ኢህአዴግ የብኩርና ክብሩን በተራ የምስር ወጥ ለወጠ!

(www.EthiopiaFirst.com) – ኢህአዴግ ይህቺን ሃገር የመምራት የሞራል ስብዕና የለውም::

የኢህአዴግ የስራ አስፈፃሚ ትላንትና በአንድ ቀን ስብሰባው ለዘመናት ሲያወራላቸው የነበሩት መርሆቹን በሙሉ ትቶ አዲስ መስመር መቀየሱን አውጇል::

ከኢትዮጵያ አየር መንገድ እስከ መብራት ሀይልና ቴሌ ለመቸብቸብ ውሳኔውን አሳውቋል:: በዚህ ብቻ ሳያቆም ታሪክ በቀጣይ በክህደት ሲዘክረው የሚኖረውን ግዙፍ ግፍም ፈፅሟል … ባድመን ለሻዕቢያ አስተላልፎ ለመስጠት!! 

ያኔ ባድመ ላይ የተሰዉትና ዛሬ ላይ ደማቸው ደመ-ከልብ እንዲሆን የተፈረደባቸው ውድ የሀገራችን ልጆችን በዚህ ወቅት በተሰበረ ልብ ሆነን ልንዘክራቸው ይገባናል:: የዛሬ 18 ዓመት ወረራን በመቀልበስ ባድመ ላይ የኢትዮጵያን ሰንደቅ-አላማ በድጋሚ ለማውለብለብ መሪር የሆነ መስዋዕትነት ተከፍሏል:: ወጣቶች ፈንጂ ላይ በመረማመድ ሳይቀር ተሰውተዋል … በሀገሪቷ ከጫፍ እስከ ጫፍ እናቶች ነጠላ አዘቅዝቀዋል … ጥቁር ለብሰዋል:: 

ግና ምን ያደርጋል … በትላንትናው እለት የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ በተመቻቸ ሶፋ ላይ ተቀምጦ ባድመ ላይ በደምና በህይወት መስዋዕትነት የተገኘውን ድል አራክሶታል:: ክህደት ፈፅሟል! በመፅሀፍ ቅዱስ ውስጥ የምናውቀው ኤሳው በኩርነቱን አቃሎ በምስር ወጥ እንደለወጠ ሁሉ ኢህአዴግም አሜሪካንና ሻዕቢያን ለማስደሰት ሲል ያንን የደም መሬት ለአልባሌ ነገር እየለወጠው ነው:: ዛሬላይ ኢህአዴጎች የዘነጉት እውነታ ወዲ አፎም እንደሆነ አይደለም ባድመን ይቅርና አክሱምንና አዲግራትን በወርቅ ሳህን ብታቀርቡለትም አይረካም:: ከመነሻው ጥያቄያቸው “ኤርትራ የግላችን … ኢትዮጵያ ደግሞ የጋራችን!” የሚል ስለሆነ::

በየትኛውም አመንክዮ ኢህአዴግ ሀገሪቷን በዚህ መልኩ መምራት መቀጠል የለበትም:: ድርጅቱ የአቋም ለውጥ ሆነ ባሻው አቅጣጫ መንሸራተት መብቱ ነው:: ነገር ግን ትላንትና ለሀገር ሉዓላዊነት ሲባል ልጆቹን ወደ እነ ባድመ መርቆ ሲልክ የነበረ ኩሩው የኢትዮጵያ ህዝብም በተራው የሚናገርበት እድል ሊሰጠው ይገባዋል:: ህዝብ ድምፁን ማሰማት የሚችለው በምርጫ ሂደት ስለሆነ አስቸኳይ ሀገራዊ ምርጫ ይካሄድ … ህዝብ ይናገር!

አደራ የምንለው ከባድመ ላይ የኢትዮጵያ ሰንደቅአላማ ተነቅሎ በሻዕቢያ ባንዲራ የሚተካበትን ቀን በይፋ ይነገረን … ይህ የክህደት ድርጊት በድቅድቅ ጨለማ እንዳታደርጉት!! ያቺ እለት እኛም ባድመን ለመታደግ ሲሉ የተሰው ወንድሞቻችንና ልጆቻችንን የምንዘክርበት ይሆናል … 

በጀግንነት የደመቀው “ዘመቻ ፀሀይ ግባት” እራሱ ላይ ግብዓተ መሬቱ የሚፈፀምበት እለት … የክህደት ዕለት!!!

Leave A Reply

Your email address will not be published.