ኢህአዴግና መጪው የአካል ጉዳተኝነት አደጋ

(ሰላምወርቅ ሁላገር) – ውድ የተከበራቹ አንባብያን ሆይ በአይጋና ሌሎች ድረ ገጾች እንዲሁም አንድ መጽሔት ላይ ኢህአዴግ ከቸልሲ ምን ይማር እንዲሁም የፖለቲካ ኤሊኖ በኢህአዴግ በሚሉ ስሜቴን ለመግለጽ በሞከርኩባቸው ጽሁፎቼ ተገናኝተን ነበር፡፡ ጽሁፎቹን ተከትሎ በኢ-ሜይልና ፌስቡክ አድራሻየ ከጠበቅኩት በላይ ገምቢ የድጋፍና የትችት መልእክቶች ደርሰዉኛል። ለሁላችሁም ምስጋናዮ ከፍ ያለ ነው።ይሁንና ሁለት የኢ-ሜይል መልእክቶች በፃፍኩት ሀሳብ ሳይሆን በማንነቴ ዙርያ የሂስ ይዘት ያላቸው ለየት ያሉ ስለሆኑ ባካፍላቹ የተሻለ ነው ብየ አመንኩ።የሁለቱ ሃሳብ በይዘታቸው አንድ ሆነው አንደኛው “አንተ አማራ አይደለህም ትግሬ ይመስለኛል” የሚል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ “አንተ በትውልድ ትግሬ ሆነህ የብአዴን አመራር ነህ” ብሎ ስም በመጥቀስ አስተያየቱን አድርሶኛል። እኔ ለማለት የሞከርኩት አገር በእንዲህ አይነት አደጋ ውስጥ ናት እና ከእጃችን ሳታመልጥ እናድናት ነው። እንዲህ ያለ የአገር እናድን ጥሪ የአማራው ሃሳብና ጭንቀት ሊሆን አይችልም ያለው ማን ነው? የሚል ጥያቄ በማቅረብ ትላንት ዛሬ ነገና ተነገ ወድያ በአማራነቴ እንደምኮራ መለስኩላቸው።

ዛሬ አዲስ ነገር ይዠ አልመጣሁም። ዛሬም ያለፉት አጀንዳዎች ከተወሰኑ ወቅታዊ ሁኔታዎች ጋር በማያያዝ የተወሰነ ነገር ለማለትና እንዳለፈው ግዜ ጭንቀቴ ለማጋራት ነው።የፅሁፉ መነሻ እየተካሄደ ያለው “ተሃድሶ” እኔም ሌላው ህዝብም በጠበቀው መንገድ እየሄደ አይደለምና ይስተካከል የሚል ነው።

የትግሬ የበላይነት የአገሪቱ ከፍተኛ የፖለቲካ አጀንዳ ሆኖ ስለመቀጠሉ፤

ከከላይ የገለፅኳቸው የሁለት ሰዎች አስተያየትና በቅርቡ በ”ተሃድሶ” ስም በየመስራቤቱ እየተካሄዱ ባሉ መድረኮች እየቀረቡ ካሉ ሃሳቦች ለመረዳት የሚቻለው በብሔራዊ ማንነትና ትርጓሜ የዚች አገር የዛሬና የነገ ሁኔታ ላይ ፍፁም የተዛቡ አመለካከቶች እንዲያዙ በማድረግ የትግሬ የበላይነትና የሌሎች ተበድለናል ስሜት እንዲፈጠር በማድረግ የዚች አገር ዋነኛ የፖለቲካ አጀንዳ ሆኖ እየታየ በመሆኑና እንደ አገር ያለው ስፋትና አደጋው ቀላል እንዳልሆነ ያሳያል።በመሆኑም ዛሬም በዚሁ ዙርያ የተወሰነ ማለት እንደሚያስፈልግ ስላመንኩበት የተወሰነ ልበል።

በአሁን ወቅት በአገራችን የአንድ ብሔር የበላይነት አለ ወይስ የለም የሚለው ከህገ-መንግስቱና አገሪቱ እየተከተለችው ስላለው የመንግስት ስርአት አይነትና አፈፃፀሙ በተመለከተ ባለፈው ጽሁፌ ለመግለጽ የሞከርኩት ስለመሰለኝ ዛሬ በዚህ ጉዳይ አላወራም።መነሻየ በአገሪቱ የትግሬም ሆነ የሌላ ብሔር የበላይነት የለም የሚል ሆኖ ታድያ ለምን ይህ አጀንዳ የወቅቱ የፖለቲካ አጀንዳ ማጠንጠኛ ሆነና እንዴት በዚህ ደረጃ ስፋት ሊያገኝ ቻለ የሚለዉን ለመዳሰስ እንሞክራለን።

በኔ እምነት አጀንዳው የተቀረፀው ከቅርብ አመታት ወዲህ ሳይሆን መነሻው ከአፄዎቹ ጀምሮ በዚህ ዘመን ደግሞ ደርግ ከወደቀ ማግስት ጀምሮ “የዚች አገር እጣ ፋንታ ከኛ በላይ የሚያውቅና የሚፈርድ የለም” የሚል እምነት ይዘው ህዝቡን ለበርካታ አሰርት አመታት “እገሌ ታላቅ ነው ከዚህ ውጭ ያሉ ደግሞ ቀጥለው የሚታዩ” እያሉ በተፈጥሮ

ታላቅ እንደሆነ የተነገረው ብሔር ይቅርና ሌላውም እንዲቀበል ያስገድደው የነበረ ስርአት አካሉ ከተቀበረና ቀድሞ ፍሬው አፍርቶ የተበነና ሌላ ክረምት ሲመጣ ተሎ የሚበቅልው አረም አይነት ራሱን እያባዛ የመጣው የአመለካከት ችግር ነው።ይህንን የብተና አመለካከት የሚወክሉ ሰዎችና ቡድኖች ከተቀበሩ በኋላ እንደ ቁልቋል ተክል ወይም እንደ ጤናአዳም የተቀረው ቁራጭ አካላቸው ማቆጥቆጥ ስለሚችልና ስለቻለ ኢህአዴግ ደግሞ እንደ ሰነፍ ገበሬ “አንዴ

አዝመራው ሰብስቤ አውድማ ላይ ከከመርኩት ችግር የሚባል ነገር የለም” በሚል እሳቤ የትምክህት ስርአት የመጨረሻ ተወካይ የነበረ ደርግ ከደመሰሰ በኋላ ለሚታዩ የአመለካከት ችግሮች ማቆጥቆጥ ተገቢው ግምት ሳይሰጥ እናንተ የተቀበረው ስርአት ርዝራዦች በሚል ድንፋታ ብቻ ለውጥ የፈጠረ እየመሰለው በቂ ግዜ ስላገኙ እንደሆነ ይሰማኛል።

የዚህ የትግሬ የበላይነት አጀንዳ ዋና አላማና ስትራቴጂ በውጭ ኃይሎች ፍላጎትና በአገር ውስጥ ኃይሎች ሽፋንና ዋና ስራ አስፈፃሚነት ኢህአዴግን ከስልጣን በማውረድ ስም አገር ለመበተን ሲሆን መስፈፀምያ ስልቱም ሌላው ህዝብ የሁሉም ችግር ምክንያት የትግራይ ህዝብ እንደሆነ እንዲያምን በማድረግ እንደጠላት እንዲመለከተውና አሁን ያለው መንግስትም የትግራይ መንግስት ነው በሚል ህዝብና መንግስት መለያየት መቻል የሚል ሲሆን የትግራይ ህዝብም ቢሆን ከመንግስት ለመነጠል ህዝቡ በሌላው ህዝብ ጥቃት እንዲደርስበት በማድረግ የትግራይ ህዝብ ደግሞ መንግስት ከጥቃት ስላላዳነኝ የኔ መንግስት አይደለም ብሎ በሌላ አቅጣጫና ምክንያት ከተቻለ በመንግስት እንዲያምፅ ካልሆነ ከመንግስት እንዲነጠል በማድረግ አገር መበተን ይቻላል የሚል ነው ተረቱ።ይህ እንዲሆን ሁሉም የስራ ክፍፍል በማድረግ ለአመታት ሲሰሩበት እንደቆዩ በግልፅ ስናየው የነበረ ነው። እነዚህ ኃይሎች ይህንን አስተሳሰብ ወደ ህዝቡ አእምሮ ዘልቆ እንዲገባ ገንዘባቸው፣ እውቀታቸው፣ጉልበታቸውና ግዜያቸው በሙሉ ሲያንቀሳቅሱ ቆይቷል።

የትግራይ ህዝብ እንደ ጠላት የሚያይ አስተሳሰብ በሌላው ህዝብ ዘንድ እንዲሰርፅ ለማድረግ በብተና ኃይሎች በየትምህርት ቤቶች፣መስራቤቶች፣የእምነት ተቋም፣ ካፌዎች፣እድሮች፣አዝማሪ ቤቶች፣ታክሲና ባስ መጠበቅያ ቦታዎች፣በተለያዩ የኮሜዲ፣የግጥምና ስነ ፅሁፍ በመሳሰሉ የኪነ ጥበብ ውጤቶችና በቤተሴብ ደረጃ የተሰራበት ሲሆን በታሪካችን ለመጀመርያ ባገኘነው ሃሳብን በነጻ የመግለጽ ዴሞክሪያሳዊ መብት ተጠቅመው በብዙ ጋዜጦችና መጻህፍት ሳይቀር ፀረ-ትግራይ ህዝብ ብዙ ተብለናል።ስለ ተፃፉት ብዙ ነገሮች ብዙ ማለት ቢቻልም ያስገረመኝ ነገር

አንድ ሲሳይ የተባለ የክልላችን ተወላጅ በፃፈው መፅሃፍ “የህዋሃት ሰዎች በትግል ወቅት የረገጡት መሬት ሁሉ የኛ መሬት ነው ይላሉ” በሚል ያሰፈረው ሃሳብ ሲሆን እነዚ ህዋሃቶት አፋር፣ወሎ፣ጎንደር፣ጎጃም፣ወለጋ፣ሰሜን

ሸዋ፣ምእራብ ሸዋና ሌሎች አከባቢዎች ከባድ ዋጋ የከፈሉበት ስለሆነ በሲሳይ ጥቆማ መሰረት የይገባናል ጥያቄ አቅርበው እንደሆነ ሳጣራ እንኳን የሰው መሬት በወቅቱ በእነዚህ ሁሉ ቦታዎች የዘሩት የትግራይ ልጆች አፅምና መስዋእትነትም ጭምር መርሳት እንደጀመሩ ነው የሰማሁት። መገመት የሚያዳግት ውለታ የዋለልን የትግራይ ህዝብ እንደ ጠላት እንዲታይና የአንድ ብሄር የበላይነት አለ እንድንል ባለቤት ያልነበረው የመንግስት ሚድያ የነገረንስ መቼ ትንሽ ሆነና። አሁንስ በዛ አትበሉኝና ምን ታዘብኩ መሰላቹ አንዳንድ በEBC የተቀጠሩ ግን ለጥፋት ኃይሎች የሚሰሩ የመንግስት ሚድያ ጋዜጠኞች በአንዳንድ መስራቤቶች ፕሮግራም ለመስራት በሚል ሽፋን ሄደው የትግራይ ተወላጅ ኃላፊ የሆነባቸው መርጠው አጀንዳ ፈጥረው በቴሌቭዥን እንዲቀርብ ያደርጉታል። ኃላፊው ሌላ ሆኖ ምክትሉ የትግራይ የወላጅ ከሆነ እሱን ያቀርባሉ፣በተሰራ ጥሩ ነገር የህዝብ አስተያየት ሲሰበስቡ መንግስትን ለማመስገን የቀረቡ አስተያየቶች በስም፣በቋንቋ አጠቃቀም፣በፊታቸው ወይም በአለባበሳቸው ለመረዳት እንደሚቻለው የትግራይ ተወላጅ ናቸው።እዛም እዚህም እነሱ ናቸው ለማስባል ነው። የበደል ደረሰብን አስተያየት የሚያቀርቡ ሲሆን ደግሞ ብዙዎቹ የሌላ ብሔር አባላት ያቀርባሉ። ምን አለፋቹ ብቻ እስኪ ቴሌቭዥን ክፈቱና በዜና፣በአስተያየትና በፕሮግራም በአንድ ቀን ስንት የትግራይ ተወላጅ እንደሚያቀርቡ ተመልከቱ።

በየክልሉና በፌደራል መንግስት ያሉ የህዝብ አገልጋይነት ስሜት የሌላቸው እና ሙሰኛ ባለስልጣናት ደግሞ ህዝቡ ልማት አምጣ ሲለው ልማት የትግራይ ህዝብ ስለወሰደው ማምጣት አልቻልኩም፣በክልላችን የመልካም አስተዳደር ችግር ነግሷል ሲል አዎ በህዋሃት መንግስት ምክንያት፣ወጣቱ መሬት ይሰጠን ሲል መሬት የለንም ምክንያቱም ህዋሃት መሬቱ ቆርሶ ወደ ትግራይ ክልል ስለወሰደውና የተረፈው ደግሞ ለሱዳን ስለሸጠው ፣ ድርቅ የመጣው በትግራይ የበላይነት ምክንያት ፣ በአገሪቱ ስራ አጥነት የተንሰራፋው በትግሬ የበላይነት፣ታክሲ ወረፋ የበዛው ተጠያቂው ትግሬ፣የዘይትና ስኳር እጥረትና የዋጋ ንረት እንዲሁም የመብራትና ውሃ መቆራረጥ የችግሩ ምንጭ ትግሬው ወዘተ እያሉ ባገኙት አጋጣሚ ሲሰብኩና ችግሩ እኔ ጋር አልነበረም ሲሉ ከርመዋል።

በሌላ በኩል በኢትዮጵያውያን የጥፋት ኃይሎች ስራ አስፈፃሚነት በምእራባውያን የሚተላለፈው ኢሳትና የኤርትራ ቴሌቭዥኖች ይህንን አጠናክሮ በመቀጠል በየቤቱ ወጥ ያረረውና በየምጣዱ እንጨት አልነድ ያለውም ጭምር ተጠያቂው የትግራይ ህዝብና ህዋሃት ነው አሉን።ዘንድሮ የሚገርም ነገር እየታጣ ነው እንጂ የሚገርመው ነገር በኢትዮጵያዊነት ስም ከውጭ የሚተላለፉ ሚድያዎች ህዝብን ለዚያውም እንደ ትግራይ ህዝብ ያለን ውለታ ብዙ ህዝብ በጠላትነት ፈርጀርጀው በአማራ ክልል፣ እንደ ሻሸመኔና በአንዳንድ የቦረና አከባቢዎች እነሱ ባቀጣጠሉት እሳት ሲቃጠል ለይምሰል እንኳን ምንም ለማለት አለመፈለጋቸው ነው። ለነገሩ የመደባዊ ቦታ ጉዳይ ሆነና በትግራይ ህዝብ ስም ለትግራይ ህዝብ አርነት ተቋቆምኩ የሚለን አረና ትግራይ የተባለ ድርጅትስ ህዝቡ ሲታረድ መቼ ትንፍሽ አለና። የመደባዊ ቦታ ሽግሽግ ያደረጉ እነ ጀነራል ፃድቃንም ቦታቸው ለማስጠበቅ ብዙ አልሰነፉም።

ከዚህ ጋር በተያያዘ አንድ ገጠመኝ ሳላካፍላቹ ማለፍ የጤና ምንጭ የሆነ ሳቅ ለብቻየ ማድረጌ ከግለኝነት ያስቆጥርብኛልና እንካቹ፤ በነዚህ ቅስቀሳዎች የሰከረ ግዛቸው የተባለ ባልደረባችን በአንድ ካፌ ተቀምጠን እያወራን የትግሬ የበላይነትማ አለ አለንና በEBS ቴሌቭዥን ለመሸጋገርያ የብሔር ብሔረሰብ አጫጭር ዘፈኖች ይቀርባሉና ከትግርኛ የዳዊት ነጋ ወዛመይ ዘፈን አለ። ከሌሎች ዘፈኖች ረጃጅም ሴኮንዶች ይቆያል አለን። እናስ ስንለው እናማ የትግሬ የበላይነት አንዱ መገለጫ ነዋ ብሎን እርፍ።

አብረው አቅደው ለአንድ ግብ በተለያየ አቅጣጫ የስራ ክፍፍል በማድረግ የሚንቀሳቀሱ የኢትዮጵያ የለውጥ ግስጋሴ በስጋት የሚያዩ የውጭ የብተና ኃይሎች በወቅታዊ አጠራራቸው የቀለም አብዮተኞች በበኩላቸው በተለያየ አለማቀፍ ድርጅቶች ስም ባደራጇቸው ተቋማትና በሚድያዎቻቸው አመካኝነት “እናንተ ኢትዮጵያውያን ከናንተ ጋር ያለ ችግር የትግራይ የበላይነት ብቻ መሰላቹ?” ብለው ይጠይቁና “በአገራቹ ዴሞክራሲም ቢሆን እኮ ከዜሮ በታች ነው፣ህግ የለም፣ሃሳብ በነፃነት መግለፅ የለም እናም ለምን ዝም እንዳላቹ ብቻ ነው ያልገባን” ይላሉ።

“ውሸት ሲደጋገም እውነት ይመስላል” እንዲሉ በየቀኑና በሁሉም አቅጣጫ አንድ ነገር ብቻ የተነገረው የተወሰነ የህብረተሰብ ክፍል ጉዳዩ እውነት ነው ብሎ በማመን በህዝቡና በህዋሃት ላይ በጎ ያልሆነ አመለካከት ተፈጥሮ አመፅ

ለማነሳሳትና በአንዳንድ የብሔሩ ተወላጆች ላይ ምንም በማያውቁት ጉዳይ የህይወት መጥፋት፣የአካል መጉደልና በእድሜ ዘመናቸው ሙሉ ያፈሩት ሃብታቸው የመውደም ችግር የደረሰባቸው ሲሆን መንግስት መፍትሔ ያመጣል በሚል በትግስት ከመጠበቅ የዘለለ ምንም አይነት የበቀል እርምጃ አልወሰዱም።የበቀል እርምጃ አለመውሰድ ብቻ ሳይሆን በወቅቱ በተለያየ ምክንያት በትግራይ ክልል ለነበሩ የአማራ ብሔር ተወላጆች የፍራቻ ስሜት

እንዳያድርባቸው በማሰብ ልክ በ1973 ዓም ኢህዴን ለመመስረት የቆረጡ ታጋዮች የትግራይ ህዝብ ያስጠልለናል የሚል እምነት ይዘው በሄዱ ግዜ በወቅቱ በነበረው በድህነት አቅሙ ከራሱና ከልጆቹ ቀምቶ እንደተንከባከባቸው ሁሉ ለነዚህም ከወትሮው የተለየ እንክብካቤ ሲያደርግላቸው እንደነበር ለአሸንዳ በአል በክልሉ የነበሩ የአገው ላስታና አንዳንድ የሰሜን ወሎ ተወላጆች በአግራሞት ሲናገሩ ሰምተናል። ከዚህ የዘለለ ደግሞ ወቅቱ ክረምትና የክረምት መውጫ ስለነበር በአመዛኙ ከጎንደር ሌላው ከጎጃምና ወሎ የሄደ ለአረምና ሰሊጥ አጨዳ ከ150 ሺ የአማራ ተወላጅ የቀን ሰራተኛ በትግራይ ክልል ምእራባዊ ዞን ቃብታ ሁመራ ይገኝ እንደነበር አንድ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ስታስቲክስ ያሳያል። ታድያ በዚህ ወቅት ሰውም ቢሆን እንኳን ለህይወቱ የሚያሰጋ ነገር መፈጠር ይቅርና የሰራበትን ገንዘብ ለማስቀረትም የተመኘ ሰው እንዳልነበረ በባንክ ስራ በሁመራ ከተማ የነበረ የጎንደር ማክሰኝት ከተማ ተወላጅ በመደነቅ አጫውቶናል።የሚደንቀው ግን አለን ይህ ሰው የሚደንቀው ግን በዚህ ወቅት አፄ ዮሀንስ ለዚች ክብርት አገር ብለው አንገታቸው ለሳፍ ሰጥተው ከወደቁባት ከመተማ የሞተ ከሞተ በኃላ “ትግሬዎች ይውጡልን” ተብለው ያፈሩትን ቤትና ንብረታቸው ተዘርፎና ተቃጥሎ ባዶ እጃቸው በሺ የሚቆጠሩ ሰዎች ተፈናቅለው በዚሁ በሁመራ በተሰባሰቡበት መሆኑ ነው ይላል።

እርግጥ ነው ይህ ህዝብ እንኳን ድንጋይና ጩቤ ይዞ ሊደፍረው ያለ የአማራን ህዝብ የማይወክል የወሮ በላ መንጋና የተሸናፊው ስርአት ትራፊ ይቅርና ሚግ፣ታንክና ቢኤም ይዞ ልጫንህ ያለው የደርግ ስርአትን አሽቀንጥሮ የጣለ ህዝብ ነውና ላሳየው ትእግስትና የኢትዮጵያዊነት ስነ ምግባር ልናመሰግነው ይገባልና አመስግኑልኝ።

ባለፈው ፅሁፌ ለመግለፅ እንደሞከርኩት የትግራይ ህዝብና ህዋሃት አሁን ባለን ሰላም፣አሁን ባለን ሃብት፣አሁን ባለን የትምህርት እድልና ደረጃ፣አሁን ባለን ፈጣንና ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የሚነካ የኢኮነሚያዊ እድገት፣አገራችን አሁን ባላት የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ፣የዴሞክራሲና አዲስ ከፍታ የሚመነዘር ትርፍ ዋጋ ከፍሎ ሲያበቃ ማመስግን ሲገባን ምስጋና ሳይጠብቅና የካሳ ይከፈለኝ ፣የአድርጉልኝ ጥያቄ ሳያቀርብ በጠባብና የተራቆተች መሬቱ ልማት ለማረጋገጥ ሲፍጨረጨር ባላሰበው መንገድ ወራሪ፣ ከሃዲ፣ አገር አጥፊ ተብሎ መፈረጁ እንኳን ለነሱ ለማንኛውም ሰብአዊ ህሊና ያለው ሰውም ይመራል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ የኪነ ጥበብ ድርሰት የሚመስል ግን እውነተኛ ታሪክ ልንገራቹ።የታሪኩ ግጥምጥሞሽና አሳዛኝነት ራሱ የቻለ መፅሐፍ ይወጣው የነበረ ቢሆንም ለዚህ ፅሑፍ በሚሆን ብቻ አድርጌ ላቅርበው። በወቅቱ በአከባቢው ነበርኩ ብሎ ለኔና ለሁለት ጓደኞቼ ያወራን በደቡብ ጎንደር ዞን የአስተዳደር እርከን ውስጥ የሚሰራ ሰው ነው የነገረን። ታሪኩ ወልዳይ ጣረው የተባለ የህዋሃት ታጋይ የነበረ ሰው ታሪክ ነው። ጣረው ትርጉሙ ባናውቀውም የአባቱ ስም እንዳልሆነ ነግሮናል። ሰውየው እንደሚለው የ1973 ዓ/ም ታጋይ ነው። ከደርግ ጋር በነበረ ውግያ በብዙዎቹ

ተሳትፏል።ትግራይ ነፃ ካወጣ በኃላ “መላው ህዝብ ነፃ ካልወጣ ሙሉ ነፃነት አይሆንም “ በሚል ከነበረበት ወታደራዊ ክፍል ጋር በመሆን እየተዋጋ ጉና ተራራ ደረሰ። የጉና ውግያ በኢህአዴግ የውግያ ታሪክ ፈታኙ እንደነበር ተደጋጋሚ

ሲያወሩ እሰማሎህ። ወልዳይ በወቅቱ ደረጃው ባይገባኝም ቦጦሎኒ አመራር ነበር አሉት። እንደ ታሪካዊ አጋጣሚ ከዛ በፊት በነበሩ በርካታ ውግያዎች ቆስሎ አያውቅም ። በፈታኙ የጉና ውግያ የአማራ ህዝብ እንደ ትግራይ ህዝብ ከአረመኔው የደርግ ስርአት ነፃ ይውጣ ያለው ወልዳይ ጣረው ከበረዶ ግግርና ከመድፍ እየተዋጋና እያዋጋ ከዋለ በኃላ ወደ ማታ አከባቢ በከባድ መሳርያ እግሩ ክፉኛ ተመታ።ወድያው ወደ ህክምና ወሰዱትና እግሩ ተቆረጠ።

የተቆረጠችው እግሩ እዛው ደቡብ ጎንደር ከጉና ተራራ ብዙ በማይርቅ አከባቢ ተቀበረች። ወልዳይ ቦርድ ተብሎ ሰው ሰራሽ እግር አስገጥሞ ለሰዎች ተባበሩኝ እያለ ይነግዳል።ታድያ በቅርቡ በክልላችን በነበረው ግርግር በትግራይ ተወላጆች ጥቃት ሲደርስ ባህርዳር ስለነበር ወደ መቀሌ እየተጓዘ ለዛ ህዝብ ነፃነት እግሩ ተቆርጦ በተቀበረበት ንፋስ መውጫ አከባቢ ሲደርስ በጥቂት ወጣቶችና የፖለቲካ አጀንዳ አለን በሚሉ ሰዎች መንገድ ተዘግቶ ከየመኪናው የትግራይ ተወላጅ አምጡ እያሉ መኪኖች እየተፈተሹ መሆናቸው ሲያይ ህይወቱም እንደ እግሩ በዚሁ ቦታ ልትቀበር እንደምትችል በማሰብ ከባድ ድንጋጤ ውስጥ ገብቶ ያዩት የአከባቢው ነዋሪዎችና አንድ የክልሉ ፖሊስ ወደ መንደር ወስደው በመደበቅ ከሶስት ቀን በኃላ ወደ መቀሌ ሸኙት አለን። እዚህ ላይ ያስገረመኝ በአንድ በኩል የሰውየውና የቦታው ግጥምጥሞሽ በሌላ በኩል ግን የደቡብ ጎንደር ህዝብ በጉና ተራራ ውግያ ወቅት ቆስሎ ከጓዶቹ ተነጥሎ የቀረና በጠላት እጅ ሊወድቅ የነበረ አንድ የህዋሃት ታጋይ ህዝቡ ደብቆ፣አክሞና ተንከባክቦ ከወራት በኃላ ከጓዶቹ እንዲቀላቀል ማድረጉ ብዙዎቻችን ሰምተናልና በዚህ ህዝብ ተመሳሳይ ታሪክ መደገሙ ኩራት ተሰማኝ። ድሮም “ህዝብ እንደ ህዝብ መሳሳት አይችልም” የሚል አባባል ጋህድ አደረገልኝ።

ወደ ተነሳሁበት ልመለስና በአንድ አገር የአንድ ብሔር የበላይነት አለ ሲባል ከትርጉሙም ሆነ ከነባራዊ ሁኔታ ለኛ አገር የሚገልፅ ሊሆን አይችልም ።በርግጥም በዚህ አገር የአንድ ብሔር የቋንቋ፣የኢኮኖሚ፣የባህል፣የፖለቲካና የማህበራዊ መስተጋብር የበላይነት የያዘ የለም።አንድ ብሔር በሌላ ክልል ገብቶ እንዳታለማ፣እኔ ነኝ የማስተዳድርህ፣በቋንቋህ እንዳትናገር፣እንዳትዳኝ፣ዴሞክራሲ ለኔ እንጂ ላንተ አይመለከትህም፣እኔ አውራ ብሔር አንተ ሁለተኛ የመሳሰሉ ተፅእኖዎችና አድልዎ የሉም።

በዚህ ላይ ተደጋግሞ የሚነሳውና በህዝብ አስተሳሰብም ተቀባይነት አግኝቷል ብየ የማምነው በመከላከያ የትግራይ ብሔር ተወላጆች ቁጥርና ኃላፊነት የበላይነት አለ የሚል ነው። እኔም ከምሰማው አንፃር በቁጥርም ሆነ በኃላፊነት ሙሉ በሙሉ የተመጣጠነ ነው አልልም። የዚህ ምክንያት ግን ብዙ ግዜ ሲነግር እንደሰማነው በትጥቅ ትግሉ ወቅት በቁጥርም ሆነ በኃላፊነት ብሎም በአስተዋፅኦ የነበረው በጣም ሰፊ ልዩነት እንደ ታሪካዊ መነሻ መወሰድ ግድ የሚለን ሲሆን ከዛ በኃላ ይህንን ያለመመጣጠን ተሰውተው ያገኙት ነው በሚል ባለበት እንዳይቀጥል ለአገራዊ መግባባትና ለፍትሃዊነት ሲባል ከጅምሩ የተለያዩ የማመጣጠን እርምጃዎች ለመውሰድ ሞክረዋል። ባለፈው ፅሁፌ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት ከተራ ተዋጊ እስከ ብርጌድ የሚባል አዋጊዎች በሺዎች የሚቆጠሩ የህዋሃት የጦር አባላትና መኮንኖች በህይወታቸው አልመውት ወደ ማያውቁት የግብርናና የከብት ርቢ ህይወት ተቀላቅለዋል።በወቅቱ እንኳን ህይወቱና አካሉ ከፍሎ አሁን ላለንበት ደረጃ ያደረሰን ይቅርና የተወሰኑ አመታት አገልግሎት ለሰጠህ ታማኝ ሰራተኛ በስጦታ ከሚሰጠው ሱጠታ ባነሰ እንዲቋቋሙ ተደርገዋል።ይህንን አላምን ያለ ካለ በትግራይ ክልል ፀገዴ ወረዳ ዳንሻ ቀበሌ በመሄድ በአካል ማረጋገጥ ይቻላል።

ሌላው ሁሉም የህዋሃት የጦር መኮንኖች የተመጣጠነ አገራዊ ሰራዊት እንዲኖረን ብለው ከነበራቸው ኃላፊነት ሁለት ደረጃ ዝቅ እንዲሉ ተደርገዋል። ሌላው እውነታ ከተወሰኑ አመታት ወዲህ በጥሮታና በተለያዩ ምክንያቶች ከሰራዊቱ እንዲገለ ተደርጓል እየተደረገም ይገኛል።እርግጥ ነው ይህ ተግባር ለህዋሃት አባላት የነበሩ ብቻ እየተደረገ እንዳልሆነ ግልፅ ነው። በጥፋትና በተለያዩ የስነ ምግባር ችግሮች የተባረሩ ሳይጨምር ከሰራዊቱ የተቀነሱ ቁጥራቸው አይገናኝም ። ከብአዴንና ከኦህዴድ የተቀነሱ ጀነራሎች ቀጥራቸው ሁላችን የምንሰማው ስለሆነ እናውቀዋለን ከህዋሃት

ታጋዮች የነበሩ ከ15 ያላነሱ ጀነራሎች መቀነሳቸው ስማቸው እየተጠራ ሲነገረኝ እውነታው ከኔም ከእናንተም ግምት ውጭ እንደነበረ እገምታሎህ። በቁጥር በትክክል ሊነግረኝ የሚችል ባላገኝም የተቀነሱ ኮለኔሎች ልዩነቱ በጣም ሰፊ እንደሆነ ተረድቻሎህ። ይህ በአንድ በኩል ሆኖ በሌላ በኩል ደግሞ ከደቡብና ከኦሮምያ ክልል ከተለያዩ የመንግስት መስራቤቶች የተውጣጡ ስቪል ሰራተኞች ወደ መከላከያ እንዲቀላቀሉና በቀጥታ የመኮነንነት ኮከብ ትክሻቸው ላይ ሰቅለው ታሪክ ለሰሩ ታጋዮች አለቆቻቸው ሆነው ሲመደቡ አገራዊ መልክ ያለው ሰራዊት መገንባት ግድ መሆኑ ከማመናቸውና እየተገበሩት ከመሆን ውጭ ምን ትርጉም ይሰጠዋል። ይህንን ስል ግን በአመራር አከባቢ ያለው የመመጣጠን ሂደት ከዚህ በላይ መፍጠንና መቀጠል የለበትም ማለት አይደለም።

በመጨረሻ ከሰዎች ጋር በምናደርገው ውይይትና ክርክር የትግራይ የበላይነት ማሳያ እየሆኑ የሚቀርቡ አብዛኛዎቹ የአዲስ አበባ ህንፃዎች የትግራይ ተወላጆች ናቸው የሚል ሲሆን ባለፈው እንገለፅኩላቹና በኃላም እድሉ አግኝቸ በዳታ ለማረጋገጥ እንደቻልኩት የአዲስ አበባ ህንፃዎች ብዙዎቹ የትግሬውም ሆነ የአማራው አይደሉም። አይደሉም እንጂ እስኪ እነዚህ ህንፃዎች የትግሬ ናቸው ብለን እንነሳና እንደ ፓርላማ ወንበሩ 38 ህንፃ ብቻ ነው የሚገባው ካላልን በስተቀር በላቡ ያፈራው ሃብት ሌላው በሌላ ኢንቨስትመንት እንደሚያውለው ሁሉ በህንፃ ላውል ብሎ ቢሰራስ?ወይም በህግ የተደነገገ ለዚህ ብሔር አድልዎ ያደረገ ህግ አለ ?ሌላው ህንፃ ልስራ ብሎ አይ እሱማ ለእገሌ

ብሔር ነው ተብሎ የተከለከለ አለ? ለነሱ ብቻ የሊዝ፣የግንባታ እቃና ሌሎች ቅናሽ ተደረገ?ወይስ ለነሱ ብቻ የተለየ የቀረጥ ነፃ መብት ተሰጣቸው? መልሱ ግልፅ ነው። በነገራችን ላይ በአዲስ አበባ አስተዳደርና የብሔር ተዋፅኦም የተዛባ አስተሳሰብ አለ ባይ ነኝ። የአዲስ አበባ መስተዳድር የብሔር ተዋፅኦ በየክልሉ ባለው የብሔሩ ህዝብ ቁጥር ልክ የማሰብ ሁኔታ አለ። አ/አበባ መስተዳድር በከተማው ለሚኖር ህዝብ አስተዳዳሪ እንጂ የፌደራል ፓርላማ ወይም አስፈፃሚ አካል አይደለም።ስለ ሆነም ተዋፅኦው መመዘን ያለበት በከተማው በሚኖር ህዝብ ቁጥር መሆን ይገባዋል የሚል እምነት አለኝ።

ሌላው በክርክር የሚነሳው በየቦታው በርካታ ክራይ ሰብሳቢ ባለሃብትና አጭበርባሪ ደላላ የትግራይ ተወላጅ እየበዛ ሃብት እየሰበሰበ ነው የሚል ነው። እዚህ ላይ በእውነታው እኔም እስማማለሁ።የማልስማማው ግን የትግሬ የበላይነት መገለጫ ሆኖ መቅረቡ ነው። ለምን ቢባል በዚህ አገር ሌባ ባለሃብትና አጭበርብሮ ሃብት ያከማቸ ደላላ ትግሬው ብቻ ስላልሆነና ይህንን ችግር አገራዊ ችግር እንደመሆኑ መታገል ያለብን ሁላችን እንጂ የትግራይ ህዝብ ብቻ እንዲሆን የሚተው ስላልሆነ ነው።

የ”ጥልቅ ተሃድሶ” አፈፃፀም፣ውጤቱና ቀጣይ አዝማምያው፤

ተሃድሶ ማለት ምን ማለት ነው? ብዙ ፍልስፍና ውስጥ ሳንገባ ዳግም መነሳት፣ መንቃት፣ መታደስ፣መጠገን የመሳሰሉ ፍቺዎች ሊሰጠን ይችላል። ከሁሉም ፍቺ የምንጠብቀው ውጤት ደግሞ የጠራ፣የደመቀ፣የፋፋ፣የጎመራ ነገር እንደሆነ ደግሞ የሚያከራክር አይሆንም።

ስለ ተሃድሶ ሲነሳ ብዙ ግዜ ስለ ፖለቲካ ተሃድሶ ይወራ እንጂ ከፖለቲካው ተነጥለው ለየብቻቸው የኢኮኖሚ ተሃድሶ፣የጥበብ ተሃድሶ፣የባህል ተሃድሶ እየተባሉ ብዙ የተሃድሶ አይነቶች ሰምተናል አይተናል።ከዘመናዊ አውሮፓ መፈጠር ጋር ተያይዞም በርካታ የተሃድሶ መስኮች ታይተዋል።በወቅቱ ጎልቶ የሚጠቀሰው በጣልያን የተካሄደ ተሃድሶ

ነው። ከጣልያን ኢፓየር መውደቅ በኃላ በአውሮፓ ተከስቶ የነበረው የመበተን አደጋ የታደገው ተሃድሶ እንደሆነ ተፅፎ አንብበናል። ሌሎች ተመሳሳይ ታሪኮች በማውራት ብዙ ላደነቁራቹ አልፈልግም። የመጀመርያው ምክንያቴ እውቀቴ በጣም ትንሽ በመሆኑ ሲሆን ሌላው ለተነሳሁት ሃሳብ እንዳያንዛዛብኝ ነው።

ስለ ኢህአዴግ የመጀመርያው ተሃድሶ ባለፈው ፅሁፌ ብዙ ብያለሁና አሁን ማለት የምፈልገው የለኝም። የዘንድሮ “ጥልቅ ተሃድሶ” ትርጉም በተመለከተ በኛም ሆነ በመንግስት ባለስልጣናት በሁለታችን ዘንድ የተዛቡ አስተሳሰቦች በመያዝ ተሃድሶውን እየገመገምን እንዳለን ይሰማኛል። በኛ በህዝቦች በኩል የ”ጥልቅ ተሃድሶ” ውጤት የሚለካው

ቱባ ቱባ ባለስልጣናትን ወህኒ ሲወርዱ ማየት እንደሆነ ወይም አሉብን ብለን ያቀረብናቸው ችግሮች ከስብሰባው መልስ በኃላ እንደ ደራሽ ወንዝ በአንድ ጀምበር ጠራርጎ የሚፈታ እንደሆነ የማሰብ ነገር ስላለ በደፈናው ተሃድሶ የታለ? ተሃድሶማ በሬድዮና ቴሌቭዥን በወሬ ብቻ ቀረ እንላለን። በመሪዎቻችን በኩል ደግሞ “ተሃድሶ ማለት ሰው አይነካም ከነካም የበታች እንጂ አመራርን አይነካም። መስመር ብቻ የማጥራት ግብ ብቻ ነው ያለው” የሚል ሃሳብ ሲያራምዱ እናያለን። ህዝቡ በዚህ ዙርያ ደጋግሞ ጥያቄ ሲያቀርብ ደግሞ “ማስረጃ የለም እንጂ ማስረጃማ ቢገኝ ሰውም አይምርም ነበር” ይሉናል።አንዳንድ ከፍተኛ አመራሮች ሳይቀሩ መሰረታዊ ችግሩና ትግሉ ከአመለካከት መሆኑ ቀርቶ ከላይ ሚኒስትር ከታች አንዳንድ አስፈፃሚ አካላት በማውረድና በመስቀል ተሃድሶ ለዚያውም ጥልቅ ተሃድሶ ያካሄዱ የሚመስላቸው አሉ።የተሃድሶው ውጤት በዚህ አስተሳሰብ ሊገመግሙት ይፈልጋሉ።

ለማንኛውም በኔ እይታ “ጥልቅ ተሃድሶ” ሲባል በመስመር ጥራት ዙርያ፣በነበሩን ዘርፈ ብዙ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂ ጥራትና ጉድለት ደረጃ፣ከከፍተኛ አመራሩ ጀምሮ በአስፈፃሚ አካላት ያለው የአመለካከት፣ የእውቀትና ክህሎት ዙርያ

እንዲሁም የውስጥና የውጭ የኃይሎች የወቅቱ አሰላለፍና ከዚህ አንፃር ማድረግ ስለሚገባ ለውጥ በጥልቀት መገምገም። ከዚህ ግምገማ አኳያ ከአዲሱ አስተሳሰብና አሰራር ዘይትና ውሃ ሆኖ መቀራረብ ያልቻለ የጠራውን እንዳያቆሽሽ ቦታው የሚይዝበት ሁኔታ መፍጠር እንዲሁም የህዝብና የአገር ጥቅም ወደ ራሱ ጥቅም የቀየረ ወይም ለሌላ አሳልፎ የሰጠና እንደ ማግኔት ተመሳሳይ ፖል {ጫፎች} ማቀራረብ የማይቻለውን በህግ መዳኘትንም

ይጨምራል።ሌላው የ”ጥልቅ ተሃድሶ” ጥልቀት የሚለካው ይህ አዲስ አስተሳሰብና አሰራር ከከፍተኛ አመራሩ ጀምሮ እስከ ህዝብ ድረስ በማውረድ አዲሱ አስተሳሰብ እስከ ታች ዘልቆ እንዲገባ መስራትና በዚህ ጉዞ የሚታዩ እንቅፋቶችንና ፍልሚያዎች አሸንፎ መውጣት ነው።

የአስተሳሰብ ትግሉ አሁን እያየነው እንዳለን ጉድለት የተባለውን ሁሉ በአንድ ስብሰባ መዘክዘክና እንደ አዋጅ በመገናኛ ብዙኃን በመንገር ሳይሆን ያለ ማቋረጥ በቀጣይነት የሚካሄድ የአስተሳሰብ ትግል ስለሆነ ግዜ ይወስዳል። ለዚህ ነው ተሃድሶው ጥልቅ የሚሆነው።

በዚህ መነፅር የኢህአዴግ “ጥልቅ ተሃድሶ” እንዴት እየሄደ ነው ያልን እንደሆነ እንደ ነብር ቆዳ ዥንጉጉር ነው የሚል አስተያየት አለኝ። ምንም እንኳን የተሃድሶ ፕሮግራሙ ከረጅም ግዜ ጀምሮ የታሰበበትና የተሟላ ጥናት ሲደረግ ቆይቶ

የመጣ ሳይሆን ህዝቡ ዱላ ሲያነሳ በሩጫ ሩጫ የተጀመረ ነው የሚል እምነት ቢኖረኝም የተነሱ ሃሳቦችና የተለዩ ችግሮች ትክክል ነበሩ የሚል እምነት አለኝ።የተደረጉ ውይይቶች ችግሮቹ ለመፍታት የሚያስችሉ ነበሩ ባልልም ህዝቡም ሆነ አብዛኛው አመራሩ ቆም ብለው እንዲያስቡ ያስቻሉ ነበሩ ብሎ መውሰድ ይቻላል።በአንዳንድ

አከባቢዎችም በንፅፅር ሻል ያለ ተግባር ተከናውኗል ብዮ አምናለሁ።በአፈፃፀሙ እንደ አንድ ፋሽን መወሰድና ከበስተጀርባው ያሉ የተለያዩ አመለካከቶች ትተን እንደ የተሃድሶው አካል ተደርጎ አዳዲስ ሰዎች ወደ ኃላፊነት ለማምጣት የተደረጉ ጥረቶች እንደ በጎ እርምጃዎች እንውሰዳቸው የሚል ሀሳብ አለኝ።

በኔ እምነት ይህ የተሃድሶ መድረክ ከተጓዘው መንገድ ይልቅ የቀረው ርቀት በጣም የበዛ ከመሆኑ በተጨማሪ በተጓዘው ርቀትም የተንጠባጠቡ ነገሮች በርካታ ናቸው።በርግጥ ተሃድሶው በጣም የዘገየ መሆኑ አያጠያይቅም።ከመጀመርያው ተሃድሶ በኃላ ተሎ መፈተሽ የነበረባቸው አልተፈተሹም፣ከአምስት አመት በፊት የነበረ ሁኔታ ተሃድሶ ይጠይቅ ነበር፣ካለፈው የኢህአዴግ ጉባኤ በፊት ተሃድሶ የሚጠይቁ ሁኔታዎች አይናቸው አፍጥጠው ይጠብቁ ነበርና ይህንን ያደረገ አልነበረም።

መዘግየቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ከላይ ለመግለፅ እንደሞከርኩት ሂደቱ በበቂ ጥናትና ዝግጅት የተጀመረ አይደለም የሚል ግምት እንዲኖረኝ የሚያደርጉ በርካታ ነገሮች አይቻሎህ ።ይህ ሲሆን ደግሞ “የነተሎተሎ ቤት ግድግዳው ሰምበለጥ”

እንደሚባለው መሆኑ አይቀርም።በመሆኑም ከሰነድ ዝግጅቱ በኃላ ከፍተኛ አመራሩ ባደረገው ውይይት አቋሙ ከመግለፅ አንፃር በጥሩ ጎኑ የሚታይ ቢሆንም የተሳሳቱ አመለካከቶች በሚገባ ተወግዘው አልወጡም።የኃላ ኃላ እንደተረዳሁት እንደህ የበሰበሰ አመለካከት ተሸካሚ የነበረ አመራር ከማፈርና የጥፋት ደረጃው ከመረዳት ይልቅ እንዲህ አይነት ሃሳብ በድፍረት የሚያቀርብና የሚከራከር ጀግና ተብሎ የተወደሰበት አከባቢ አውቃሎህ።

በኢህአዴግ ከፍተኛ አመራር የተሃድሶ ስብሰባ ወቅት ብዙ ሚስጥር አላገኘንም ነበር። ይህ ከኢህአዴግ የቆየ ድርጅታዊ ባህልና አሰራር አንፃር ስናየው እንደ አንድ የተሃድሶው ውጤታማነት መገለጫ ታይቶ የነበረ ሲሆን ብሔራዊ ድርጅቶች ወደየ ቦታቸው ሲመለሱ ለመስማት እንኳን የሚከብድ አስተሳሰብ በኩራትና በጀግንነት ሲነገር ተደመጠና ማን ምን አይነት አቋም እንዳራመደ ለመወቅ ሁለት ቀን ብቻ ነው የፈጀብን።እዚህ ላይ የድርጅቱ ዴሞክሪሳዊ ማእከላዊነት የሚባል ትልቅ አቅም መሸርሸሩ ብቻ ሳይሆን አመራሩ በችግሩና ችግሩን ተከትሎ እየመጣ ባለው አደጋ ዙርያ መግባባት ሳይደረስ መለያየቱ ነው።ከፍተኛ አመራሩ በጋራ በነበረበት ወቅት ለችግሩ የሚመጥን መነሻ ቅጣት ማስቀመጥ ሳይችል ወደየክልሉ መበታተኑና በየብሔራዊ ድርጅቱ እንዲታይ መወሰኑ የተሃድሶ ስሜቱ በራሱ በአመራሩ መቦርቦር የመጀመርያው ምዕራፍ ተደርጎ ይታያል።የተለያዩ የድርጅት አሰራር አይፈቅድም የሚል በምክንያትነት ሊጠቀስ ይችል ይሆናል። ይሁን እንጂ ያለንበት ሁኔታ የተለየ በመሆኑና አንዳንድ አሰራሮች ለለውጥ እስከሆነ ድረስ እንደየ ትርጉማችን መውሰድ እንችላለን። ከከፍተኛ አመራሩ በጋራ የመገምገም አቅጣጫ ሲከተሉ ሰምተናል። ትክክልም ነበር።

በየብሔራዊ ድርጅት የተደረገ ግምገማ ከድርጅት ድርጅት የሚለያይ ቢሆንም በመሰረታዊነት ብዙም ልዩነት አለ ማለት አይቻልም። መጀመርያ አንዳንድ እርምጃዎች መውሰድ የጀመረው ኦህዴድ ስለነበርና በኢህአዴጋቸው አሰራር መሰረት በአካሄድ የእያንዳንዱ አመራር የግል ግምገማ ከመደረጉ በፊት በአቋራጭ ወደ ሹምሽር በመግባታቸውና በሹም ሽሩ ወደ ኃላፊነት ከመጡ አመራሮች መካከል ብያንስ አንዱ በሙስና ይጠረጠሩ ከነበሩ መካከል በመሆናቸው ስጠብቀው ከነበረ ለውጥ አኳያ በተስፋ አስቆራጭነት ስሜት ተቃውሞየን በፌስቡክ አድራሻየ ገልጨ ነበር። በኃላ የከፋ ነገር እየመጣ ሲሄድ “ከቀዳዳ ይሻላል ጨምዳዳ” እንዲሉ ኦህዴድ ከነ ብዙ ጉድለቱ የተሻለ

ጥረት ለማድረግ እየሞከረ እንደ ሚሆን ማሰብ ጀምሬለሁ።ሚድያው እየሸወደን ካልሆነ በስተቀር ከጭንቅላት ዝቅ ብለው በተወሰዱ እርምጃዎችም ቢሆን ኦህዴድ የተሻለ ድፍረት ነበረው የሚል እምነት ይዣለሁ።

ይሁን እንጂ የኦህዴድ ስኬት የሚለካው በኦህዴድ ውስጥ በክራይ ሰብሳቢነትና የዚህ ብልሹነት መሸሸግያ ከሆነው በብሄርተኝነት ስም በከፋ የጠባብነት አረንቋ ውስጥ የተዘፈቁ በርካታ ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም እነሱ የፈጠሩት የጥፋት መረብ በመበጣጠስ በምትኩ በድርጅቱ አብዮታዊ አስተሳሰብና ተግባር የበላይነት እንዲኖረው ማስቻል መሆኑ ግልፅ ነው።ከዚህ አንፃር ከተወሰኑ ንክኪዎች በስተቀር መረቡ አላሳልፍም በማለቱ የለውጥ ጉዞው ለማቀጣጠል የሚያስችል እርምጃ ሲወሰድ አላየንም።አንዳንድ በአመለካከት ችግር ውስጥ ያሉ በፌዴራል መንግስት የነበሩ ሰዎች መልሶ በክልሉ አዲሱ ካቢኔ መካተታቸው የተሃድሶ ጉዞው ጥያቄ ውስጥ ካስገቡ ተግባራት ውስጥ ተጠቃሽ ነው።ከዚህ ሌላና ወሰኙ ነገር አዲሶቹ የድርጅቱ መሪዎች ሊቀመንበሩና ምክትሉ በኦህዴድ ውስጥ በጣም የገነገነውና ሰው የማስገደል አቅም አለው ተብሎ በሚታማው የኔትዎርክ ቡድን አባላት ናቸው የሚል ጉምጉምታ ያለ በመሆኑ የሰው ማንነት የሚለካው በእንደዚህ ያለ ፈታኝ መድረክ መሆኑ ተረድተው ይህንን በተጨባጭ ተግባራቸው በርግደው በመውጣት የለውጥ መሪዎች መሆናቸው ማስመስከር ከክልሉም ሆነ ከአገሪቱ ህዝቦች በአጠቃላይ እየተጠበቀ ያለ ጉዳይ ነው።

ከዚህ ውጭ በአንድ በኩል ራሱን ከሌላ በማወዳደር በሌላ በኩል ወሰድኩት በሚለው እርምጃ የመኩራራት አዝማምያዎች እንታዘባለን።ሌላው የተጋገረ የጠባብነት አስተሳሰብ በክልሉ ከሌላው ይቅርና ከአመራሩም ጭምር ያልተገፋ ችግር መሆኑ እንዲሁም በሌብነት ወይም በተለመደው ስሙ በክራይ ሰብሳቢነት ረገድ በክልሉ ወደ እያንዳንዱ ቤት እየገባ ያንኳኳበት ሁኔታ ስለነበር አሁን ከጭንቅላትና ከልብ ዝቅ ብሎ መውሰድ በተጀመረው እርምጃ የእንሻላለን አመለካከት በመጣል በአግባቡ እየመራ ዳር ማድረስ ይጠበቅበታል።

የብአዴን የተሃድሶ ሂደትና ውጤቱ እኔ እንደጠበቅኩት ነበር ማለት ይቻላል።አብዛኛው አመራር ለለውጥ ዝግጁ ሆኖ ሳለ የተሃድሶ በር ለመክፈት ቁልፉ ከያዙትና ከመንገድ ካፈነገጡ ጥቂት ግለሰቦች መቀማት ባለመቻሉ ምክንያት የብአዴን ተሃድሶ ከዜሮ ብዜት አይነት ውጤት ብዙም ፈቅ ያላለ ሆኖ ይገኛል ። ባለፈው ፅሁፌ ከሌሎች በተሻለ በቅርበት እያየሁት ስለነበረው ብአዴን ጥቂት ነገር በማለቴ ብዙ ነገር ሲባል ሰምቻለሁኝ። ከተሃድሶ በፊት የፃፍኩት በተሃድሶ ወቅት ሙሉ በሙሉ ትክክል መሆኑ ከመረጋጡ በተጨማሪ ለማመን የሚከብዱ ሌሎች ችግሮች መቅረባቸው ሰምቻለሁ።እንድያም ሆኖ እያንዳንዱ አመራር በነበረው የጥፋት ደረጃ ራሱን ያየበት ሁኔታ አልነበረም ማለት ይቻላል። ለምሳሌ የትምክህት አስተሳሰብና ተግባር ለበርካታ አመራር ጠፍሮ የያዘውና ከድርጅቱና ከክልሉ በላይ አገራዊ አደጋ ሆኖ ሳለ አመራሩ በየግል በሂስና ግለሂስ ሲታይ የትምክህት አመለካከት ትንሽ ውልብ ብሎ ልብሴ በመንካት አልፎ ሄደ አይነት ግለ ሂስ ነው የሰማነው ። በርካታ የብአዴን አመራር በኢህአዴጉም ይሁን በድርጅቱ የተሃድሶ መድረክ ፀበሉ ሳይነካቸው የወጡ በመሆናቸው ምክንያት ራሳቸው ሳያድሱ በየደረጃው በነበረ መድረክ እንዲመሩ በመመደባቸው መድረኩ በተሃድሶው ስሜትና አቋም ሳይሆን በራሳቸው እምነትና የፖለቲካ አቋም ሲመሩት አስተውለናል።የብተናና የጥፋት አስተሳሰባቸው ላልደረሰው ለሌላው ዘርተው የወጡበት ሁኔታ እናያለን።በተወሰኑ መድረኮች ላይ በአንዳንድ ተቋማት “የትግሬ የበላይነት” አለ የሚል ማጠቃለያ ሰጥተው አባሉ

ያሰናበቱ የማ/ ኮሚቴ አባላት አሉ።በብዙ አከባቢዎች ህዝቡ በክልሉ ያለው ዋናው ችግር ክልሉ በጥፋት ኃይሎች

በመመራቱና የከፋ የመልካም አስተዳደር ችግር መኖሩ ሳይሆን የወልቃይት ጥያቄ አለመመለሱ ነው የሚል እምነት እንድይዝ ጥረት ያደረጉና በአንዳንድ አከባቢም የተሳካላቸው ከፍተኛ አመራሮች አሉ።”ፍየል ወድያ ቅዝምዝም ወዲህ” አሉ! በህዝብ ጭፍጨፋ ተሳትፈዋል ተብለው ታስረው የነበሩ አስፈፃሚ አካላት ለማስፈታት የተደረገ ትግልና

እንቅልፍ የለሽ ጥረታቸው ብዙ ሰው ሰምቶታል።ከነ ደጀኔ ማሩ ጀምሮ በርካታ የጥፋትና የብተና ኃይሎች አባላት የሆኑ ግለሰቦች በኮማንድ ፖስቱ እንዳይያዙና እንዳይፈረድባቸው ምህረት ሰጥተናቸዋል ተብሎ ከለላ ለመስጠት የተደረገ ሩጫና በመጨረሻ ፌዴራል ስለሚፈልጋቹ ውጡ ብሎ የሚሸኝ የብአዴን የጥፋት ቡድን ከነ ሙሉ ትጥቁ ባለበት ሁኔታ ተሃድሶ አገሩ ከወዴት ነው? ረብሻው የመራ ከማ/ኮሚቴ አባላት ጀምሮ የነበረው የመንግስት መዋቅር ላይ እርምጃ አለመወሰዱ ብቻ ሳይሆን ከሌላው አባል በፊት እነዚህ አጥፊዎች መልሶ ለመመደብ የነበረ ሩጫ በርዮ 2016 ኦሎምፒክ ቢሆን ኖሮ በርግጠኝነት ኢትዮጵያ የወርቅ መዳልያ ቁጥሯ ከፍ ብሎ ደረጃዋም በከፍተኛ ደረጃ ታሻሽል ነበር።

አብዛኛው የብአዴን አባል ከሌላው ብሔራዊ ድርጅት አባላት በተለየ የብአዴን ኢህአዴግ መታደስ ይፈልግና በጭንቀት ይንፈራገጥ ነበር። ለምን ቢባል ድርጅቱ የከፋ ችግር ውስጥ እንዳለና በዚህ ምክንያት ትልቅ ዋጋ ለመክፈል እንደሚችል ያውቅ ስለነበር ነው።በድርጅቱ ጥቂት ግን ወሳኝ ሚና የነበረው የጥፋት ቡድን ተሃድሶውን ከመሰረቱ ሳይቀበለው ምን አይነት ተሃድሶ ሊካሄድ ይችላል?ምንስ ተካሄደ?መልሱ ለመላ አገሪቱ ህዝብ በተለይ ለክልልችን ህዝብ ግልፅ ነው።ዋናው ጥያቄ ግን የድርጅቱ ጤናማ አመራርና አባላቱ እንዲሁም ኢህአዴግ ምን ለማድረግ አስበዋል?የሚለው ነው። እኔ እንደ አንድ ለውጥ ፈላጊ ሰው ምን ይደረግ? የሚል አስተያየቴ ባለፈው ፅሁፌ ገልጫለሁ።እሱም መሰረታዊ የመላ አካላቱ ቀዶ ጥገና ሲሆን ህክምናው ውጤታማ የሚሆነው ግን በስመ ዶክተር ከጥቂቶቹ በስተቀር በድርጅቱ አመራርነት ያሉ አንዳንድ ዶክተሮች ካልተሳተፉበት ነው።

የደኢህዴን ጉዳይ ሾላ በድፍኑ እንደሚባለው አይነት ነው።አሁን ባለው አገራዊ ሁኔታ ሁኘ ስመለከት ደኢህዴንና የደም ግፊት ያለበት ሰው ተመሳስለውብኛል። ከሌሎች በጭቅጭቅ ላይ አሉ የሚባሉ እህት ድርጅቶቹ ጋር ስሙ እንዳይነሳ፣በውስጡም ልዩነት የሚመስል ነገር ትንፍሽ እንዳይባል፣በውስጡ ጤንነት የጎደለው ብዙ ሰው ሆኖ እያለ የደም ግፊት ያለው ሰው በውጭ ምንም የጤንነት መጓደል ያለው እንደማይመስል ሁሉ ጤነኛ መስሎ ለመታየት እየጣረ ያለ ድርጅት ሆኖብኛል። የፍጭት ድምፅ ስላልተሰማ ብቻ ራሱን ከሌላው የተሻለ አድርጎ የሚያስብ ነው።በመንገዱ አደናቃፊ ድንጋይና እሾህ እያለ ድንጋዩ ሲነሳ ኮሽታ ከሚሰማ አለመጓዝን አስቦ የሚንቀሳቀስ ሆኖም ይሰማኛል።ለዚህም ይመስለኛል በህግ ይጠየቁ ይሆናል ብለን ስንጠብቃቸው የነበሩ የደኢህዴን ከፍተኛ አመራር የነበሩ አንድ ሚኒስትር የተሃድሶ ግምገማ በተጀመረበት ወቅት ከኃላፊነት ወርደው፣ማንኛውም ከፍተኛ አመራር በግምገማ በተጠመደበት ወቅት በትምህርት ሽፋን በጠቅላይ ሚኒስትሩ ፍቃድ ከአገር የወጡት። ይባስ ብሎ “ግንባር

ላይ ያለ ጉድፍ ለራስ አይታይም” እንዲሉ ደኢህዴን በአንድ ድርጅት በውስጡ ያለና እሱ በሚያስተዳድረው ክልል በርካታ የብሔር ግጭቶች ተከስተው መፍታት ሳይችል የደኢህዴን ሊቀመንበር “የኢህአዴግ ችግር ህዋሃትና ብአዴን

የድንበር ግጭታቸው ሳይፈቱ መቆየታቸው ነው።” ሲሉ መደመጣቸው አስገራሚ ነበር።በተሃድሶ ወቅት አቶ ኃይለማርያም ወደ ቴሌቭዥን ደጋግመው በቀረቡ ቁጥር ደጋግመው ያነሱት ስለ ሁለቱ ክልል የድንበር ግጭት ነበርና ወዴት ወዴት ነው ነገሩ ያስባለ ነበር።ምልአተ ህዝቡ ከድርጅቱ ብዙ አዲስ ነገር ሲጠብቅ የኢትዮጵያ ህዝብ ጥያቄ

መልስ የሚያገኘው ግጨው የተባለ በሰሜን ጎንደርና በምእራብ ትግራይ መካከል ያለው የድንበር አለመግባባት ሲፈታ ነው አይነት እንድምታ ያለው መልስ ሲሰጡ ሰምተናል።

ሌላው ይቅር የደቡብ ኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰብ ለዘመናት ከሰው በታች ሁለተኛ ደረጃ ሰው አድርገው ይቆጥሩት የነበሩ ኃይሎች ገርስሶ እኩልነቱ ያረጋገጠለትን ስርአት ሲያፈርሱት እንኳን ጉዳዩ የሌሎች ክልሎች አድርጎ ያየና ዝምታን የመረጠ ድርጅት ነው። ጉዳዩ ወደ ጓጓው ገብቶ በዲላ ቃጠሎ እስኪነሳ ድረስ በደኢህዴን እምነት ጉዳዩ በስርዓቱ ላይ የተደቀነ አደጋ ሳይሆን በጠገዴና ፀገዴ ያለው የድንበር ውዝግብ ነው።ግጭት በነበራቸው የተወሰኑ አከባቢዎች የብሔር ብሔረሰብ እኩልነት የሚወክል አርማ ያለበት ሰንደቅ አላማ ሲቃጠል መብቴ ተነካ በሚል ሆ ብለው እንዲነሱ የምትጠብቃቸው በክልሉ ያሉ ብሔር ብሔረሰብና ህዝቦች ናቸው። ግን አላየንም ። ለምን ከተባለ የመሪ ድርጅቱ የ አስተሳሰብ ጉዳይ ሆነና ነው። በመሆኑም ደኢህዴን ራሱን በተሃድሶ መንገድ ሲያይ በመካከል የሌላ አካል ምስል እየጋረደው ስልነበር ራሱን በደንብ አላየም የሚል ሃሳብ ነው ያለኝ።

ለኔ ከሁሉም በላይ የገረመኝ ግን ስለ ህውሃት ነው።ህዋሀት ከትግራይ ህዝብ ጋር በመሆን በዚህ ለውጥና እድገት የማይተካ ሚና መጫወቱ የሚክድ ካለ ታሪክን ከግሉ ፖለቲካዊ አቋም ጋር አያይዞ ማየት የሚፈልግ ብቻ ነው።የህዋሃት የትግል፣ የህዝዊነት፣የለውጥና የተግባር ምሳሌነት ግን አሁን በቦታው የለም ብቻ ሳይሆን በአንዳንድ ሁኔታና በአንዳንድ ተግባሮች ዘንድ በርካታ አመራሮች በመጥፎ ምሳሌ የሚነሱ እየበዙ ነው።የክራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር ለነሱ ሩቅና ነውር ሆኖ ይታያቸው የነበረ አሁን በደንብ አንጥፈው የተኙበት እየተበራከቱ ናቸው።የሚገርመው ነገር እነዚህ ሙሰኛ አመራሮች ስለሚጠረጠሩበት ሙስና ሲነሳባቸው እንኳን እኛ ብዙ መስዋእትነት የከፈልን ሌላው እንኳን እየበላ ነው የሚል አመክንዮ ሲደጋግሙ የመደመጡ ሰዎች መኖራቸው ነው።በድርጅቱ በርካታ በሙስና የማይታማ አመራር ያለ ቢሆንም አንድም ታግሎ የመቀየር አቅም የሌለው ነው አልያም ትንሿ አቅሙ በክፋት ተተብትባለች ይላሉ አባሎቻቸው። በዚህ ምክንያት ለውጥ ለማምጣት የተቸገሩ ይመስለኛል። የከፋ ነገር ደግሞ ከመለስ በኃላ እንደ አቡነ ዘመሰማያት የሚደጋግሙት “የመለስና የሌሎች ሰማእታት አደራ እንፈፅማለን”እያሉ ሲዘምሩ በተግባር የእርስ በርስ መነቋቆርና መተማማት እየተበራከተ መምጣቱ ነው።

ሌላው በጥቂት አመራሮች ያለ መሰባሰብ ስሙ ቡድንተኝነት ሳይሆን አብዮታዊ ያልሆነ ግንኙነት ይባላል ይላሉ አሉ።ከመለስ በኃላ አዲስ ሃሳብ የሚያመነጭ የለም ሲባል ነበር ለካስ አለ ።እንዲህ አይነት ሃሳብ ግን በልማት ማፋጠን ዙርያ ቢሆን እንዴት ጥሩ ነበር መሰላቹ።

ሌላው የመለስ ጋቢ ተከናንባቹ፣የመለስ ስም እያነሳቹና መለስን የመሃላ መፈፀምያ መሳርያ እያደረጋቹ ክብር ለማግኘትና ጉድለታቹ ለመሸፈን የመንቀሳቀስ ነገር ገና አልሰለቻቹም ይባላል።ይህ ሁሉ እየሆነ ያለው ጠላቶች የህዋሃት ታሪክና መስዋእትነት በወንጀልና ተጠያቂነት እንዲተካ ጥረት እያረጉና በተወሰነ ደረጃም እየተሳካላቸው ባለበት ሁኔታ መሆኑ ለየግላቹ የሚሰጣቹ ስሜት ምንድነው? “አንንተ ቆዩ እኔ ልሰዋ” ብሏቹ እናንተ እንድትቆዩ እሱ

መስዋእት ከፍሎ አሁን ላይ ደርሳቹ በተሽከርካሪ ወንበራቹና በዘመናዊ መኪኖቻቹ ሆናቹ ትዝ ሲላቹ ምን ትላላቹ? በኔ እምነት ታግሎና አታግሎ እዚህ ላደረሳቹ ህዝብ ፍትህ ነፍጋቹ፣አገልግሎት ከልክላቹ፣ ጉቦ ተቀብላቹ፣ ዴሞክራሲው አጥብባቹ፣ አገር እንድታለሙበት የተሰጣቹ በጀት ወደ ቆንጥራቹ ለግላቹ ወስዳቹ ትግራይ በሚፈለገው እንዳትለማ አድርጋቹ፣ካንተ ቀድሜ እኔ ልሰዋ ቀርቶ ከህዝብ ሰርቄ ቀድሜ ልበልፅግ እያላቹ፣ሰኔ 15 ሲደርስና ጉባኤ ሲሆን

የሰማእታት ስምና ፎቶ እያነሱ ደጋግሞ መሃላ ማካሄድ የሰማእታቱ አጥንት ከየ ተራራው እየሰበሰባቹ ገበያ አውርዳቹ ለሽያጭ ከማቅረብና ከዚህ ጥቅም ከመፈለግ ውጭ በፍፁም ሌላ ትርጉም የለውም። ግን ለምን? ግን እንዴት?

ይህ ከላይ የተገለፀው ሀሳብ ለሁሉም አመራርና አባል ይመለከተዋል ማለት አይደለም።እየተካሄደ ባለው ተሀድሶ በአንዳንድ ጥቃቅን ነገሮች ትንሽ የተሻለ ሁኔታ አልነበረም ማለትም አይደለም።እነዚህን ከለውጥ መቁጠር ማለት በራስና በህዝብ እንደመቀለድ የሚታይ ነው።እባካቹ ህዝቡ ተመልሶ መከራ ውስጥ የገባው በእናንተ ስንፍና ነው።ህዝቡ በዚህ ሁኔታ እያለም እናንተ የሚያስጨንቃቹ የግል ክብራቹና የግል ተጠቃሚነታቹ ነው።ከህዋሃት አመራር እንዲህ ያለ ነገር መስማት ይገርማል!!

በአጠቃላይ በኢህአዴግ በቅርቡ በነበረው የተሃድሶ መድረክ ግምገማው ከነብዙ ድክመቱ ከሌላው ግዜ የተሻለ ነበር ብለውኛል።እንደ ሰማሁት ከሆነ ችግሮች ከሰው ጋር ለማያያዝ የተሞከሩበት ሁኔታም አጥጋቢ ባይሆንም አይከፋም። ግን ምን ዋጋ አለው?የኔ ዋናው ችግር ያለው “ስልጣንን ለህዝብ አገልግሎት ሳይሆን ለግል ጥቅምና ብልፅግና መፈፀምያ መሳርያ ማድረጋችን ነው።” ብሎን ስያበቃ በነማን ስንለው እንዳው ለነገሩ ነው እንጂ እያለን ነው። ግምገማውም ቢሆን ከሌላው ግዜ መሻሉን እንጂ እንደ ዘንድሮ በርካታ የኃይማኖት አማኞች ጧት “የዛሬው ማረኝ ሁለተኛ አልደግምም ብሎ” ከምሳ በኃላ ተመሳሳይ ወይም የባሰ ጥፋት ሲፈፅም የሚገኝ አይነት ሆነብኝና ጨነቀኝ።ከችግሩ ጋር የሚመጣጠን እርምጃ አለመውሰድ ሌላው የተሃድሰው መሰረታዊ መሸርሸር ነው።በተለይ ከፍተኛ አመራሩ ላይ ሲደርስ መቅኔው ፍስስ የማለቱ ነገር አስገራሚ የሚሆነው ኢህአዴግ ለመሰረታዊ ለውጥ ቆርጨ ተነስቻሎህ ብሎ ፀረ ትምክህት፣ፀረ-ጠባብነት፣ፀረ-ኮራብሽን፣ፀረ-አደርይባይነት፣ፀረ-መልካም አስተዳደርና ፀረ- አንድነት አመለካከትና ተግባር ወዮላቹ ብሎ ዘራፍ ሲል ስንሰማ ተስፋችን ከፍ ካለ በኃላ ይህንን ለመናድ የተሰለፉ የታንክ አፈሙዞች አገሪቱን ወደ ጥፋት እየመራ የሚገኝ ከፍተኛ አመራር ላይ ሲተኩሱ ውሃ የመትፋት ጉዳይ ምክንያት ብፈልግ አላገኘሁም።”ከፍተኛ አመራሩ የተዘፈቀው በገንዘብ ኮራብሽን ሳይሆን ከሱ በባሰ የፖለቲካ ኮራብሽን ነው” አሉን።ታድያ የወሰዳችሁት የፖለቲካ እርምጃ የታለ?ስንል የለም።አመራሩ እርስ በርሱ መደፋፈር እንዳቃተው የበግሉ ሲናገር ያምናል። አመራሮቹ በየግል ወደ ሚድያ ቀርበው ሲጠየቁ የተለያየ መልስ ሲሰጡ ሰምተናል። አንዱ ተሃድሶ የመስመር ማጥራት እንጂ ሰው የማሰር አላማ የለውም ሲል ሌላው ራሱ ከደሙ ንፁህ በማድረግ ጥፋት የፈፀሙ አንለቃቸውም እርምጃ እንወስዳለን ይላል።ሌላው እርምጃ ያልወሰድንበት ምክንያት በከፍተኛ አመራሩ ማስረጃ በሰማይም በምድርም ፈልገን ስላጣን ነው ብሎውናል።

ውድ አንባብያን እዚህ ላይ ለከፍተኛ አመራሩ ማስረጃ ከታጣ ለመካከለኛና ዝቅትኛ አመራሩ ወደ ህግ ለማቅረብ ማስረጃ የተገኘው በየትኛው ክሊኒክ ወይም ሆስፒታል ያለው ላቦራቶሪ በተደረገ ምርመራ ይሆን የሚል ጥያቄ አላነሳችሁም?እኔ ግን አዎ አንስቻለሁኝ።

ኢህአዴግ ገዢ ፓርቲ እንደመሆኑ የድርጅቱ ተሃድሶ የአገር ተሃድሶ እንጂ የአንድ ፓርቲ ተሃድሶ ሊሆን አይችልም።ስለሆነም ይህ የተሃድሶ ንቅናቄ በድርጅቱ በራሱ እየታየ ካለው ከመንገድ የመንሸራተት አደጋ ወደ መንገድ የመመለሱ ጉዳይ እንደተጠበቀ ሆኖ የታዳጊ ክልልች ህዳሴ እንዴት እየተረጋገጠ እንደሆነ ካልተፈተሸ በስተቀር አገር ሆነን የመቀጠላችን ጉዳይ በችግር ውስጥ መውደቁ አያጠያይቅም።

በጋምቤላ በኑዌርና አኝዋክ ያለ ውጥረትና በአኝዋኩ ያለ የመገለል ስሜት እንዲሁም በሁለቱም ያለ ደገኛውን የመጥላት አስተሳሰብ፣በቤንሻንጉል ያለ የአቅም ውስንነትና በጎሳዎች መካከል ያለ አለመተማመን፣በአፋር ያለ የከፋ የማስፈፀም አቅም ማነስ፣ የተማረ ሰው ጥላቻ፣ በክልሉ ባሉ ጎሳዎች ያለ የገመድ መጉተት ፍኩክር፣ በሱማሌ ክልል ያለ ፀረ-ዴሞክራስያዊነትና የተወሰኑ ጎሳዎች ተገልለናል የሚል አስተሳሰብ እንዲሁም በሁሉም ክልሎች ያለው በህግ የተደነገገ በሚመስል መልኩ የክራይ ሰብሳቢነት ዘመቻ፣ህዝብን ማገልገል ሳይሆን ህዝቡን እንደ የራስ መገልገያ መሳርያ የማየት አዝማምያ ተደማምሮ ህዝቡ የልማት ተጠቃሚ ባለመሆኑ በስርአቱ ላይ አደጋ ከተቃጣ ዋስትና ይሆናል የሚባል ህዝብ አሁን አሁን ፀረ መንግስት አቋም እያዳበረ እየመጣ ያለ በመሆኑ በስርአት የተመራ የተሃድሶ መንገድ ውስጥ ገብተው ተጨባጭ ለውጥ እንዲያመጡ መስራት ካልተቻለ አደጋው የከፋ ነው።

የኢህአዴግ የፖለቲካ ስራዎች ውድቀት በዚህ በተሃድሶ ግዜ ብቻ የታየ አይደለም።መሰረታዊ ውድቀቱስ ምን ሆነና ነው።ኢህአዴግ እንኳን የጠላቱን ፕሮፖጋንዳ በብቃት ለመመከት የሚያስችል ስራ ሊሰራ ይቅርና የሰራውን በቅጡ መግለፅ መቼ ይችልበታል።በጎንደር እየተረዳሁት እንዳለሁ አንዳንድ አመራርና ፅንፈኛ ዳያስፖራ በዘሩት እሾህ በህዝብ ዘንድ በርካታ የአስተሳሰብ ችግሮች ሰፊ ስፍራ ይዘዋል።የጎንደር ህዝብ ኃይማኖተኛ እንደሆነ ስለሚታወቅ ጧት ጧት ቤተክርስትያን ሲሄድ ፈጣሪ ይነግረዋል በሚል ይመስለኛል ብአዴን ይህንን ከህዝብ አስተሳሰብ ሙሉ በሙሉ ያልተፋቀው የወልቃይት ጉዳይ ዋነኛ የህዝብ ጥያቄ አድርጎ የማሰብና የትግራይ ህዝብን አስመልክቶ ያለው የተዛባ አመለካከት በመቅረፍ ወደ ልማት እንዲያስብ ማድረግ አልተቻለም።አለመቻሉ ብቻ ሳይሆን ይህንን አስተሳሰብ ከህዝቡ እንዳይወጣ በበርካታ አመራሮች ስራ እየተሰራ ይገኛል።አሁንም በተለያየ ግዜ የተለያዩ ሁኔታዎች እየተነሱ የህዝቡ ሰላማዊ አስተሳሰብ የሚሸረሽሩ እየበዙ ናቸው።የኔ ሶስተኛ ታናሽ ወንድሜ ድንጋይ በመወርወሩና ንብረት በማውደም ተሳታፊ ስለነበር በኮማንድ ፖስት ተይዞ ብርሸለቆ ተሃድሶ ወስዶ የተለቀቀ ሲሆን ብርሸለቆ እያለ በወሰደው ትምህርት ምን ያክል የአስተሳሰብ ለውጥ አምጥቶ እንደተመለሰ ሰምቻለሁ። ወድያውኑ እንደመጣ እቤት ለነበሩ ሁለት ወንድሞቼ መምከር ጀምሮ ነበር።አሁን አሁን ደግሞ ተመልሶ ግራ የመጋባት ሁኔታ እንዳለው ስለተነገረኝ በስልክ ጥያቄ ሳነሳለት ግራ መጋባቱ በማመን ምክንያት የሚለው እዚህ የቆየን አብዛኛው ወጣት ምንም አይነት የፖለቲካ ስራ ያልተሰራበት በመሆኑ የምትነግረው እውነታ አይቀበልህም ብቻ ሳይሆን በየሄድክበት ቦታ እንደ አዲስ ይቀሰቅሳሃል፣ግራ ያጋብሃል ብሎኛል። በወንድሜ እምነት ከዚህ በኃላም ሩቅ ባልሆኑ ወራቶች በጎንደርና አንዳንድ ቆላማ ወረዳዎች ግርግር መፈጠሩ አይቀርም።በራሴ ለማረጋገጥ እንደቻልኩትም የጥፋት ኃይሉና አመራሩ የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ የሚነሳበት ቀን በጉጉት እየጠበቁት ነው። ይህ በከፋ ሁኔታ ያለን የጎንደር ህዝብ አነሳን እንጂ በሁሉም ክልሎች የተሀድሶ ስሜትና አላማ ወደ ህዝቡ በሚፈለገው ደረጃ እየወረደ አይደለምና ይታሰብበት።

ኢህአዴግ እነዚህ ከላይ የተገለፁ ታዳጊ ክልሎችና ህዝቡ ላይ ተገቢው የተሀድሶ ስራ ካልሰራ ብዙ አካሉ የጎደለ ፍጡር ይሆናል።በዚህ አካል ጉዳተኝነት ወደ አከባቢ ምርጫ እየደረሰ ሲሆን በቅርቡ በደቡብ አፍሪካ በአከባቢ ምርጫ ትልቅ ኪሳራ ያጋጠመው ANC አይነት ሳይሆን የከፋ ችግር ይገጥመዋል።ይህ ችግር ካጋጠመው ዞንና ወረዳ የሌለው የኢህአዴግ መንግስት ይሆንና ያለ እግር ልጓዝ ብሎ ተላልጦ ይሞታል።

ሚድያ ፣ ህዝብና አገር፤

ይቅርታ ይደረግልኝና ዛሬም ሚድያውን መውቀሴ አልቀረም።ሚድያ ከቴክኖሎጂ ማደግና ከግሎባላይዜሽ ጋር ተያይዞ በአንድ ሰውና በአንድ ቤት የተደረገ ነገር በአንድ ሴኮንድ በመላው አለም የመዳረስ አቅም አግኝቷል።ሚድያ በርካታ ተልእኮ እንዳለው ሲነገር እኔም እንደ እናንተ ሰምቻለሁ።ከነዚህ ውስጥ የአንድ የኢኮኖሚ ስርአት ማገልገል፣ ማዝናናትና ማሳወቅ ወ.ዘ.ተ ይባሉ እንጂ ዞሮ ዞሮ በሁሉም መስክ ተፅእኖ ማሳደር የሚለው ዋነኛ እንደሆነ ክርክር የለውም።በዚህ ረገድ በአለም የተከሰቱ የቀለም አብዮቶች፣ጦርነቶችና ግጭቶች የሚድያ ድርሻ በጣም ከፍተኛና ወሳኝ እንደነበር ከሩቅ እስከ ቅርብ የነበሩ ታሪኮችና ሁኔታዎች ቁልጭ አድርገው አሳይተውናል። በቬትናምና አሜሪካ ጦርነት ወቅት፣በቅረቡ በግብፅ የተካሄዱ የመንግስት ለውጦች፣ሁሉም የቀለም አብዮቶች በመሳሰሉ ሚድያዎች የነበራቸው ድርሻ መተክያ እንዳልነበረው ማየት ይቻላል።

ሚድያ የአንድን አገር የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ያሰቀይራል።በአገራት መካከል ያለን ግንኙነት ያሻሽላል ያበላሻል።በአጠቃላይ ሚድያ የአንድ አገር ህዝብ አስተሳሰብ ወደ ሚፈልገው መንገድ በመዘወር በሌላው ህዝብ፣በራሱ መንግስት እንዲሁም በአለም አቀፍ ሁኔታ የጥፋት ወይም የድጋፍ አስተሳሰብና እርምጃ እንዲወስድ የማድረግ አቅም አለው።ይህ ከሆነ ዘንዳ ሚድያ አይደለም አንድ አገር አለምን የመቀየር አቅም አለው። በቅርቡ በቱርክ መፈንቅለ መንግስት ሙከራ ከተካሄደ በኃላ የቱርክ ሚድያዎች በመፈንቅለ መንግስቱ ጀርባ አሜሪካ እጇ አለበት በሚል መዘገባቸው ብቻ በወቅቱ 75% የቱርክ ህዝብ ፀረ አሜሪካ አቋም መያዙ በወቅቱ የተሰበሰበ የህዝብ አስተያየት ያስረዳል።የእንግሊዝ ህዝብ አገሩ ከአውሮፓ ህብረት መውጣት እንዳለባት ሲወስን ሚድያ ትልቁ ድርሻ እንደተጫወተ ተደጋግሞ ሲነገር ሰምቻሎህ።አሌክሳንደር ቤስት የተባለ የሶሻል ሳይንስ ሙሁር TED በሚባል የሃሳብ

መንሸራሸርያ ሚድያ why brexit happened and what to do next በሚል ሚድያው ላይ ቀርቦ በገለፀው ሃሳብ እነዚህ ከአውሮፓ ህብረት እንውጣ ብለው ድምፅ የሰጡ አከባቢዎች ከሕብረቱ ይበልጥ ተጠቃሚ ነበሩ ብሎ ሚድያው ተጠቃሚነታቸው ሳይገልፅ መለየታቸው እንደሚጠቅማቸው በመቀስቀሱ ፀረ-ጥቅማቸው ድምፅ እንዲሰጡ ማድረጉ ይገልፃል። የአገሪቱ ህዝብ ተጠቃሚነቱ የሚፃረር አስደንጋጭ ውሳኔ ከወሰነ በኃላ አንዱ ጠ/ ሚኒስትሩ ህዝበ ዉሳኔ በመጥራቱ ተጠያቂ ሲያደርግ ሌላው ለተማረው ክፍል፣ የተማራው ላልተማረው በመወንጀል ተጠያቂ ማድረግ ጀምረዋል ይላል።

በአሁኑ የአሜሪካ ምርጫ ሄላሪ ክሊንተን ከተመራጩ ፕሬዝዳንት የተሻሉ ነበሩ የሚል የብዙ የአለም ክፍል አስተያየት ነው።በተወካይ ተወካይ ሳይሆን በህዝብ ምርጫ ክሊንተን ከሁለት ሚልዮን ድምፅ በላይ ትራምፕን በልጠው እንደነበር እንደተጠበቀ ሆኖ በዴሞክራቶች መካከል በነበረ ምርጫ አቶ አንደርሰን ከክሊነቶን የተሻለ ለአብዛኛውና ለታችኛው የህብረተሰብ ክፍል የሚጠቅም የምርጫ አጀንዳ ነበራቸው።ሚድያው በተጫወተው ሚና ግን እኛ 99%

አሜሪካውያን በ1% እየተጎዳን ነን ያለው አሜሪካዊ ለድሃው የተሻሉ የተባሉ ተመራጭ ጥሎ ሄላሪን ወከለ። እንዲህ እያልን ብዙ ምሳሌዎች ማቅረብ ይቻል ይሆናል።ከዚህ ብቻ መረዳት የሚቻለው ሚድያ የዳበረ አስተሳሰብ አለው ለሚባል ማህበረሰብም ጭምር ተፅእኖ ፈጥሮ ፀረ ተጠቃሚነቱ ማሰለፍ ይችላል ነው።

ወደ ራሳችን ቤት ወደ አገራችን እንመለስና ሚድያው ለዚህ አገር አንድነት፣ ሰላም፣ዴሞክራሲና ልማት እያበረከተው ያለ አስተዋፅኦ በሚፈለገውና በሚገባው ደረጃ አይደለም የሚል እምነት አለኝ።ይህ ሲባል ምንም አልሰሩም እያልኩ እንዳልሆነ ግን ግንዛቤ ውስጥ እንዲገባልኝ እፈልጋለሁ። ለምሳሌ ከመጀመርያው ተሃድሶ በኃላ ድህነት ከምንም በላይ

ጠላታችን እንደሆነ፣በሚሌንየም አከባቢ ውጭ የሚገኘው ዳያስፖራ ወደ አገሩ ገብቶ በልማት ተሳታፊ እንዲሆንና በፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ላይ መሆናችን፣ ገፅታችን እየተቀየረ መሆኑ በመሳሰሉት የተሰራ ስራ አለ።ለዚህም ተገቢው ዋጋ እሰጣለሁ።ይህ ግን በዋናነት በመንግስት ሚድያዎችና የተወሰኑ ኃላፊነት አለብን ያሉ የግል ሚድያዎች የታጠረ ነበር ብሎ መናገር ይቻላል።በቁጥር አንድ ወይም ሁለት ከሚባሉት የግል ሚድያዎች በስተቀር አንዳንዶቹ ጭራሽ የተሰራ በጎ ስር እንዳይታየን መጋረጃ ሲፈልጉ፣አንዳንዶቹ ሰላም ልማትና ዴሞክራሲ የሚባሉ ቃላቶች ኢህአዴግ የፈጠራቸው ስለሚመስላቸው እነዚህን ቃላት አንስቶ መፃፍ ወይም መናገር ገለልተኛ አልባልም ብሎ የሚያስብና አንዳንዱ ደግሞ በነፃ ፕረስ ስም ከፖለቲካዊ አቋሙ አንፃር ሆን ብሎ አጣሞ ለህዝብ በማቅረብ ህዝቡ የተሳሳተ ውሳኔ ላይ እንዲደርስ ወገቡ ታጥቆ ይሰራል።እንደኔ ትእዝብት ጠቅለል ባለ መልኩ ሲታይ የአቅም ውስንነት፣የልምድ እጥረት፣የፖለቲካ መሳርያ አድርጎ መጠቀም በመሳሰሉ ጉዳዮች የተተበተበ ነው።በቅርቡ እሁድ ጧት በሸገር ሬድዮ በሚድያ ዙርያ በነበረ ጠቃሚ ውይይት ተወያዮቹ በችግሩና በችግሩ ምንጭ ዙርያ ጠቃሚ ሃሳቦች አንስቷል።በተለይ ከፎርቹን ጋዜጣ ይቀርብ የነበረ ሃሳብ ድጋፍ አለኝ።

አንዳንድ ጋዜጠኞች በሌላው ማህበረሰብ ያለው የልምድ፣አባባል፣የታሪክና የባህል ሁኔታ ምንም ግንዛቤ እንኳን ሳይኖራቸው አለምን የሚያዳርስ የሬድዮ ወይም የቴሌቭዥን መነጋገርያ በእጃቸው እንዲጨብጡ በማድረግ ግራ ገብቷቸው ግራ ያጋባሉ።አንድ የFM 97.1 ጋዜጠኛ “በተለምዶ የአክሱም ሃወልት እየተባሉ የሚጠሩ በአክሱም የሚገኙ ሃወልቶች” ብሎ አቅርቧል። ስለ ስምና የተለምዶ ስም ልዩነት ማን ይንገርልኝ።ይህ ስም ማጥፋት ነው ካላቹ የ17/12/2008 ዓ/ም ፕሮግራማቹ ፈትሹ።ርእስ መረጣና ዝርዝሩ የተዛባ መልእክት ማስተላለፍ ብዙ ነው። በ13/01/2009 ዓ/ም የሸገር የቀትር ወሬ ላይ መንግስት የአ/አበባ የቤት ችግር በኮንዶምንየም አልፈታም አለ ይላል።ኮንደምንየም መስራት አቆመ ብየ ዝርዝሩ ጠብቄ ስሰማ ከኮንዶምንየም በተጨማሪ ሌሎች አማራጮችንም መፈለግ እንደሆነ ተረዳሁኝ። ብዙ ግዜ የሚገርመኝ አንድ የግል ተብሎ የተሰየመ ሚድያ የግል የሚባለውና ገለልተኛ መሆኑ የሚረጋገጠው ስለ መንግስት ጥሩና ድክመቱ ሰብሰብ አድርጎ በመጥፎ የሚፅፍና የሚናገር እንደሆነ የሚያስብ፣ ሚድያ ሚድያ የሚባለው ስለ ሰላም ሳይሆን ስለ ጦርነት ሲዘግብ እንደሆነ፣ምልአተ ህዝቡ ሰላም ሆኖ ከታያቸው በህዝቡ ውስጥ የሁለት ጎረቤታሞች ግጭት እንዴት ወደ ህዝብ ለህዝብ ግጭት ተሸጋግሮ ለዜና እንዲበቃ መደረግ እንዳለበት መፀለይና መጓጓት የሚድያ ግብ አድርጎ የሚያስብ አስተሳሰብ መንገሱ ነው።የአገሬ የሚድያ ማህበረስ ሆይ! አገራችን በማህበራዊ ሚድያ የተዛቡ መልእክቶችና ቅስቀሳዎች ገብታበት የነበረ የጨለማ ጉዞ አይታቹሃል። የሌላ አለም ተሞክሮም ብዙ ነው።በሚድያ ስራ በርካታ አገሮች ፈርሰዋል።ምናልባት ግን እነዚህ አገሮች በሽግግር መንግስት ወይም በጥምር መንግስት ወዘተ ተመልሰው አገር የመሆን አጋጣሚ ሊያገኙ ይችሉ ይሆናል።እኛ ይህንን አጋጣሚ ደግመን የማግኘት እድላችን ወደ ዜሮ የተጠጋ እንደሆነ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ወይም የፖለቲካ ፍላስፋ መሆን ሳይጠይቅ በተለያየ ቁርሾ የተሞላ የመጣንበት ታሪካችንና በአሁኑ ወቅት ደግሞ ይህንን እንደ መልካም አጋጣሚ በመቁጠር ታሪካዊ ጠላቶቻችን እንዲፋፋም በማድረጋቸው ወዴት አምርቶ እንደነበር ማየት መቻላችን በቂ ነበር።ስለሆነም እባካቹ ይህችን አገር እንደ አገር እንድትቀጥል ኢትዮጵያዊ የዜግነት ግዴታቹ ተወጡ።

ወቅታዊ አለማቀፋዊ ሁኔታና የውጭ ግንኙነታችን፤

ከቀዝቃዛ ጦርነት ማብቃት በኃላ አለም በአንድ የመሀል ዳኛ ብቻ ፍርድ ትቀበል እንደነበረ ሁላችን የምናውቀው ጉዳይ ነበር።ብዙ ሊቃውንት ብለን የምንላቸው ፀሐፍትና የመስኩ ተኝታኝ የሚባሉ ሰዎች ይህ የአንድ የአለም ዳኛና ከሱ ጋር ተያይዞ ያለው አዲሱ ሊበራሊዝም{Nio-liberalism} የአለም ሁሉ አስተሳሰብና መመርያ ሆኖ የሚቀጥልና ምናልባትም እስከወድያኛው የሚተካው አስተሳሰብ አይኖርም ያሉ ብዙ ናቸው።በተነፃፃሪ ብዙ አልቆየም በሚባል ወቅት የዚህ አስተሳሰብ መሸርሸርና አለም ከአንድ አድራጊ ፈጣሪ ወጥታ በቀዝቃዛው ጦርነት ከነበሩት ሁለት አለቆች በላይ ወደ ብዙ ጉልበተኛና አንዱ የአንዱ ተፅእኖ ለመቋቋም ሲል የቻለውን ሁሉ ማድረግ የጀመረበት ሁኔታ እንዳለ እያየን እንገኛለን።ኒዮ ሊበራሊስቶች የአለም መጨረሻ ያሉትን አስተሳሰብ በተግባር መሸርሸር የጀመሩት ራሳቸው ናቸው።ኒዮ ሊበራሊዝም አንድ ድንገተኛ ጎርፍ እንኳ መከላከል የማይችል መሆኑ ተጨባጭ ማሳያ የሆነው እ.አ.አ 2008 ያጋጠመ የኢኮኖሚ ቀውስ ተከትሎ የዚህ አስተሳሰብ ባለቤት የተባሉና ሌሎች አገሮች “በውድም በግድም በዚህ መጓዝ አለባቹ ካልሆነ የተረጋጋ መንግስት ሁናቹ መቀጠል አትችሉም” እያሉ ዱላ ሲመዙ በሌላ በኩል ራሳቸው የአስተሳሰቡ ባለቤቶች የጨዋታው ህግጋት ሲጥሱት ታይቷል። ባንኮቻቸው ሲከስሩ፣ካንፓኒዎቻቸው ሲንገዳገዱና በአንዳንዶቹ በግብርና የተሰማሩ ዜጎቻቸው ከመንገድ እየወጡ መሆናቸው ሲያዩ በጠራራ ፀሐይ የወሰዱት እርምጃ አይተናል ሰምተናል። የሚገርመው ነገር እነሱ በቸገራቸው ግዜ እጃቸው እንኳን ሳይታጠቡ ወደ ገበያው መአድ እንዴት እንደገቡ ግልፅ ሆኖ ሳለ አሁንም በዚሁ አስተሳሰብ አንሄድም ለሚሉ አገሮች እንቀጣለን ማለታቸውና እየቀጡ መሆናቸው ነው።አገራችን የውስጥ ተጋላጭነቷ እንደተጠበቀ ሆኖ በተደጋጋሚ ፈተና ውስጥ እየወደቀች ያለችዉም በዚህ አለማዊ የጦርነት ሜዳ ላይ ነው።እስካሁን በጥናትና በመርህ ላይ የተመሰረተ ፖሊሲ በመከተል፣ በተነፃፃሪ ጠንካራ መንግስት ስላለንና በኢኮኖሚ ትክሻችን በማወፈር ይህንን ተቋቁመን ልክ ከ121 አመታት በፊት በምኒሊክ አመራር በህዝቦች የጋራ ቆራጥነት ፈረንጅን አሸንፈን በጭቆና ለነበሩ የአለም አገሮች ምሳሌ እንደሆነው በዚህ ዙርያም ለሌላው አለም በተለይ ለአፍሪካ አገሮች እንደ ሞዴል ሆነን ወጥተናል። ከአሁን በኃላስ?

ከቅርብ ግዜ ወዲህ በአለም ፖለቲካ እየታዩ ያሉ ተለዋዋጭ ሁኔታዎች ለትንበያ የሚያዳግቱ መሆናቸው እሙን ነው።የቅርብ አመታት ብቻ እንኳን ብንወስድ በርካታ አስገራሚ ነገሮች ስናይ ከርመናል።እነዚህ ሁኔታዎች አንድ ባልደረባየ በአንድ የኮሌጅ መመረቅያ መፅሔት ውስጥ የመጨረሻ ቃል {last word} እየተባለ በሚጠራ ሀሳብ መስጫ ቦታ አንድ ተማሪ አሰፈረው ብሎ የነገረኝ ፅሁፍ ትዝ አስባለኝ።ተማሪው “በማህበረ-ፖለቲካ 1+1=2 የሚባል የለም ይላል አለኝ።” የዚህ ሀሳብ ስሜት ምን እንደሆነ ማብራራት አይጠበቅብኝም።ዋናው ነገር አለማቀፍ ግንኙነትም የራሱ የሒሳብ ስሌት አለውና ይሆናል ብየ ስጠብቃቸው የነበሩ ፍፃሜያቸው ያስገረሙኝ ብዙ ናቸው። ለምሳሌ ብጠቅስ የግብፅ የወታደራዊ መፈንቅለ መንግስትና የአለም ማህበረሰብ ከዝምታ እስከተለሳለሰ አቋም፣ብራዚል በደቡብ አሜሪካ የአለም አንድ ሌላ ዋልታ ማእከል እየሆነች ነው በተባለበት ሁኔታ ወደ ፖለቲካ ቀውስ መግባት፣በተባበሩት መንግስታት ፍቃድና ያለ ፍቃድ የመንን ጨምሮ አገሮች በተናጠልና በህብረት ሌሎች አገሮችን የማጥፋትና የሌላው ዝምታ፣እንግሊዝ ከአውሮፓ ህብረት የመውጣት ውሳኔ፣ የራሻና ቱርክ ማታ ጦር ሲማዘዙ አምሽቶ ጧት የቀለጠ ፍቅር ውስጥ መግባት፣ የኮሎምብያ መንግስት ፋርክ ከሚባል አማፂ ቡድን ጋር ያደረገው የሰላም ስምምነት ህዝቡ በህዝበ ውሳኔ ውድቅ ማድረጉና የትራምፕ ምርጫ ወ.ዘ.ተ ከብዙዎቻችን ግምት ውጭ ይሆናሉ ሳይባሉ ሆኖው ከተገኙ ክስተቶች ውስጥ ተጠቃሽ ናቸው።

በአሜሪካም ሆነ በአውሮፓ ምርጫዎች የቀኝ አክራሪ አስተሳሰብ የበላይነት እያገኘ መሄድ ሳስብ በአገራችን በአንድ ወቅት የነበረ የጫማ ማስታወቅያ ትዝ አስባለኝ “ማምለጥ ነው ለጫማው በኃላ ይታሰብበታል” ይላል።ቅድምያ ለራሴ

ሌላው የራሱ ጉዳይ የሚል አስተሳሰብ እነሱ በበላይነት እናቀነቅነዋለን ከሚሉት ዴሞክራሲም ሆነ ከሰብአዊነት በሚጣረስ መልኩ የፍፁም ግለኝነት አስተሳሰብ እየተራመደ ይገኛል።ከመራመድ አልፎም ወደ አሸናፊነት መምጣት ጀምሯል።ፕሬዝዳንት ትራምፕ ፀረ-እስልምና፣ፀረ-ጥቁር ህዝብ፣ ፀረ-ሴቶች፣ ፀረ-አለማቀፍ ትብብርና ግንኙነት፣ፀረ- ስደተኛ አቋም በግልፅ እያራመዱና ከአሜሪካ ታሪካዊ ጠላት ከምትባለው ሩስያ ጋር የጠበቀ የቢዝነስ ትስስር አላቸው እየተባሉ ባሉበት እንዲሁም ባደጉት አገራት በተለይ በአሜሪካ እንደ አስነዋሪ ተግባር የሚታይ በሰነድ የተደገፈ ግብር ያጭበረበሩ ሰው ቅድምያ ለአሜሪካ ሌላው የራሱ ጉዳይ የሚል መፎክር በማንሳታቸው ብቻ ለስልጣን በቅቷል።ይህ አለማዊ ሁኔታ ለኛ ያለው እንድምታ ምንድነው?

ከቀጠናዊ ጉዳዮች አንፃር ካየንም የገልፍ አገሮች በየመን ምክንያት በሞት አፋፍ የነበረው የኤርትራ መንግስት በመደገፍ ህይወት እንዲዘራ መቻሉ፣የግብፅ መንግስት በዲፕሎማሲና መልካም ግንኙነት ድንኳን ተከልሎ ኢትዮጵያን ለመቅበር መሰረተ ሰፊ ጉድጓድ እየቆፈረ መሆኑ፣የሶማልያ ጉዳይ ብዙም የጎላ መሻሻል ሳያሳይ መቀጠሉና በከባድ ድርቅ መጠቃት የነበረውን የፖሊቲካና ፀጥታ ሁኔታ በአሉታዊ መንገድ ሊጎዳው የሚችልበት እድል እየሰፋ መሆኑ፣የደቡብ ሱዳን ጉዳይ ከመጥፎ ወደ በጣም መጥፎ እያደገ ልክ እንደ ውስጣዊ ጉዳያችን እኛን ልያቃጥለን የጀመረ መሆኑ፣ሁላችን እንደምናውቀው የሱዳን ጉዳይ ጫፉ የታጣ ውስብስብ ያለ ገመድ መሆኑ፣በቅርቡ ከሪፖርተር ጋዜጣ እንዳየነው የሱማሌላንድ ወደቦች የባለ ብር አረብ አገሮች ትኩረት ከመሳብ አልፎ በአፍንጫችን መጥተው ስምምነት እስከ መፈራረም መድረሳቸው፣ ከቅርብ አመታት ወዲህ የኬንያ የፖለቲካና የፀጥታ ሁኔታ እየተወሳሰበ መምጣቱ እንዲሁም ሌሎች የአከባቢ አገሮች ከኢትዮጵያ ጋር የቀጠናው የበላይነት ፍኩክር ውስጥ ገብተው ግስጋሴዋ ያልወደዱላት አገሮች መኖራቸውና የውስጥ ተጋላጭነታችን እየሰፋ እንጂ እየጠበበ ያለመሆኑ ተደማምሮ ለአገራችን ከቅርብና ከሩቅ ግዜ አንፃር እንድምታው ምንድነው?

ይህንን የዲፕሎማሲ ግንባር እንዲሸፍን የተመደበው የውጭ ጉዳይ ሰራዊት በምን ሁኔታ ይገኛል? ብየ ስጠይቅ ምቾት አይሰማኝም።የመጀመርያው ሀሳቤ በውጭ ጉዳይ መሰረታዊ ለውጥ በሚያመጣ መልኩ ተቋም አልተገነባም የሚል እምነት እንድይዝ የሚያስገድዱኝ ሁኔታዎች ስላሉ ነው።የአሰራር ማሻሻያ ጥናት BPR ያለ አግባብና ያለ ማሻሻያው አላማ ለራሳቸው ለሰዎቹ ጥቅም አስቦ የተጠናና የተተገበረ መስራቤት አለ ከተባለ አንዱ ውጭ ጉዳይ ነው የሚል እምነት አለኝ።ዲፕሎማትነት የተከበረ ሞያና አገራዊ ፋይዳውም ከፍ ያለ ሆኖ ሳለ በአሁኑ ወቅት የሞያው ብቃትና ክብር የሚያሟሉ እንዲሁም ለቦታው የሚመጥኑ አምባሳደሮች መኖራቸው እንደተጠበቀ ሆኖ አምባሳደርነት ማለት የተሸጋሸጉ አመራሮች ማረፍያ፣ያኮረፉ አመራሮች ማስተንፈሻ፣ የአመለካከት ችግር አለባቸው ተብለው የተጠረጠሩ ማስረጃ የታጣባቸው አመራሮች መጠግያ እንዲሁም ከሞያው ብቃት ውጭ የብሄራዊ ተዋፅኦ መርህ መተግበርያ ሆኖ ይታያል።ከብዙ ሰዎች እንደሚሰማው ከድሀው ህዝብ ግብር ተሰብስቦ ዶላር የሚከፈላቸው ብዙ ዲፕሎማቶች ህዝቡን ለማገልገል ካላቸው ጉጉት ይልቅ ቤተሰቦቻቸው ወደ ውጭ ወስደው እዛው ለማስቀረት ያላቸው ተነሳሽነት ከፍተኛ ነው ተብሏል።በርካታ ዲፕሎማቶች ወደ አገር የሚመለሱም ቢሆን አገራዊ ስሜት ኑሯቸው ሳይሆን ከቀረፅ ነፃ መብት ተጠቅመው ተጨማሪ ጥቅም ለማጋበስ እንጂ የመመለስ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ጥቂቶች ናቸው ይባላል።

የህዝብና የመንግስት ዶላር እየበሉ በፅንፈኛ ዳያስፖራ የፖለቲካ አክራሪነት ተፅእኖ ውስጥ ገብተው ፀረ-መንግስትና ህዝብ የሚንቀሳቀሱም ቁጥራቸው ቀላል አይደለም ተብሏል።

ከሁሉም በላይ የውጭ ጉዳይና የደህንነት ፖሊሲና ውጭ ጉዳይ የሚጓዝበት መንገድ ለየቅል የሆኑበት አጋጣሚም አያሎህ። በፖሊሲው የተቀመጠ አንደኛው መርህ ሁሉም የዲፕሎማሲ ጦር የሚያነጣጥረው ቅድሚያ ለአገር ውስጥ ጉዳይና ለኢኮኖሚ እንዲሁም ከውጭ ብሔራዊ ጥቅማችን ከማስጠበቅ አንፃር ለጎረቤቶቻችን መሆን አለበት ይላል።ከዚህ አንፃር ፖሊሲው ለመተግበር የስምሪት ማእከላት፣ብቃትና ልምድ ያለው የሰው ኃይል የት መመደብ እንዳለት የሚያመላክት ሲሆን ትግበራው ስናየው የትየ ለልየ ነው።በአንዳንድ አገሮች ያለን ስምሪት በምናይበት ወቅት ለሚሾመው አምባሳደር ታስቦ ብቻ የተወሰነ ይመስላል።

ይህ የመስራቤቱ ችግር በመሀል የተከሰተ ሳይሆን ከመጀመርያው ጀምሮ እያደገ የመጣ ብልሽት አሰራርና አመራር ሲሆን በዚህ ተቋማዊ ሁኔታና አለማቀፋዊ ሁኔታ አገራዊ ጥቅምን እንዴት ማረጋገጥ እንደሚቻል አስቡት።ስለሆነም አዲሱ ሚንስትር የሚችሉ ከሆነ መጀመርያ ራስዎን ከማንኛውም አመለካከትና ችግር ፀድተው ስራዎን ተቋማዊ ለውጥ በማምጣትና ካለንበት አለማዊ ሁኔታ ጋር የሚጣጣም አሰራር መከተልና አመራር መስጠት ግድ የሚላቸው ይመስለኛል።

እንደተለመደው ትንሽ የሚያግዙ ከሆኑ የሚከተሉትን ምክረ ሃሳቦች ልሰንዝር፤

1. እናንተ ኢህአዴጎች ምልአተ ህዝቡ ለለውጥ በተነሳሳበት ወቅት ተሃድሶው እንዴት ገድላቹ እየቀበራችሁት እንደሆነ ከላይ ባየነው መልኩ መረዳት ይቻላል።በኔ እምነት ረፍዷል እንጂ አልጨለመምና አቅጣጫው አስተካክላቹ ወደ መንገድ ለመመለስ ያለው የመጨረሻ አማራጭ ተጠቀሙበት።ከግል ጥቅምና ክብር የህዝብና የአገር ጥቅም ይቀድማል።አንዳንድ ሰው ፈጣሪ የለም ሲል ከርሞ ሲታመም ወይም አደጋ ሲያጋጥመው ፈጣሪ ማረኝ እንደሚል ሁሉ እናንተም ችግር ውስጥ ነን ስትሉ ብቻ የህዝብ ስም አትጥሩ።ህዝቡ ክራይ ሰብሳቢነትና የመልካም አስተዳደር ችግር ነግሷል ሲላቹ ካንተ ጋር ሆነን እንታገለዋለን፣እንዲህ መደረግ አለበት ሲባል ህዝባችን አማክረን እንወስናለን፣ ህዝቡ መብቱ አሳልፎ መስጠት የለበትም፣ ከህዝብ የተሰወረ ነገር የለምና ያለ ህዝብ ተሳትፎ ምንም ነገር ማድረግ አይቻልም የሚሉ ህዝብን የሚሸነግሉ ቃላት መጠቀም ብቻ ለውጥ ስለማያመጣ ተሃድሶም ይባል ሌላ በህዝብና በአገር ተጠቃሚነት የሚለካ ስራ መሰራት ያለበት።

እስካሁን በነበሩ መድረኮች የተገኙ ጥሩ ልምዶች በመጠቀምና የነበሩ ውድቀቶች ገምግማቹ እስካሁን የተካሄደ መድረክ የመጀመርያ የንቅናቄ መፍጠርያ መድረክ እንደሆነ ወስዳቹ ምእራፍ ሁለት ብላቹ ወደ ዋናው የተሃድሶ መድረክ ግቡና አገርና ህዝብ ከፊታቸው ከተደቀነውና በታሪካቸው አይተውት ከማያውቁ ጥፋት አድኑ።ይህ ሁሉ ለናንተ እየቀረበ ያለው ልመና የኢትዮጵያ እጣ ፈንታ በእናንተ ብቻ የሚወሰን ስለሆነ አይደለም ።ያለንበት ተጨባጭ ሁኔታ ለመፍትሄው የቀረበ ከናንተ የተሻለ አማራጭ ከፊታችን ስላጣን ነው።

ከዚህ ጋር ተያይዞ እናንተ ነባር ታጋዮችና አመራሮች ድርጅቶቹን በተለይ ብአዴንን ለጥፋት ኃይል ካስረከባቹ በኃላ ሆነ እንጂ በዚህ ባሳለፍነው መድረክ የተሻለ ትግል ማድረጋቹ ይሰማል።የእናንተ ጥረት እና ትግል እስከዚህ ድረስ ብቻ ነው ሳትሉ ድንበሩ ድርጅቱ ድኖ በሁለት እግሩ እስኪቆም ድረስ መሆኑ አምናቹ ሁሉም አይነት መሳርያ በመጠቀም ድርጅታቹና አገራቹ አድኑ።

2. ከመንግስት ከፍተኛ አመራሩ ጀምሮ በፌደራል መንግስትም ሆነ በክልል መስተዳድሮች ዘንድ በየደረጃው ባሉ የመንግስት አስፈፃሚ አካላት ስለ የኢትዮጵያ ፌደራሊም ባህሪና በሁለቱም መካከል ስላለው ዝምድና በሚመለከት እውቀቱ በጣም አነስተኛ መሆኑ መረዳት ይቻላል።ከዚህ ጋር በተያያዘ ያለው የህገ-መንግስት ድንጋጌ አስመልክቶ ያለው ግንዛቤም እንዲሁ ዝቅተኛ ይመስለኛል።በርግጥ ከፍተኛ አመራሩ በህገ- መንግስቱ ስለ ፌዴራሊም የተደነገገው ብቻ ሳይሆን ስለ ሌሎች የህገ-መንግስት ድንጋጌም ቢሆን ቃሉ ደጋግሞ በስብሰባ ከመጠቀም በዘለለ ያለው እውቀት ትንሽ እንደሆነ መናገሬ በድፍረት አይቆጠርብኝ።ከክልል ክልልና ክልሎች ከፌደራል መንግስት ጋር የሚታዩ አለመግባባቶችና ውዝግብ መነሻቸው ይህንን ችግር ይመስለኛል።የክልል መስተዳድሮች ራስክን በማስተዳደርና ነፃ አገር በመሆን ያለው ልዩነት በውል የተገነዘቡት አይመስሉም።ሚድያዎችም ከዚህ የተለየ ሁኔታ ውስጥ አይደሉም።በቅርቡ በፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ተዘጋጅቶ በነበረ የፌደራሊዝም ግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ አስመልክቶ በ4/6/2009ዓ/ም ጧት በአባይ ኤፍ ኤም ዜና ላይ የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር “በመንግስታቱ መካከል ያለው ግንኙነት የግንዛቤ ጉድለት እንዳለበት ተገለፀ” ብሎ በአርእስተ ዜና ሲገልፅ የትኞቹ መንግስታት እንደሆኑ እያሰብኩ ወደ ዝርዝር ሲገባ የክልልና የፌደራል መንግስታት መሆናቸው ገለፀ።ማታ በEBC ዜና ሚኒስትሩ ሲናገሩም ተመሳሳይ ነገር ገለፁ። በኔ እምነት የክልል መንግስታት እየተባሉ ያሉትን የክልል መስተዳድሮች የክልል ፕሬዝዳንት እየተባሉ ያሉ የክልል ርእሳነ መስተዳድር በሚል መተካት ያለበት ይመስለኛል።ይህ ስማቸውና አጠራሩ በስነ-ልቦና የራሱ አሉታዊ ሚና አለው። ከዚህ በፊት እንዳወራነው ስለ አገራዊ አንድነት የተሰራው ጥቂት እንደሆነና በየክልሉ ያሉ በብሔር ስም የህዝብ ስጋ እየተመገቡ መኖር የጀመሩ የፖለቲካ ጭልፊቶች በየክልሉ ያለው ህዝብ እንደ ርስትና የግል ንብረት ለመጠቀም በመፈለግ በጠባብ ብሔርተኝነት ስሜት እያነሳሱ ከእጃቸው እንዳይወጣ ልማት ማምጣት ሳይሆን ነጋ ጠባ “ባለፈው ስርአት እንደ ሰው ያልተቆጠርከው በአማራው አሁን ያለብህ ችግር ምንጩ ትግሬው” የሚል ቅስቀሳ ነው። በመሆኑም በሁሉም ስብሰባም ይሁን የሚድያ ስራ ይህንን አገራዊ አንድነት የሚያጠናክር እንዲሆን ማድረግ ያስፈልጋል።

ሌላው ጉዳይ በየክልሉ ያሉ የተዛቡ አመለካከቶችና ተግባሮች ማስፈፀምያ እየሆኑ ያሉ በልዩ ኃይል ስም የተደራጁ ኃይሎች በየትኛው የህገ-መንግስት አንቀፅ እንደተቋቋሙ ግልፅ ባይሆንም ለኃይሉ የተሰጠው ግዳጅ ከፌደራል ፖሊስ የተለየ ሆኖ አላየውም።በመሆኑም በየክልሉ ያለው በመበተን ወደ ፌዴራል ፖሊስ እንዲቀላቀል መደረግ አለበት።

ከዚህ ጋር ተያይዞ የፌደራል መንግስትም ቢሆን ጥምር አይሉት ጥርቅም መንግስት ተዋፅኦ ለማመጣጠን በሚል ሲሰቃይ እያየን ነው።ሚዛናዊ ተዋፅኦ እንደተጠበቀ ሆኖ በዚህ ስም ምንም አቅሙ የሌላቸው

በማሰባሰብ መንግስት ገነባን ብትሉ ትርፉ የአገር ህልውና ላይ መደራደር ነውና መጀመርያ ብቃት እንዲኖራቸው አግዙዋቸው።

 

ከላይ ለመጠቃቀስ እንደሞከርኩት ተሃድሶው በገዢ ፓርቲው ብቻ የታጠረ እንዳይሆን መስራት ያስፈልጋል። በፌዴራል ተቋማት እየተደረገ ያለው ተሃድሶ የተሰየመ ስብሰባ የቀልድም ቀልድ እንደነበር በተለያዩ ተቋማት የሚሰሩ ጓደኞቼ ነግረውኛል። አንዳንዱ መስራቤት ያሉና የሌሉ ችግሮች በመዘክዘክ ብቻ ከሁሉ መስራቤት የጠለቀ ተሃድሶ እንዳደረጉ የሚያስቡ ናቸው። የተወሰኑ መስራቤቶች መንግስት የሚመራው መሆኑና አለቃ እንዳለው ሁሉ የሚያጠራጥር ሁኔታ እንታዘባለን። አንድ ገበሬ በማሳው የነበረ ክምር በመጫን ወደ አውድማ ከበተነውና ክብቶች አስገብቶ ማስኬድ ከጀመረ በኃላ በመሃል አቋርጦ አመታዊ ጥረቱ ለበላተኛ በትኖ ወደ ቤቱ እንደመመለስ አይነት ነው ያለው።አንዳንዱ ተሃድሶ የሚባል ነገር ለኔም ይመለከታል የሚል አስተሳሰብ የሌለው አለ።በአንዳንድ መስራቤት ያሉ ኃላፊዎች ዋናው ችግር የአመራር ችግር ሆኖ እያለ “እኔ ሌላ ቦታ ስለተገመገምኩ ስለኔ ምንም ነገር እንዳታነሱ የራሳቹ ችግር ብቻ

ማየት ነው የናንተ ኃላፊነት” በሚል ተሃድሶውን ወገቡ ቁርጥ ያደረጉ የፓርቲ መሪዎችና የተቋም ኃላፊዎች ብዙ ናቸው።ስለሆነም መንግስት ማለት አራት ኪሎ ያለው ብቻ ሆኖ እንዳይቀርና አብዛኛው አካሉ ያለ የሚመስል በድን እንዳይሆን በተለየ ትኩረትና ክትትል መመራት ያለበት ይመስለኛል።
ባለፈው እንደጠቀስነው ከሁሉም በላይ በትኩረት መሰራት ያለበት የፀጥታ አካላትና ላይ መሆን እንደሚገባው ብዙ መገለፅ የሚቻሉ ምሳሌዎች አሉ።በመከላከያ፣በፌደራል ፖሊስ፣በየክልሉ ያለ ፖሊስና ልዩ ኃይል በተለየ ሁኔታ የተለየ ክትትል ተደርጎ የተሃድሶና የማጥራት ስራ ካልተሰራ አገር መበተኛ አቋራጭ መንገድ ይሆናል።በተወሰነ ደረጃ እንደሰማሁት ደግሞ አንዳንድ የሰራዊቱ አባላት በብሔራቸው ስም ከተደራጁ ፀረ-ሰላምና አሸባሪ ኃይሎች ጋር የመተሳሰር ሁኔታ ከመኖሩ በተጨማሪ ህዝብንና አገርን ለገበያ በማቅረብም ጭምር ጭፍን የሆነና በቃኝ የሌለው የጥቅም አሳዳጅነት አለ።እነዚህ የአመለካከት ችግሮች አሁን ካለንበት አሳሳቢ አገራዊ ሁኔታ ጋር ሲዳመር ጉዳዩ ከባድ ያደርገዋልና ይታሰብብት።

እኔ ብዙ የማይገባኝና የሚገርመኝ ነገር በዚህ አገር ወታደራዊ ፍርድ ቤት አለ ወይ የሚል ሲሆን የአገር ክህደት የፈፀሙ የወታደራዊ ክፍሉ አባላት በራሱ ፍርድቤት ሲቀጣ አልሰማሁም ።እንዲህ ጥርጣሬ ውስጥ ያስገባኝ ደግሞ ሌላ እውቀት ባይኖረኝም በጎንደር ጎረቤታችን የነበሩ ሁለት ሰዎችና የታናሽ ወንድሜ ጓደኛ የነበረ ሰው በመከላከያ እንደነበሩና ከመከላከያ ከድተው ከነ ሙሉ ትጥቃቸውና አንዱ ደግሞ የመገናኛ ሬድዮም ጭምር በመያዝ ወደ ጠላት አገር ኤርትራ በመክዳት የመከላከያ ሚስጥር ለጠላት አሳልፈው ሰጡ የተባሉ ሰዎች ሁሉም ምህረት ጠይቀው ወደ አገራቸው ተመለሱ ተብለው ታፍኖ ወይም ተታሎ ኤርትራ ከሄደውና ምህረት ብሎ ከመጣው ስቪል ጋር በእኩል ተቀብሎ ወደ ቤት መሸኘት ስላየሁ ነው።

 

ሌላው በአገሪቱ ያሉ የፋይናንስ ተቋማት በተለይ በባንኮች ከባንኮችም በተለይ የመንግስት ባንኮች ያለው የአጥፊነት እንቅስቃሴ በመገደብ ለልማትና ለአገራዊ ህዳሴ የሚያግዙ እንዲሆኑ በትኩረት መታደስ ያስፈልጋቸዋል። መንግስት ድህነቱ እየነገረን ከድሃው ህብረተሰብ ሳይቀር አምስት ብር እየተቀበለ አባይ ለመገደብ ሲንቀሳቀስ እነዚህ ተቋማት በአደራ የያዙትን የህዝብ ገንዘብ በኢንቨስትመንትና ኮንስትራክሽን ብድር ስም ለአንድ ሰው ሰላሳና አርባ ሚልዮን ብር በመስጠት በፐርሰንት የሚታሰብ ክፍያ ለባንክ ማናጀሮችና ደላሎች በማከፋፈል ላይ ናቸው።በጋምቤላ፣ቤንሻንጉልና ሶማሌ ክልል በመሬት ኢንቨስትመንት ስም የተጠቀሰው ሚልዮን ብር ከወሰዱ ሰዎች አንዳንዶቹ ከዚህ ብር በፊት ሃያ ሺ ብር እንኳ ቆጥረው የማያውቁና ገንዘቡ ለማስተዳደር ይቅርና ካልደጋገሙት በቀር ለመቁጠር እንኳን የሚቸገሩ እንደሆኑ ደጋግመን አድምጠናል።ገንዘቡ ለማስተዳደር እንዲቀላቸው ለእርሻ ኢንቨስትመንት ብለው ያወጡት ብር ከአንድ በላይ የቤት መኪና፣የመስክ መኪናና የጭነት መኪኖች እንዲሁም ቤት በመግዛት ጫናቸው ቀለል ለማድረግ የሞከሩ በርካታ መሆናቸውም ሰምተናል።ሰላሳና አርባ ሚልዮን ብር በሁሉም ክልል ባለው ኢንቨስተር ቁጥር አባዙና ምን ያህል ቢልዮን የህዝብና የአገር ብር እንደ ጠፋ ንገሩኝ ካልኳቹ ሒሳብ የሚችል ባንክ ነው ስለምትሉኝ ትቸዋለሁ።

በዚህ የሚያበቃ እንዳይመስላቹ።ከውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ትሩፋት ከሆኑት ቴክኖሎጂ፣እውቀትና ገንዘብ ይዘውልን መጥተው ስራ አጥነት በመቀነስም ትልቅ ፋይዳ ስላላቸው በሚል በብዙ ቅስቀሳ ወደ አገር የመጡ ኢንቨስተሮችም የዚህ ፀበል ተቋዳሽ ሆነው ትንሽ ይዘው ገብተው ከባንኮች ጋር ተመሳጥረው ብዙ ገንዘብ ተበድረው ይዘው መሬቷን ጥለውልን እብስ ያሉም ቁጥራቸው ቀላል አይደሉም ተብሏል። ከዚህ ጋር ተያይዞ ከነሱ ጎን ለጎን የሚንቀሳቀሱ የኢንሹራንስ ኩባንያዎችም በጉዳት ካሳ ክፍያ ስም በተመሳሳይ የኮሚሽን ስራ ምክንያት ቢልዮኖች እየጠፋ ነው።ስለሆነም በነዚህ ተቋማት ይህንን አስቁሞ አዲስ አመለካከት፣አዲስ አሰራርና ለውጥ የሚፈጥር ተሃድሶ ካልገባ ተሃድሶው በምን ሊለካ ይችላል? እርግጥ ነው ኢንቨስትመንት ኢንዲስፋፋ ብድር ያስፈልጋል።እርግጥ ነው የተወሰኑ ሰዎች የተሰጣቸው ገንዘብ በሚገባ የተጠቀሙ መኖራቸው አይካድም ።

5. ሌላው የአገራዊ ተሃድሶ ትኩረት መሆን ያለበት የብረታብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን ነው። ከአንዳንድ አገር ልምዶች በመነሳት የትራንስፎርሜሽኑ ጉዛችን እንዲመራና እንዲያስቀጥል፣የኢንዱስትሪና የቴክኖሎጂ ሽግግር ማእከል እንዲሆን፣የሰው ኃይላችን የእውቀት ምንጭ እንዲሆን በአጠቃላይ የአገሪቱ ራእይ መሳካት ቁልፍ መሳርያ ሆኖ እንድያገለግል ታስቦ መቋቋሙ ትልቅ ሃሳብ ባለ ትልቅ ራእይ መንግስት ያሰኘዋል።ወደ አፈፃፀሙ ስንገባ በመጀመርያዎቹ አከባቢ ተስፋ ሰጪ ሁኔታዎች መታየታቸው እሙን ሆኖ ሳለ ከተቋሙ ራእይና ተልእኮ ጋር የሚሄዱም የማይሄዱም እያከናወናቸው ተግባሮች ይነስም ይብዛም ጠቃሚ መሆናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ በተቋሙ ያለው ችግር ግን ከኢህአዴግ ከራሱ ያልተናነሰ ትልቅ የተሃድሶ አብዮት የሚያስፈልገው ነው።ከመጀመርያዎቹ ፅሁፎቼ በአንዱ ጠቆም ለማድረግ እንደሞከርኩት በየትኛውም የመንግስት ተቋም አለ ተብሎ ከሚታሰበው የሙስና ችግር በላይ እዚህ ቤት አለ። የተደራጀና ጥቂቶችን ብቻ ሳይሆን ከተቋሙ ዋና መሪ ጀምሮ በየደረጃው ያለ አብዛኛው አመራር የሚያሳትፍ ሙስና እዚህ ቤት አለ። በአንዳንድ የተቋሙ ጉብኝትና በመከላከያ በአል በኢግዝብሽን መልክ ከሚቀርቡ እቃዎች መካከል ጥቂቶቹ ራሳቸው ያልሰሯቸው መሆኑ ኢህአዴግ አልሰማም ማለት አልችልም።እንደ ትራስፎርመርና ሌሎች እቃዎች ከሌላ ገዝተው የራሳቸው አስመስለው ስለማቅረባቸውም ይሰማል ።ከሁሉም በላይ አስጨናቂው ነገር በምርት ጥራት ይታያል ስለሚባለው ጉዳይ ሲሆን በብሸፍቱ ባስ እንኳን እኛም አይተነዋል።በህዳሴው ግድብ በያዙት ስራ ይህንን እንደማይታይና ታሪካዊና በትውልድ ሁሉ ይቅር የማይባል ጥፋት እንደማያጠፉ ተስፋ አደርጋለሁ።ይህ ሁሉ የምለው ዜና ለመንገር ሳይሆን በዚህ ተቋም በዚህ ልክ ከጥልቅም ሌላ ጥልቅ ተሃድሶ ስለሚያስፈልገውና መንግስት በተለየ ሁኔታ አይቶ ስር ነቀል ለውጥ እንዲያመጣ ዛሬ መስራት ያስፈልጋል የሚል የዜግነት ሃሳቤ ለማካፈል ነው።

 

ኢህአዴግም ሆነ እሱ የሚመራው መንግስት የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ የፈጠረው ምቹ ሁኔታ በአግባቡ ሲጠቀሙበትና ለአዋጁ ምክንያት ለሆኑ ችግሮች ግዜ የለኝም በሚል በዛው ልክ በዛው ፍጥነት ለመፍታት አልተንቀሳቀሰም። በመሆኑም አዋጁ ለማንሳት ሲታሰብ የነበሩ ችግሮች እንደነበሩ ያሉባቸው አከባቢዎች እንደ ሰሜን ጎንደርና ሌሎች ካሉ ተፈትሸው በተወሰኑ አከባቢዎች አዋጁ እንዲቀጥል ቢደረግ።

 

ህዝቡ በተለይ ወጣቱ ያገኘውን በማጣጣም ያጣውን በህጋዊ መንገድ በመጠየቅ ላይ የተመሰረተ ትግል ማድረግ ይገባዋል።ኢህአዴግ ያጎደለው እንዳለና ከባህሪው አንፃር ብቻ ሳይሆን ከራሳችን መሰረታዊ ጥቅሞቻችን አንፃር ያጠፋው ቀላል አለመሆኑ መተማመን እንችላለን።ይሁን እንጂ የኢህአዴግ ችግሮች በድፍረት ለመናገር እንደቻልኩት በጣም በድፍረት መናገር የሚቻለው ኢህአዴግ ኢትዮጵያን ወደ አዲስ ምእራፍ ወደ ከፍታ ማሸጋገር መቻሉ ነው።እንዲህ ነው እንዲያ ነው በሚል መልኩ ለመዘርዘር አልፈልግም። ሁሉም ሰው ባያጣጥመውም የሚያየው በመሆኑ ነው። በዚህ አገር ያለ መልካም ለውጥ መናገር ራሱ የብሔር ጥያቄ የሚያስነሳ በመሆኑ ብዙ ሰው ብዙ ማውራት አይችልም ።አንዳንዴ እንደምታዘበው ደግሞ በባህሪ የራሳችን ትተን የውጭ ናፋቂና አድናቂ መሆናችን በተለያየ ግዜ ከተለያየ መገለጫ ጋር ሲቀርብ ቢቆይም የኔ አንድ ትእዝብት ደግሞ በመኪኖች ስለሚለጠፉ ምስሎች ነው።በታክሲ፣በቤት መኪና፣በንግድ መኪኖችና በአስጎብኚ ድርጅት መኪኖች ላይ በብዛት የተለጠፉ የግለሰብ ምስሎች በመለጠፍ አድናቆታችንና ፍቅራችን ስንገልፅ አያሎህ።ብዙ ግዜ የምናያቸው ምስሎች በብዛት የሮናልዶ፣ የሜሲ፣ የቸጎቤራ፣የቦብ ማርሊ ሲሆኑ ቀጥለው የአፄ ቴድሮስ፣የአፄ ሚኒሊክ፣ የአፄ ኃይለስላሴ፣ የቴዲ አፍሮ፣ የመሳሰሉ እናያለን ከአፄዎቹ አጥፍተዋል ተብለው የሚወቀሱበት ቢኖርም አገራቸውን ሲመሩ በአንድ ወይም በሌላ መለኩ የሰሩት በጎ ነገር ስላለ ማድነቃችን ትክክል ነው።ግን ለአገርና ለህዝብ ልእልና ዘብ በመቆም ከሆነ፣የአገር ክብር ከፍ እንዲል በማድረግ ከሆነ፣አገርን ከባእዳዊ ወረራ መከላከል ከሆነ ከብዙ ሰው በፊት የድንቅ ባለ ታሪክ አብዲሳ አጋ፣ የኢትዮ ሶማሌው ደጃዝማች ዑመር ሰመተርና ሌሎች ውለታቸው የበዛ ኢትዮጵያውያን ጀግኖች ምስል በብዛት ባየን ነበር።በአፄነት ከሆነ ደግሞ ከአንዳንዶቹ ባልተናነሰ የአፄ ዮሀንስ ምስል ባየን ነበር።ለምን ቢባል ከትንሽ ሙከራ በኃላ ጣልያን መጣ ብሎ ህዝብና አገር ጥሎ የሸሸ ንጉስና ዱርቡሽ መጣ ብሎ በውግያ መሃል ገብቶ ደረቱን ለጥይት አንገቱን ለሴፍ የሰጠ ንጉስ እኩል አይሆኑምና ነው። ከላይ በተገለፁ ጠላትን ከወረራ፣ከድህነት፣ከፍፁም ፀረ ዴሞክራሲያዊ ስርአት በማላቀቅ አገርን ወደ ብልፅግና በማሸጋገር

መስፈርቶች ቢሆን ደግሞ በአብዛኛው መኪና የመለስ ምስል ተለጥፎ እናይ ነበር። ከዚህ ሁሉ የሚገርመው ግን በአንድ የታርጋ ቁጥር ኮድ 2 አ.አ 6844- በሆነና በተለምዶ “ወያነ” እየተባለ የሚጠራ መኪና የአፄ ኃስላሴና የመንግስቱ ኃማርያም ምስል ከኃላ ለጥፎ ሲዞር ያየሁት መኪና ነው።እኔ እኮ መንግስቱ ሰው በላና አገር ያጠፋ እንደሆነ የምንግባባ ይመስለኝ ነበር።አገርን ለጥፋት፣ ለኢኮኖሚያዊ ድቀት፣ ለድንቁርና፣ ለአስከፊ ድህነትና እርዛት ያበቃን ሰው፣የሰው ደም እንደ ቄራ ያፈሰሰን ሰው አደንቃሎህ ብሎ ምስሉ በመኪና ለጥፎ መዞር በምክንያት ሊጠቀስ ይችላል ብየ ባስብ ባስብ ሊቀራረብ የሚችል ምክንያት አጣሁና ወዴት እየሄድን እንደሆነ ጠቋሚ ነገር እንደሆነ ወሰድኩ።

ህዝቡ በተለይ ወጣቱ ትውልድ ያጣውን ፍለጋ ሲወጣ ብዙ የአፍሪካ ህዝቦች ብያገኙት እንደ መንግስተ ሰማይ የሚመኙት በእጁ ያለው ጥሩ ነገር በመርገጥና አሻግረን የምናየው የህልም ዳመና ለመቧጠጥ በመሞከር አይደለም ለውጥ መፈለግ ያለብን።በአብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮች ዴሞክራሲ የሚባል የለም።በኛ ብያንስ የተሻሉ ጅምሮች አለን።በብዙ አገሮች መሰረታዊ ሰላም የለም።እኛ ጋ በቅርብ ግዜ ከየበረው ችግር ውጭ በሰላም በኩል እፎይታ አለን።በበርካታ አገሮች የተረጋጋ መንግስት ሳይኖር ረሀብ ተንሰራፍቷል።እኛ ዘንድ በታሪካችን አይተነው የማናውቅ ድርቅ ገጥሞንም ቢሆን ሰው ሳይሞት ተቋቁመን መውጣት የቻልንበት ሁኔታ ነበር።ለምን? በሌላ አገር የስራ አጥ ቁጥር ከግዜ ወደ ግዜ በእጥፍ እየጨመረ ይገኛል።በአገራችን ስራ አጡ ብዙ ቢሆንም በጣም በርካታ የስራ እድል እየተፈጠሩ ያሉበት ሁኔታ አለ።በአገራችን ለብዙ ተደራሽ እየሆነ ያለ እድገት አለ።በብዙ አገሮች ግን ስለ ልማት ማውራት ስለ ጌጥ ወይም ትርፍ ነገር አድርገው ያስባሉ።ምክንያቱም በነሱ ዘንድ ተርበህም በሰላም የምትተኛበት አገር አጥቷልና ነው።እኛ አጎደልክብን ብለን የምንጠይቀው መንግስት አለን።ባለፈው በስፋት እንዳልነው በብዙ አገሮች የዚህ አገር ባለቤት እገሌ ነው ማለት የማይቻልበት ሁኔታእየተፈጠረ ያለ መሆኑ ነው።ስለ መንግስት አልባዎቹ አገሮች እንተውና መንግስት አላት የምትባል የሶርያ ጉዳይ እንኳን ብንመለከት የአገሪቱ እጣ ፋንታ የሚወስኑ ሌሎች ሆነው አይተናል።በቅርብ ወራት በሶርያ የሞስሊሞች የአረፋ በአል ለማክበር የተኩስ አቁም ስምምነት ያደረጉ የሶርያ መንግስትና አማፅያን ሳይሆኑ የሩስያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭና የአሜሪካው አቻቸው ጆን ኬሪ ነበሩ።

በቅርቡ በአንድ ጋዜጣ ላይ ያነበብኩት ስሜቴን ስለያዘው ለዚህ አስረጂ አድርጌ ላቅርበው። አንድ የሶማልያ ስደተኛ ያለው ነው።’’ከሁሉም በላይ ክብር አገር ስትኖርህ እንደሆነ ያወቅኩት አገሬ ያጣሁ ቀን ነው።በቁሙ እያለ የሌለ ተብሎ የሚጠራ ሰው አገር የሌለው ሰው መሆኑ ሁኜ አይቸዋሎህ’’ ይላል።ሌላው ብ/ጀነራል ለማ ገ/ማርያም የተባሉ አባት አርበኛ የጣልያን ወረራ ለመመከት ከአዲስ አበባ ተነስተው ለመዝመት ጉዞ ለመጀመር እግራቸው ማንሳት በጀመሩ ግዜ መልእክተኛ መጥቶ “ወንድምህ ስለሞተ ተመለስ ቅበረው” ሲሏቸው “ወንድሜ ከሞተ ቅበሩት እኔ አገሬ ከሞተች ቀባሪ ስለማይኖራት እንዳትሞት ተሎ መድረስ አለብኝ” ብለው ወደ ዘመቻው መሄዳቸው ከፅሁፍ በተጨማሪ በቅርቡ በEBC ተጠይቀው

ራሳቸው ሲናገሩ ሰምተናል።ስለሆነም የጎደለን ስንጠይቅ ያለን ሳንረሳና የአገር ህልውና ጥያቄ ውስጥ በማያስገባ ሁኔታ መሆን ይገበዋል።
ይህች አገር ወልዳ፣አስተምራ፣ለቁምነገር አብቅታ እዚህ ከደረሳቹ በኃላ ተመልሳቹ ለዝያውም ከደመኛ ጠላቶቿ ጋር አብራቹ ቁልቁል እንድትደፋ እየሰራቹ ለምትገኙ የጥፋት መልእክተኞች ሆይ ዛሬ ሁለቴ አስቡ።ስለ አገር መኖር ስለ አገር መሞት ምን ማለት እንደሆነ ግራ ከገባቹ ለሪቻርድ ፓንክረስትና ቤተሰቦቻቸው ጠይቁ።

ውድ አንባብያን ሆይ ይህንን የመሰለ ረጅም ፅሁፍ ለማንበብ በመፍቀዳቹ በእጅጉ አመሰግናለሁ።አለን ለምትሉት ማንኛውም ሃሳብ በተለመደው አድራሻየ እንገናኝ።ለማስታወስ ያክል፤

E-mail…… agerawiguday@gmail.com ወይም

Facebook selamwerq huluager ብላቹ ፃፉልኝ።

ሰላምወርቅ ሁላገር ነኝ ከአዲስ አበባ

Leave A Reply

Your email address will not be published.