ኢህአዴግና ተፎካካሪ ፓርቲዎች የመግባቢያ ሰነድ አቀረቡ

 

 

ከገዢው ፓርቲ ጋር ውይይትና ድርድር እናካሂዳለን ያሉ ሀገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች የመግባቢያ ሰነድ ለተወካዮች ምክር ቤት እያስገቡ ነው፡፡

የድርድሩ ተሳታፊ ለመሆን ህብረት የፈጠሩት 11 የፖለቲካ ፓርቲዎች የመግባቢያ ሰነዱን ይዘት የተመለከተና በጋራ ለመስራት የደረሱበትን ስምምነት ይፋ አድርገዋል፡፡

ከ2008 ዓ.ም አጋማሽ ወዲህ በሀገሪቱ የተፈጠረው የፖለቲካዊ ግርግር ይዟቸው ከመጣቸው ጉዳዮች አንዱ ኢህአዴግ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ውይይት አደርጋሁ የሚለው ይጠቀሳል፡፡ ገዢው ፓርቲ ከሀገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ለመወያየትና ለመደራደር ተዘጋጅቻለሁ ማለቱን ተከትሎም 21 የሀገር ውስጥ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ፍቃኝነታቸውን መግለፃቸው ይታወሳል፡፡ እነዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከግዢው ፓርቲ ጋር ጠንከር ባለ መልኩ ለመወያየትና ለመደራደር ህብረት እየፈጠርን ነው ሲሉ እየተደመጡ ናቸው፡፡

እስካሁን ባለው አሰላለፍም ፓርቲዎቹ በሶስት ጎራ ተሰባስበዋል፡፡ የመጀመሪያው ህብረት 11 ፓርቲዎችን ያጣመረው ስብስብ ሲሆን፡፡ ሁለተኛው ደግሞ 6 ፓርቲዎችን ያቀፈው ቡድን ነው፡፡ የተቀሩት አራት የፖለቲካ ፓርቲ ድርጅቶች በተናጠል ለመወያየትና ለመደራደር የተዘጋጁ ናቸው፡፡ የ11 ፓርቲዎችን ስብስብ የያዘው የፖለቲካ ቡድን በጋራ ተሟሙቶ ያዘጋጀውን የመግባቢያ ሰነድ ለተወካዮች ምክር ቤት እንዳስገባ ገልጿል፡፡

ውይይቱና ድርድሩ ከገዢው ፓርቲ ጋር ከመካሄዱ በፊት ለተወካዮች ምክር ቤት የገባው የመግባቢያ ሰነድ 4 ነጥቦችን የያዘ መሆኑን የፓርቲዎቹ ስብስብ አስታውቋል፡፡ የመጀመሪያው ነጥብም ስነ-ሥርዓትን የሚመለከት ሲሆን፤ ክርክርሩን ውይይቱንና ድርድሩን በሚመለከት የተያዘውን ነጥብ የ11ዱን ፓርቲዎች ሰብሳቢና የአንድነት ፓርቲ ሊቀመንበር ትዕግስቱ አወሉ፣ ለኢ ኤን ኤን ገልፀዋል፡፡

የ11ዱን የፖለቲካ ፓርቲዎች ስብስብ የሚመሩት አቶ ትዕግስቱ አሁን የተፈጠረው አጋጣሚ ጥሩ መሆኑን አንስተው ከመንግስት ጋር የሚደረገው ውይይትና ድርድር የሰለጠነ እንዲሆን ተስፋ አድርገዋል፡፡

የ11ዱ ፓርቲዎች ስብስብ ከኢህአዴግ ጋር ውይይት ስለሚያደርግባቸው ጉዳዮች ዝርዝር ሀሳብ ለመስጠት ፍቃደኛ አልሆነም፡፡ ይሁን እንጂ በመግለጫው ወቅት አንዳንድ ፍንጮች ተስተውለዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል ፓርቲዎቹ አሳሪ ህጎች በሚሏቸውና አንዳንድ የህገ-መንግስት አንቀጾች ላይ እንደሚወያዩ ተመላክቷል፡፡

ሁሉም ውይይቶችና ድርድሮች ለመገናኛ ብዙን ክፍት ይሆናሉ የሚል ሀሳብ ይዘናል ቢሉም የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ተፈፃሚነቱ ላይ ግን ስጋት አላቸው፡፡ ከመንግስት ጋር የሚደረገው ውይይትና ድርድር የህዝቡ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የሆኑ ፖለቲካዊ ችግሮች መፍትሔ እስካላገኙ ድረስ ትግላችን አይቆምም ያሉት አቶ ትዕግስቱ ለዚህ ጉዳይ ህብረተሰቡ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል፡፡

ምንም እንኳን በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ፓርቲዎች የመተቻቸትና መፈራረጅ ልማድ ቢኖራቸውም በዚህ አጋጣሚ ግን ከኢህአዴግ ጋር ለሚያደርጉት ውይይትና ድርድር ልዩነታቸውን ወደ ጎን ትተው የጋራ በሚያደርጋቸው ሀገራዊ ጉዳይ ላይ ተስማምተው እንደሚቀጥሉ የ11ዱ ፓርቲዎች ስብስብ አስታውቋል፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.