ኢትዮጵያ የመንጋጋ ቆልፍን መቆጣጠር ከቻሉ አገራት መካከል አንዷ ሆነች

(ኢቢሲ)- ኢትዮጵያ በጨቅላ ህፃናትና እናቶች ላይ የሚከሰተውን የመንጋጋ ቆልፍን /ቲታነስ/ በቁጥጥር ስር ካዋሉ 42 የዓለም አገራት አንዷ መሆን እንደቻለች የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል፡፡

በኢትዮጵያ በሁሉም ክልሎች የዓለም ጤና ድርጅት፣ ከህፃናት አድን ድርጅትና ሌሎች ተባባሪ አካላት ጋር በጋራ ባደረጉት የማረጋገጥ ጥናት መንጋጋ ቆልፍ በተቀመጠው መስፈርት መሰረት ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠር መቻሉን አረጋግጠዋል፡፡

የመንጋጋ ቆልፍን በሽታ በአንድ ወረዳ በህይወት ከሚወለዱ 1000 ህፃናት የመከሰት እድሉ ከ1 በታች ሲሆን አንድ አገር ከበሽታው ነጻ መሆኗ እንደሚረጋገጥም በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የእናቶችና ህፃናት ጤና ረዳት ዳይሬክተርና የክትባት ኬዝ ቲም አስተባባሪ ወ/ሮ ሊያ ወንድወሰን ለኢቢሲ ገልፀዋል፡፡

ኢትዮጵያ የመንጋጋ ቆልፍ በሽታን ለመቆጣጠር ያከናወነቻቸው ውጤታማ ስራዎች ትልቁን ሚና እንደሚጫወቱም ወ/ሮ ሊያ ተናግረዋል፡፡

በተለይም በህክምና ተቋማት የሚወልዱ እናቶችን ቁጥር ወደ 80 በመቶ ለማድረስ መቻሉ፣ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሞያዎች ክትትል መሻሻሉ እንዲሁም የክትባት ተደራሽነት በአስተማማኝ ደረጃ ላይ መድረሱ ለውጤቱ መገኘት ዋነኛ ምክንያቶች መሆናቸው ተገልጿል፡፡

ቴታኖስን በመቆጣጠር ረገድ የተሰራው ስራ የሚያበረታታ ቢሆንም ዘላቂነቱን ለማረጋጋጥ የሚያስችሉ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠል እንደሚኖርባቸውም ወ/ሮ ሊያ ወንድወሰን አብራርተዋል፡፡

በተለምዶ የመንጋጋ ቆልፍ እየተባለ የሚጠራው ቴታኖስ መነሻው በአከባቢ ላይ የሚገኝ ባክቴሪያ ሲሆን በማንኛውም ሰው ላይ ሊከሰት የሚችል በሽታ ነው፡፡

በሽታ አምጭው ባክቴሪያ በቁስል፣ በእርግዝናና በወሊድ ወቅት፣ በጨቅላ ህፃናት እትብት አካባቢ በሚገኝ ቁስል ወደ ሰውነት መግባት ሲችል በሽታው ይከሰታል፡፡

በእናቶች ላይ የሚከሰተው መንጋጋ ቆልፍ በእርግዝና ወቅት በመጀመሪያዎቹ 6 ሳምንታት አልያም በውርጃ ጊዜ የሚከሰት ሲሆን በህፃናት ላይ ከተወለዱ ከ3ኛው ቀን እስከ 28ኛው ቀን ባሉት ጊዜያት በህፃናቱ የነርቭ ስርአት ውስጥ በመግባት በተለይ መንጋጋ አካባቢ ያሉ ስጋዎች እንዲጠነክሩ ያደርጋል፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.