አዲስ ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ያስፈልጋል!

(አባዲ ከሾላ ) – አሁን ኢህአዴግ ከመቼውም በባሰ ዝቅጠት ውስጥ ነው! የትኛውም፡ የመቼውም ችግር ከአሁኑ ድርጅታዊ ችግር አይወዳደርም!፡፡ መቼም እና እንዴትም ታስቦ በማያውቅ እና ሊታሰብ በማይችል ሁኔታ ኢህአዴግ በስብሷል፡ ሸቷል !!?

ግን ምን ዋጋ አለው! ስንት የራሱ አሽከር አመራር ባለበት  ʿ ስልጣንን ለግል ጥቅም የማዋል ዝንባሌ አለ ʾ  ብሎን እርፍ!  ዝንባሌ!?  ዝንባሌ ምንድን ነው? ማዘንበል ማድረግ ነው መፈለግ? ዝንባሌ ድርጊት ነው አስተሳሰብ?

ቢያንስ መቼም ሆኖ በማያውቅ  ሁኔታ ለአንድ ዓመት ያህል በታወጀ  የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት እንኳ፤ በጥልቅ ችግሬን ፈትሼ  በጥልቅ ልታደስ ነው በሚልበት በዚህ ወቅት እንኳ እየተደረገ ነው ብሎ ለማመን የሚያስቸግር ድፍረትና መበስበስ እያየን ነው፡፡

ኢህአዴግ ጉዞውን ጨረሰ?? ነው እየበሉ እና እያስበሉ መቀጠል ይቻላል? የ77 እና 97 የህወሓት ልዩነት በስንት ጣዕሙ!  አንጃ የተባሉት ታጋዮች ጥፋት በስንት ወዘናው! የነ ታምራት ላይኔ ስርቆት አሁን ከነማን ይወዳደር!?

በአንድ ወቅት ባንኮች አንድን ዶላር በሶስት ብር እንደሚመነዘሩ ደርሰንበታል ያለን፤ እስር ቤት ያላቸው ባለሃብቶች  እንዳሉ የነገረን ተተኪ ጠቅላይ ሚኒስትር በምን አስማት ነው እንደገና መረጃ የለንም ፤ዝንባሌ ነው የምንባለው? መልሶ 100 ሚሊዮን ብር ለጎሳ አከፋፍሎ የበላ ክልል አለ ያለን ጠቅላይ ሚኒስትር ነገ ማስረጃ አምጡ ይለን ይሆን? ዱባይ፤ አውሮፓና አሜሪካ የልጅ ውርስ መኖሪያ ገንብተው ስላሉት ባለስልጣናት እና ባለሃብቶች አላውቅም ነው የሚለን? ይሔ የመረጃና ደህንነት ኃይሉን መናቅና መሳደብ ነው!

ያለ ጥርጥር  ዛሬ ኢህአዴግነት ፀረ-ኢትዮጵያዊነት ሆኗል! ኢህአዴግነት ዛሬ ፀረ-ህዝብነት ሆኗል! ዛሬ ኢህአዴግነት ፀረ-አንድነት ነው! ነባር የሚባል ወታደራዊ sመኮንንም ይሁን ፖለቲከኛ በወጉ ያልቀበራቸውን የበረሃ ጓዶችን ገድል እና አደራ እንደ አንድ የሆሊውድ አክሽን ፊልም ተርኮ የተገላገለ ከሃዲ ነው! የዛሬው ተተኪ ተብዮ ኢህአዴግ በአካባቢያዊ አስተሳሰብ እና ዝርፊያ የሰለጠነ የሃሳብ ድሃ ነው፤ ንግድም ሆነ ትምህርት አልሆን ብሎት በኢህአዴግ ስም አገራችን ላይ የተጣበቀ መዥገር ነው!፤ የዛሬው ኢህአዴግ የመርህ መፅሓፉን ከመለስ ዜናዊ ጋር የቀበረ የዘራፊ መንጋ ነው! የዛሬውን ኢህአዴግ ዓይነት የአገር አመራር ማንኛውም ኃይል፤ የትኛውም ኃይል ቢሆን ይችላል! የአሁኑ ኢህአዴግ እንደማንም ነው!

እናም መፅሓፉን ከመቃብር አውጥቶ በህዝባዊነትና ዴሞክራሲዊነት የሚተገብር የልማታዊ ዴሞክራሲ ኃይሎች ፓርቲ መመስረት አለበት!

Leave A Reply

Your email address will not be published.