠሩም በሻገር ባለሃብቶች ተደራጅተው ምርቱን በማቅረብና በሌሎች ተማሳሳይ የኢንዱስትሪ ዘርፎች እንዲሰማሩ በር የሚከፍት እንደሆነም አመልክተዋል።

የፋብሪካው ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድረስ አስፈላጊው የሙያ፣ የክህሎትና ሌሎች ድጋፎች  እንደሚደረግለት ጠቁመው የትርፋማነት ምጣኔውም ከ22 በመቶ በላይ መሆኑን በጥናት መረጋገጡን አስረድተዋል።

የምስራቅ ጎጃም ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተመስገን ጥሩነህ በበኩላቸው ፋብሪካው በደጀን ከተማ አቅራቢያ መቋቋሙ “በስራ እድል ፈጠራና አርሶ አደሩን በማደራጀት በቀላል ኢንዱስትሪ ዘርፎች ለማሰማራት ያስችላል” ብለዋል።

በዚህም ለግንባታና ጥሬ እቃ ማምረቻ የሚሆነውን ቦታ ለማስለቀቅ በተካሄደ ተከታታይ ውይይትና ምክክር ከማህበረሰቡ ከፍተኛ ድጋፍ ስለተቸረው ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር ተጣጥሞ በመስራት ውጤታማ እንደሚሆን ገልጸዋል።

በመሰረት ድንጋይ መጣሉ ስነ-ስርዓት ላይ የኢፌዲሪ ፕላን ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ይናገር ደሴን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የፌዴራልና የክልል ባለስልጣናት ተገኝተዋል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.