ኢትዮጵያና ኖርዌይ በስደትና በስደተኞች አያያዝ የበለጠ ተቀራርበው ለመስራት ተስማሙ

(ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር)- የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ሂሩት ዘመነ የኖርዌይን የስደተኞችና የውህደት ሚኒስትር ሲልቪ ሊስታውግን ትናንት በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

ወ/ሮ ሂሩት በዚሁ ወቅት እንዳሉት ፍልሰት የአለማችን አጀንዳ መሆኑንና ይህም በበርከታ አገራት ላይ ተጽእኖ እያሳደረ እንደሚገኝ ገልጸው መፍትሄውም የፍልሰት መንስኤዎችን መፍታት እንደሚገባና ለዚህም በተባበሩት መንግስታት፣ በአፍሪካ ህብረትና ሌሎች ተቋማት በኩል የተለያዩ አቅጣጫዎችን በመቅረጽ መንቀሳቀስ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ስደተኞችን በመቀብል ግንባር ቀደም መሆኗን ገልጸው ይህን “ክፍት ካምፕ ፖሊሲን” በመከተል አርአያነት ያለው ተግባር እያከናወነች መሆኗን አስረድተዋል።

የስደተኞች መብት እንዳይጣስ፣ አስፈላጊ አቅርቦቶች እንዲሟሉ፣ የትምህርት እድል እንዲያገኙና በአገሪቱ ኢንቨስትመንት የስራ እድል እንዲፈጠርላቸው ኢትዮጵያ እየሰራች መሆኗንም ወ/ሮ ሂሩት ገልጸዋል።

በህዳር ወር 2010 ዓ.ም የኖረዌይ ልዑል አልጋ ወራሹ ልዑል ሃኮን ማገኑስ በኢትዮጵያ ያደረጉት ጉብኝት የአገራቱን ግንኙነት በተለያዩ ዘርፎች እየተጠናከረ የመምጣቱ ማሳያ መሆኑን ገልጸው ይህንም ኢትዮጵያ በበጎ እንደምታየው ተናግረዋል።

በደቡብ ሱዳን የሰላም ድርድር ሂደት ኖርዌይ ላበረከተችው ገንቢ ሚናም ወ/ሮ ሂሩት አመስግነዋል።

የኖርዌይ የስደተኞችና የውህደት ሚኒስትር ሲልቪ ሊስታውግን በበኩላቸው ኢትዮጵያ ስደተኞችን በመቀበልና ህገ ወጥ ስደትን ለመግታት የምታደርገውን ጥረት አድንቀዋል።

አገራቸው በስደተኞችና በስደተኞች አያያዝ ዙሪያ ከኢትዮጵያና ሌሎች የአውሮፓ አገራት ጋር ተባብራ ለመስራት ዝግጁ መሆኗን አስረድተዋል።

በተለይም ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ደላሎችን ለመቆጣጠርና ወደ ፍትህ ለማቅረብ የጋራ ጥረት እንደሚሻ ሚኒስትሯ ተናግረዋል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.