ኢትዮጵያ እና ግብፅ በግድቡ ዙሪያ በአዲስ መንፈስ በጋራ ለመስራት ተስማሙ

(ኤፍ ቢ ሲ)- ኢትዮጵያ እና ግብፅ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ዙሪያ የሁለቱን ሃገራት የመልማት ፍላጎት ባከበረ መልኩ በአዲስ መንፈስ በጋራ ለመስራት ተስማሙ።

ለሁለት ቀናት ይፋዊ ጉብኝት ለማድረግ ከትላንት በስትያ ካይሮ የገቡት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከግብጹ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አል ሲሲ ጋር መክረዋል።

መሪዎቹ በውይይታቸው ወቅት በሁለትዮሽና አካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ መክረዋል።

በግድቡ ዙሪያ ባደረጉት ውይይትም የሃገራቱን የመልማት ፍላጎት ባከበረ መልኩ በአዲስ መንፈስ በጋራ ለመስራት መስማማታቸውን የግብጽ ፕሬዚዳንታዊ ጽህፈት ቃል አቀባይ ባሳም ራዲ ተናግረዋል።

ከዚህ ባለፈም በተለያዩ መስኮች በተለይም በፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ መስኮች ያላቸውን ትብብር ማጠናከር ይገባል ማለታቸውንም ነው የተናገሩት።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ እና ፕሬዚዳንት አል ሲ ሲ የሀገራቱን ሁለንተናዊ ግንኙነት ከፍ ለማድረግም ከስምምነት ላይ ደርሰዋል።

ሁለቱ መሪዎች ሃገራቱ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን በማጠናከር በጋራ መስራት ይገባል ማለታቸውንም ቃል አቀባዩ ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በዑጋንዳ ለሁለት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል።

በጉብኝታቸው ወቅትም ከዑጋንዳው ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ጋር በሁለትዮሽና አካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ መክረዋል።

ከዚህ ባለፈም የሁለቱን ሀገራት የንግድ ግንኙነት ለማሳደግም ስምምነት ላይ መድረሳቸው የሚታወስ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዑጋንዳ ቆይታቸው ዑጋንዳ ለአፍሪካ እና ለዑጋንዳ መልካም ስራ ለሰሩ ሰዎች የምታበረክተውን ሜዳሊያ ከፕሬዚዳንት ዮዌሪ ሙሴቬኒ እጅ ተቀብለዋል።

ይህ ሽልማት በተለያዩ ጉዳዮች አስተዋፅኦ አበርክተዋል ተብለው ለተመረጡ አፍሪካዊ መሪዎች የዑጋንዳ መንግስት የሚበያበረክተው ሽልማት ነው።

የዑጋንዳ ጉብኝታቸውን ሲያጠናቅቁ ካይሮ ገብተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ቀደም ሲል በጅቡቲ፣ ሱዳን፣ ኬንያ፣ ሳዑዲ ዓረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.