ኢትዮጵያ ወደ ጂቡቲ የዘረጋቻቸው መሰረት ልማቶች ወደቡን ለ50 ዓመታት መጠቀም ያስችላታል ተባለ

(ኤፍ.ቢ.ሲ)- ኢትዮጵያ ወደ ጂቡቲ የዘረጋቻቸው መሰረት ልማቶች ወደቡን ለ50 ዓመታት በአስተማማኝ ሁኔታ መጠቀም የሚያስችላት መሆኑን የትራንስፖርት ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ አስታወቁ።

ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሼዴ ዛሬ በጂቡቲ እየተካሄደ ባለው የቀጠናዊ ትስስርና የግሉ ዘርፍ የመሰረተ ልማት ፎረም ላይ በተጋባዥነት ኢትዮጵያን በመወከል ንግግር አድርገዋል።

በዚህም ሁለቱ ሀገራት በአሁኑ ወቅት ትስስራቸውን እያጠናከሩ መሆኑን የገለጹ ሲሆን፥ ከዚህ ውስጥም በ4 ነጥብ 5 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ወጪ የተገነባውና በቅርቡ አገልግሎት መስጠት የሚጀምረው የምድር ባቡር መስመር ተጠቃሽ ነው ብለዋል።

በአፍሪካ ሀገራት በሁለት መንግስታት በጋራ ከሚሰሩት ፕሮጀክቶች መካከል የባቡር ፕሮጀክቱ ተጠቃሽ ሲሆን፥ የሁለቱን ሀገራት ሁለንተናዊ እድገት እንደሚያፋጥን ይጠበቃል ነው ያሉት።

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያና ጅቡቲን የሚያስተሳስሩ ሶስት የመንገድ ግንባታዎች እየተካሄዱ ነው፤ እነዚህም ከአዲስ አበባ አዋሽ በጋላፊ፣ ከድሬዳዋ ደወሌ እንዲሁም ከታጁራ ወደብ ጋር የሚያገናኙ ትላልቅ ፕሮጀክቶች እንዳሉ ነው የገለጹት።

የውሃ ልማት ፕሮጀክቱም እንዲሁ በ350 ሚሊየን የአሜሪካ ዶር በጋራ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል እየተገነባ ያለው በአሁኑ ወቅት ሀገሪቱ ከኢትዮጵያ የመጠጥ ውሃ እያገኘች ነው ያሉት አቶ አህመድ፥ በቴሌኮም መሰረተ ልማትም መተሳሰራቸውንም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ከጅቡቲ ጋር ለመተሳሰር ከፍተኛ ወጪ በማውጣት የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎች ማድረጓ ለሚቀጥሉት 50 ዓመታት የጅቡቲን ወደብ በአስተማማኝ ሁኔታ እንድትጠቀም ያስችላታል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከሁሉም የምስራቅ አፍሪካ አገራት ጋር ትስስሯን ትቀጥላለች፤ በይበልጥ ወደብ ካላቸው አገራት ጋር የምታደርገውን ግንኙነት አጠናክራ እንደምትቀጥል ገልጸዋል።

የጅቡቲ የኢካኖሚና ፋይናንስ ሚኒስትር ኤሊያስ ሙሳ ደዋሌ በበኩላቸው የጅቡቲ እድገት ከኢትዮጵያ ሕዝብና መንግስት ጋር የተቆራኝ መሆኑን ገልጸዋል።

“ኢትዮጵያ እድገት ባስመዘገበች ቁጥር ከውጭ የምታስገባቸው የመሰረተ ልማት፣ የፍጆታና ሌሎች ቁሳቁሶች እየጨመሩ በመሔዳቸው ሀገራችንን ተጠቃሚ ያደርጋል” ብለዋል።

ጅቡቲ ከኢትዮጵያ ጋር በመንገድ፣ በኤሌትሪክ፣ በባቡር እና በውሃ መስኮች ትብብር ፈጥራ እየሰራች መሆኑን ገልጸዋል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.