ኢህአዴግ ሰላማዊ ትግልን ምርጫቸው ካደረጉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ለመደራደር ዝግጁ ነው-ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ

(ኢዜአ)-  የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር  ሰላማዊ ትግልን ምርጫቸው ካደረጉ ማናቸውም ዓይነት የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ለመደራደር ዝግጁ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አስታወቁ።

አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትርና የግንባሩ ሊቀ መንበር ዶክተር አብይ ከኃይማኖት አባቶች፣ አገር ሽማግሌዎች፣ የተለያዩ ተፎካካሪ ፓርቲ አመራር አባላትና ከሲቪክ ማህበራት ለተውጣጡ ግለሰቦች ዛሬ በብሄራዊ ቤተ መንግስት የእራት ግብዣ አድርገዋል።

በቅርቡ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጠቅላይ ሚኒስትርነት የተሰየሙት ዶክተር አብይ፣ በሱማሌ ክልል በጅግጅጋ ከተማ ተገኝተው በኦሮሚያና ሱማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በተከሰተ ግጭት የተፈጠረውን የሰላም መናጋት በእርቅ እንዲፈታና ሰላም እንዲሰፍን ጥሪ አድርጋዋል።

በትናንትናው ዕለትም በኦሮሚያ ክልል አምቦ ከተማ በመገኘት ከአካቢው ነዋሪዎችና የአገር ሽማግሌዎች ጋር በመወያየት “ለተሻለ ስኬትና አገራዊ ለውጥ መተባበርና በጋራ መስራት” አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።

ዛሬ በብሄራዊ ቤተመንግስት በመገኘት ውይይት ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ካለጠንካራ ተፎካካሪ ፓርቲ ተሳትፎ የዴሞክራሲ ግንባታ የትም አይደርስም” ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ተፎካካሪ ፓርቲዎች እንዲጠናከሩ የበኩሉን ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።

ሰላማዊ የትግል ስልት የስልጣኔና የዘመናዊነት መገለጫ መሆኑን ጠቁመው፤ ኢህአዴግ  ሰላማዊ ትግልን ምርጫቸው ካደረጉ ማናቸውም የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ለመደራደር ዝግጁ መሆኑንም ገልጸዋል።

በቀጣይም ኢትዮጵያ ካጋጠማት ችግር በማመር የተሻለችና የበለጸገች አገር ለመገንባት ሁሉም ዜጋ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሲቪክ ማህበራትና ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች እስከ አሁን ድረስ ለአገሪቷ ለአበረከቱት አስተዋጸኦም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምስጋና አቅርበዋል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.