በአፍዴራ በቱሪስቶች ላይ በተፈጸመ ጥቃት የአንድ ሰው ህይወት አለፈ

(ኤፍ.ቢ.ሲ)- በአፋር ክልል አፍዴራ ወረዳ ለጊዜው ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች በቱሪስቶች ላይ በፈጸሙት ጥቃት የአንድ ሰው ህይወት ማለፉን ፖሊስ አስታወቀ።

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ አሎ አፍኬኤ እንደገለጹት በወረዳው ህዳር 24 ቀን ምሽት አራት ሰዓት ተኩል ተኩስ በመክፈት በተፈፀመው በዚሁ ጥቃት ህይወቱ ካለፈው ሌላ አንድ ሰው የመቁሰል ጉዳት ደርሶበታል።

ህይወቱ ያለፈው የውጭ ዜጋ ሲሆን፥ የመቁሰል ጉዳቱ የደረሰበት ደግሞ ኢትዮጵያዊ ነው።

ጉዳቱ የደረሰባቸው ሁለቱ ሰዎች አብረው ከነበሩ ሌሎች በርካታ ቱሪስቶች ተነጥለው በመሄድ ፎቶ በማንሳት ላይ እንዳሉ በተከፈተባቸው ተኩስ እንደሆነ ተመልክቷል።

የአፍዴራ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሙሳ መሃመድ በበኩላቸው ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች ጨለማን ተገን በማድረግ ጥቃቱን መፈፀማቸውን አስታውቀዋል።

በወረዳው ልዩ ስሙ ኤርታአሌ የተባለውን የቱሪስት ስፍራን ለመጎብኘት በመንቀሳቀስ ላይ በነበሩ ቱሪስቶች ላይ ተኩስ ተከፍቶ በተፈፀመው ጥቃት ጉዳቱ ሊደርስ እንደቻለ አመልክተዋል።

ጥቃት ፈፃሚዎችን ለመያዝ ከሚመለከታቸው የፍትህ አካላት ጋር በመቀናጀት ክትትልና ምርመራ እየተደረገ መሆኑን አቶ ሙሳ ገልጸዋል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.