ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል በተከናወነው የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ የዓለም አቀፍ ሽልማት ተረከበች

(ኤፍ.ቢ.ሲ)- ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል በተከናወነው የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሽልማት ተረከበች።

ሽልማቱ በረሃማነትን እና የመሬት መሸርሸርን በተሳካ ሁኔታ የሚከላከሉ ህጎችን እና አሰራሮችን አውጥቶ ተግባር ላይ በማዋል ውጤታማ ለሆኑ ሀገራት የሚሰጥ ነው ተብሏል።

ዓላማውም በረሃማነትን ለመከላከል እና ውጤታማ ዘዴዎችን ለማጠናከር ትኩረት ያደረገ መሆኑ ተገልጿል።

በረሃማነትን መዋጋት አካባቢን ለመጠበቅ ብቻ ሳይሆን ለማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ መረጋጋት ትልቅ ሚና እንዳለው ተጠቁሟል።

በዚህ ተግባር የላቀ ውጤት ያስመዘገበው የትግራይ ክልልም ሽልማቱን ተረክቧል።

ክልሉም በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ እና የወጣት ተሳትፎ ጥምረት በመጠቀም የትግራይ ህዝብ በከፍተኛ መጠን መሬት መልሶ የማልማት ስራ በመስራት ውጤታማ መሆኑ ተገልጿል።

በውጤቱም የአፈር መሸርሸር በእጅጉ በመቀነሱ፣ የከርሰ ምድር ውኃ በመጨመር፣ ዘላቂ የግብርና ልምዶችን በማጠናከር፣ በምግብ እህል ራስን በመቻል እና የኢኮኖሚ ዕድገት በማምጣት ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጓል ተብሏል።

ሽልማቱ የተሰጠው መስከረም 1 ቀን 2010 ዓ.ም የምርጥ ፖሊሲ ሽልማት በዓል አስመልክቶ በቻይና በተካሄደው የተባበሩት መንግስታት የልማት ኮንፈረንስ 13ኛ ስብሰባ ላይ መሆኑ ተነግሯል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.