አየር መንገዱ ኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ማእከልነቷን እንድታስቀጥል ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ መሆኑ ተገለፀ

(ኤፍ.ቢ.ሲ)- የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ማእከልነቷን አስጠብቃ እንድትቀጥል ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለፀ።

130 ኤምባሲዎች እና 40 አለም አቀፍ ድርጀቶችን ኢትዮጵያን መቀመጫቸው ያደረጉ ሲሆን፥ በሀገሪቱ ያለው ምቹ እና ቀልጣፋ የአየር ትራንስፖርትም ሀገሪቱን ተመራጭ አድርጓታል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም፥ አየር መንገዱ ኢትዮጵያን ከሌላው አለም ብቻ ሳይሆን አፍሪካን በሙሉ ከሌሎች አህጉራት ጋር የማገናኝት ስራ እየሰራ ነው ይላል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አክሊሉ ሀይለሚካኤል ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ የአየር መንገዱ ፈጣን አገልግሎት ከኒውዮርክና ጄኔቫ በመቀጠል በአለም 3ኛ የዲፕሎማሲ ማዕከል ለሆነችው ኢትዮጵያ አበርክቶው ከፍ ያለ መሆኑንም ተናግረዋል።

አየር መንገዱ በወጭ ንግድና በኢንቨስትመንት እንዲሁም በቱሪዝም ዘርፍም የበኩሉን እየተወጣ ያለ ድርጅት መሆኑንም ዶክተር አክሊሉ ተናግረዋል።

ዘርፉ ለቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት ድጋፍ በማድረግ በተለይም በሀገሪቱ መዋዕለ ንዋያቸውን ማፍሰስ የሚፈልጉ የውጭ ባለሃብቶችን የትራንስፖርት ጥያቄ መልስ የሰጠ ድርጅት እንደሆነም አንስተዋል።

በአጠቃላይ በዲፕሎማሲ አቅም ግንባታ፣ የቱሪስት መስህቦችን በማስተዋወቅ እና ለዘርፉ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር በሀገሪቱ የገጽታ ግንባታ ላይ ሰፊ አሻራውን እያሳረፈ ያለ ትልቅ ኩባንያ መሆኑንም ዶክተር አክሊሉ ያብራራሉ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዛሬ ላይ 110 አለም አቀፍ መዳረሻዎች፣ 96 አውሮፕላኖች እና ከ2 ሽህ 500 በላይ የበረራ አስተናጋጆችም እንዳሉት መረጃዎች ያሳያሉ።

ይህም አየር መንገዱ በ2025 እደርስበታለሁ ብሎ ካሰቀመጠው የ120 አውሮፕላኖች ባለቤት የመሆንና 90 አለም አቀፍ መዳረሻዎች ግብ አንጻር አብዛኛውን ዛሬ ላይ ማሳካት የቻለበት አቅም መፍጠሩን ያመላክታል።

በዚህ ስኬቱም ባለፉት ተከታታይ ሰባት ዓመታት ከአፍሪካ ግዙፍ ብቻ ሳይሆን በሁሉም መስክ በአንደኝነት ደረጃ ስሙን አስጠብቆ መዝለቅ ችሏል ይላሉ የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም።

እዚህ ደረጃ ለመድረስ ሁሉም ነገር አልጋ ባልጋ አልነበረም የሚሉት አቶ ተወልደ፥ ለአየር መንገዱ ስኬት አለሀ አስጨራሽ ጉዞ ጠንካራ የስራ ባህል አና የአመራር ጥንካሬን አስቀድመዋል።

በመንግስት በኩል ለበረራ ምቹ ሁኔታን በመፍጠር፣ ስትራቴጅክ እቅዶች ላይ ድጋፍ በማድረግ እና በማበረታታት የሚደረጉ ድጋፎችም አስተዋጽኦቸው ቀላል አንዳልሆነ ጠቁመዋል።

አየር መንገዱ በቀጣይ ሶስት ወር 9 አዳዲስ አለም አቀፍ መዳረሻዎች ይኖሩታል እንደሚኖሩትም አቶ ተወልደ ተናግረዋል።

መዳረሻዎቹም ከአፍሪካ የማዳጋስካሯ ነሲቦ ከተማ እና የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ኪሳጋኒ እና ባጁማ የሚገኙበት ሲሆን፥ የፖርቹጋሏ ሊዝበን እና የስዊዘርላንዷ ጀኔቫ፣ ጃካርታ እና ሽንዘን ከእሲያ እንዲሁም የቱርኳ ኢስታንቡል በአየር የመዳረሻ ከተሞች ናቸው።

ከዚህ በተጨማሪ አየር መንገዱ አመታዊ ገቢውን አሁን ካለበት 3 ቢሊየን ዶላር ወደ 10 ቢልየን ዶላር ለማሳደግ እና 1 ቢልየን ዶላር አመታዊ ትርፍ ለማግኝት በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝም አቶ ተወልደ ገልፀዋል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.