አንዲት ታጋይን በማስታወስ

(ኡስማን ሰዒድ) – እኔና ጋዜጠኛ ጓደኞቼ በትግራይ ተገኝተናል፡፡ ወቅቱ የካቲት 11 በዓል የሚከበርበት እና ልዩ ልዩ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች የሚጐበኙበት እንዲሁም አዳዲስ መሠረት የሚጣልበት በመሆኑ ከልዩ ልዩ ሚዲያዎች የተጋበዙ ጋዜጠኞችን ብዙ ወደሚባልላት መቀሌ ከተማ ገብተን ዞር ዞር ማለት ይዘናል፡፡

በእንግዳ ተቀባይነቱ እና ትሁት አንደበቱ የሚታወቀው የመቀሌ ነዋሪ ጋር ለመላቀል ሻሂ ቡና ለማለት ሲያልፍም እስክስታ ለመውረዱ ጊዜ አልፈጀብንም፡፡ መቀሌ በገባን በሁለተኛው ቀን የሚከበረው የካቲት 11 በዓል 550 ለሚሆኑ ሁለት እና ከዚያም በላይ ውድ ልጆቻቸውን እና ቤተሰቦቻቸውን ላጡ አረጋውያን የምስጋና እና የዕውቅና ዝግጅት ለመታደም ወደ ሀውልቲ አዳራሽ አመራን፡፡

አዳራሹ በህወሓት አርማ አጊጧል፡፡ የክልሉን ፕሬዚዳንት ጨምሮ ከብአዴን እና ከልዩ ልዩ ድርጅቶች የተጋበዙ እንግዶች በታደሚነት ከፊት ለፊት ቁጭ ብለው ይታያሉ፡፡ ከነሱ በላይ ግን አዳራሹን የሞሉት ከትግራይ ገጠሮች የተሰባሰቡ ልጆቻቸውን በመስዋዕትነት ያጡ በእድሜ የገፉ እናቶች እና አባቶች እንደነገሩ ለብሰው አዳራሽ ውስጥ ሲታዩ በመንፈሳችን ላይ የሚፈጥረው የራሱ የሆነ ጫና አለ፡፡

በዚህ መሐል አራት ልጆቻቸውን በትግሉ፣ ያጡ አምስት ልጆቻቸው እንደወጡ ያልተመለሱ በርካታ እናቶች እና አባቶች ስማቸው እየተጠራ የትግራይ ህዝብ የፅናት እና የድል ባለቤቶች እነሱ እንደሆኑ በመግለፅ የሕወሓትን አርማ ጨምሮ መቀሌ የሚገኘውን ሀውልት የሚያሳይ ዋንጫ እና ልዩ ልዩ ሽልማቶች ይበረከትላቸው ጀመረ፡፡

በመቀሌ ቆይታዬ በጣም ካስደነቁኝ ባለሙያዎች መካከል በወቅቱ መድረኩን ይመራ የነበረው ወጣት ጋዜጠኛ ረዘም ያለ እና አዳራሹን ወደ ዕንባ ዕልህ እና ትውስታ የመለሰ ግጥም ማንበብ ጀመረ፡፡ በግጥሙ የተደመሙ አረጋውያን እናቶች እና አባቶች ከሌላቸው ብር ላይ ሀምሳ ብር፣ አስር ብር፣ መቶ ብር እየመዘዙ ይሻልሙት ጀመር፡፡ ገጣሚውም የዋዛ አልነበረም የሞተው ደርግ እንጂ ታጋዩ አይደለም የሞቱት ሰማዕታት ሞትን አሸንፈው እንዳለፉ እየጠቀሰ አደራሹን በጋለ ስሜት አቀጣጠለው፡፡

አዳራሽ ውስጥ የተሰበሰበው ሕዝብ በእልልታ በለቅሶ እና ፍፁም ይህ ነው ተብሎ ሊገለፅ በማይችል የተቀላቀለ ስሜት ውስጥ በተዋጠበት ስሜት ላይ ነበረ ለዚህ ፅሑፍ መፃፍ ምክንያት የሆነች አንዲት ታጋይ ወደ መድረኩ ያመረችው፡፡

ታጋይዋ እናቶች የሚለብሱትን የአዘቦት ቀሚስ ለብሳለች፡፡ ነጠላዋን ደግሞ በሀዘን ወቅት ላይ እንደሚለበሰው አለባበስ በአጭር ታጥቃዋለች፡፡ በቀጥታ ወደ መድረኩ ስትሄድ ለገጣሚው ያላትን ክብር ለመግለፅ እና በዚያውም ለመሸለም ነበረ የመሰለኝ፡፡ ፊቷን አዳራሽ ውስጥ ወደታደሙ ከፍተኛ አመራሮች እና በሺ የሚቆጠሩ የሰማዕታት ቤተሰቦች መለስ አድርጋ ስታበቃ ልክ መቃብር ፊት ለፅሞና ፀሎት እንደሚንብረከክ ሰው ተንበርክካ የራሷ ዓለም ውስጥ ገብታ ጭልጥ አለች፡፡ አይኗን ጨፍናዋለች፡፡ እጆቿን አጣምራለች፡፡ አንድ ተዋናይ በትወና ሊያሳየው ከሚችለው ተመስጦ (ፖዝ) በላይ ድርቅ ብላ ቀረች፡፡ በአጭሩ ራሷ ሀውልት የሆነች መሠለች፡፡

ገጣሚው ንባቡን ቀጥሏል፡፡ ታዳሚው መሸለሙን አላቋረጠም፡፡ በታጋይዋ ሁኔታ ልባቸው የተነካ እናቶች እና አባቶች ገጣሚውን ከመሸለም አልፈው እንባቸውን እያበሱ የታጋይዋን ትከሻና ራስ ከመዳበስ ባሻገር ሽልማትም ሸጐጥ ማድረግ ጀመሩ፡፡ ታጋይዋ ግን ይህ ድርጊት ከተሰዉ ጓዶቿ ጋር የያዘቸውን ወግ የሚያቋረጥባት በመሆኑ የወደደችው አይመስልም፡፡ በተሸለመች ቁጥር ብሩን ከንገቷ ስር እያነሳች ወደ መሬት መጣል ያዘች፡፡ “እባካችሁ ከጓዶቼ ጋር ልሁንበት” የምትል ትመስላለች፡፡

የሆነስ ሆነና በዚያች ቅፅበት ታጋይዋ ምን እያሰበች፣ ምን እያየች፣ ማንን እያናገረች የትኛው አውደ ግንባር እየታወሳት ስንት አጠገቧ የወደቁ ጀግኖች ከፊቷ ድቅን ብለው ይሆን፡፡ ይህን መሰል የግሪክ ትራጄዲ ቲያትራዊ ትዕይንትስ እንዴት መፍጠር ተቻላት? አዳራሽ በሞላ ህዝብ ፊት በአጭር ታጥቆ የመቃብር ሀውልት ፊት እንደመንበርከክ ያለ ሀሳብስ ከወዴት ተከሰተላት፡፡ ግራ ገባኝ ነገሩ ካሁን ቀደምም የተለመደ ይሆን እንዴ? አልኩኝ፡፡ እንጃ፣ ብቻ ከግጥምም ሆነ ከረጅም ንግግር የበለጠ የታጋዮቹን መስዋዕትነት በውስን ድምፅ አልባ እንቅስቃሴ ጐልቶ እንዲሰማኝ እና እንዲታየኝ በማድረጓ የዚህች ታጋይ ቆፍጣና ገፅታበመቀሌ ቆይታዬ ከአዕምሮዬ ሊፋቁ ከማይችሉ ትዕይንቶች አንዱ ሆኖ ታትሟል፡፡ የትግራይ ቴሌቭዥን ጋዜጠኞች ይህችን ታጋይ በማነጋገር ማንነቱን የትግል ተሞክሮዋን እና ልታስተላልፍ የፈለገችውን መልዕክት ይዘውልን እንደሚቀርቡ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.