አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ 4 ተከሳሾች የችሎት የቃል ትዕዛዝ አልቀበልም በማለታቸው በ6 ወር ቀላል እስራት ተቀጡ

(ኤፍ.ቢ.ሲ)- አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ አራት ተከሳሾች የችሎት የቃል ትዕዛዝ አልቀበልም በማለት በድጋሚ በ6 ወር ቀላል እስራት ተቀጡ።

የቅጣት ውሳኔውን ያሳለፈው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አራተኛ ወንጀል ችሎት ነው።

በ6 ወር ቀላል እስራት የተቀጡትም አቶ በቀለ ገርባ፣ አቶ ደጀኔ ጣፎ፣ አቶ ጉርሜሳ አያኖ እና አቶ አዲሱ ቡላላ ናቸው።

ተከሳሾቹ ፍርድ ቤት ችሎት ለ30 ደቂቃ ስራውን እንዳያከናውን አድርገዋል እና የተሰጣቸውን የቃል ትእዛዝ አልተቀበሉም በሚል ነው የቅጣት ውሳኔውን ያሳለፈባቸው።

ፍርድ ቤቱ በተከሰሱበት ወንጀል ፍርድ ለመስጠት ለዛሬ ቀጠሮ መያዙ ይታወሳል።

ይሁን እንጂ ተከሳሾቹ የስም ዝርዝራቸው በችሎት ሲጠራ እና እንዲነሱ ሲታዘዙም አንነሳም በማለት ትእዛዙን ያልተቀበሉ ሲሆን፥ በዚህ የተነሳም ችሎቱ ለ30 ደቂቃ ቆይቷል።

ተከሳሾቹ ባሳለፍነው ጥር 5 2010 ዓ.ም በመከላከያ ምስክርነት ይቅረቡልን ብለው በጠየቋቸው ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ጉዳይ ላይ ፍርድ ቤቱ መቅረባቸው ተገቢ አይደለም ብሎ ትእዛዝ መስጠቱን ተከትሎ ባሰሙት ተቃውሞ ችሎቱን በማወካቸው እና በሌሎች ድርጊቶች የ6 ወር ቀላል እስራት ተላልፎባቸው እንደነበረ ይታወሳል።

ፍርድ ቤቱ ተከሳሾቹ ላይ ፍርድ ለመስጠት ለዛሬ ይዞት የነበረውን ቀጠሮ ለየካቲት 28 2010 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.